ለምሳሌ:
- የ 2018 የኢትዮ-ኤርትራ ጥድፍድፍ ያለውና ከህዝብ የተደበቀው ወዳጅነትና ስምምነት ሳይሰነብት ፈርሶ ዛሬ ሁለቱ ሃገሮች ጠላት ሆነው ሊበላሉ ተፋጠዋል። በእርግጥ ይበላላሉ ወይ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።
- በተመሳሳይ ወያኔ በ2018 በሰላማዊ መንገድ ከስልጣን ተሰናብቶ አዲስ መንግስት ተዋቅሯል፣ ወንጀል የሰሩትም በምህረት ታልፈው ጡረታ ወጥተዋል በተባለ ማግስት፣ ብልፅግናና የወደቀው ጁንታ ጦርነት ውስጥ ተዘፈቁ። ይኸ በግዴለሽነት ሃላፊነት የጎደለውና የተድበሰበሰ የይቅርታ ፍቺ ፣ በጉዳዩ ገና ሲጀመር ያዘነውን ህዝብ በስሜት ኮርኩሮ፣ ለእርስ በእርስ ዕልቂት ገንፍሎ እንዲወጣ አደረገ። በ 2022 የተደረገውም የፕሪቶሪያ ስምምነት የተወሰኑ ወገኖችን ያሳተፈና በድብቅ የተደረገ ስለነበረ፣ ዛሬ ውሉ ፈርሶ፣ ሁለቱ የወታደር ኃይሎች በድጋሚ ሊተራረዱ ተፋጠዋል።
- ተቃዋሚዎች በፖለቲካ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ከእስር ተፈተዋል ከውጭም በነፃነት ሃገራቸው ገብተው እንዲታገሉ ተስተካክሏል ከተባለ በኋላ፣ የተወሰኑትን የፖለቲካና ሲቪል አቀንቃኞች ማግለልና ማሳደድ ዛሬ ለሚገኘው የሃገር ውስጥ ሰላም መደፍረስ ምክንያት ሆኗል። ሃገሪቷን በልማት ፖለቲካና በፕሮፓጋንዳ ካጥለቀለቅናት፣ “ሽፍታው ብን ብሎ ይጠፋል” የተባለው የተጭበረበረና የተድበሰበሰ አስተሳሰብም ብዙ አለመረጋጋትና ዕልቂት አስከተለ። ከዚህም ጋራ በተያያዘ፣ “የሰላም መደፍረሱ የእኔን ክልል ስለማይነካ እነሱ እርስ በእርሳቸው ቢበላሉ ምን አገባኝ” የሚል የተንሻፈፈና በጎጠኝነት የከረረ አስተሳሰብ ወለደ።
- ልክ እንደ ፖለቲካው፣ ልማቱም ‘እንደ እነ ቶሎ ቶሎ ቤት’ ያለ ጥልቅ ፊዚቢሊቲ ጥናት በጥድፊያ ነው የሚሰራው። ብዙ መንገዶች መሰራታቸው በጎ ነገር ሆኖ ሳለ፣ የትራንስፖርት ችግር እንዴት መፈታት እንዳለበት መፍትሄ ሳይጠና በግርግር እንደተሰራ ነባራዊው ሁኔታ ያሳብቃል። የመንገድ ብዛት ብቻ የትራፊክ መጨናነቅን እንደማይፈታ ለመረዳት ደግሞ፣ በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ያለውን የሚዘገንን የህዝብና የአውቶሞቢል መጨናነቅ በየከተማው ክፍሎች እየተዘዋወሩ ማየት ነው።
- ደርግ “ወንዞች ይገደቡ ይዋሉ ለልማት” ያለውን ፉከራ ፒፒ ገልብጦ “ወንዞች ይጠረጉ ይዋሉ ለዕርካታ” ብሎ ሿ ሿ እያደረገው ነው። ሃሳቡ ባይከፋም፣ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲቀረፅ የፕራዮሪቲ ሊስት መዘጋጀት ይኖርበታል። የነጭ ፈረስ ምስሎች በሚሊዮን ብር ወጪ ቀበና ወንዝ ዳር በሚቀረፁበት ሰዓታት፣ በዚያው አካባቢ በጠኔ የሚረግፉ ብዙ ቤተሰቦች አሉ። በተለይ ከከተማው መውጫ ላይ የሚደረጉት የወንዝ ዳር ልማቶች፣ ከነባር መኖሪያ ቤቶች ዕድገት ደረጃና ፍሳሽ ጋር ስላልተቀናጁ ወደፊት በከፊል እንደሚፈርሱ ወይንም እንደሚታደሱ ያስታውቃል።
- የህንፃ ግንባታው መብዛት የኢኮኖሚውን መነቃቃት የሚያሳይ ይመስለኛል ሆኖም በአብዛኛው ያለ ጥራትና ዕውቀት በጥድፊያ ነው የሚሰራው። በዚያ ላይ የግንባታ ፈቃድ ሰጭዎችና አስፈፃሚዎች በከፍተኛ ሌብነትና ሙስና የተዘፈቁ ናቸው። ግብአቶቹም ከተለያየ ሃገሮች በዘፈቀደ ስለሚመጡ ስታንዳርድ የሚባል ነገር የለም። በትልልቅ ተቋራጮች ከሚገነቡት ውጪ፣ አብዛኞቹ ህንፃዎች አስቀያሚና መናኛዎች ይመስላሉ። የዛሬ አስር ዓመት የተገነቡት አርጅተውና ተቦዳድሰው ይታያሉ። “መልከ ጥፉን…” እንደሚባለው፣ ለማጭበርበርና ለመሸፋፈን ብቻ ሲባል በመንግስት ትዕዛዝ በነጭ ቀለምና በመብራት አሸብርቀዋል። ታዲያ ዕውቀቱ ያላቸው ሰዎች “ውስጡን ለቄስ” ይሉታል። የግለሰቦችን የህንፃ ቀለምና የውጪ መብራት ምርጫ በማስገደድ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሃገር ብትሆን አይደንቀኝም።