
ሬድዋን ሁሴን እና ጌታቸው ረዳ፤ “ህወሓት በቀናት ውስጥ ጦርነት ይከፍታል” አሉ።
“ህወሓት በቀናት ውስጥ በፌደራል መንግሥቱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ወስኗል” ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ አልጀዚራ ላይ ባስነበቡት ጽሑፍ አስጠንቅቀዋል፡፡
ሬድዋን እና ጌታቸው በጋራ ባስነበቡት ጽሑፍ፣ “ጽምዶ” በሚል ቅንጅት የፈጠሩ ኃይሎች ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት ጎትተው ለማስገባት እየተንቀሳሱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአስመራ፣ በመቀሌ እና በሱዳን በድብቅና ግልጽ በሆኑ ስብሰባዎች የተፈጠረው የጽምዶ ጥምረት፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ጌታቸው እና ሬድዋን “አክራሪና ርዝራዝ ቡድን ነው” ያሉት ህወሓት፣ በአስመራ ድጋፍና አጋዥነት፣ በሚቀጥሉት ቀናት ጥቃት ለመሰንሰር መወሰኑን አረጋግጠዋል፡፡
ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ህወሓትና የጦርነት አጀንዳውን በግልጽ ውድቅ ቢያደርግም፣ ቡድኑ የግጭት መቀስቀስ አባዜውን አልተወም ብለዋል፡፡
ህወሓት ከኤርትራ መንግስት በቀጥታ በሚያገኘው ድጋፍ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊ ኃይል መመልመል፣ ማሰልጠን እና ማስታጠቅ ቀጥሏልም ሲሉም አክለዋል።
