በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ በተፈጸመ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ህጻናትን እና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ጥቃቱ ማክሰኞ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. ከወረዳው ዋና ከተማ ዱርቤቴ 40 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው አርጌ (ዝብስት) በተባለች ታዳጊ ከተማ በተከታታይ ሦስት ጊዜ መፈጸሙን እማኞች እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ጠዋት 1፡10 አካባቢ በከተማዋ ገበያ አካባቢ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እና ጤና ጣቢያ ላይ ጥቃቱ እንደተፈጸመ እማኝነታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ “ከልጅ እስከ አዋቂ ያለቀበት” ነው ብለውታል።
በድሮን ጥቃቱ መረብ ኳስ ይጫወቱ የነበሩ ልጆች፣ ለሽምግል እና የተቀመጡ ሰዎች፣ ህክምና ላይ የነበሩ እናቶች፣ የጉልበት ሠራተኞች፣ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እና እርሻ ቦታ ላይ የነበሩ ሰዎች ሰለባ እንደሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ጥቃት የደረሰባቸው ሦስቱም አካባቢዎች በቅርብ ርቀት ላይ እንደሚገኙ ነዋሪዎች የጠቆሙ ሲሆን፤ ቢቢሲ አካባቢዎቹ ከ300 ሜትር ራዲዬስ ባነሰ ርቀት እንደሚገኙ በካርታ እና በሳተላይት ምሥል አረጋግጧል።
“ሰው መሆን ያስጠላል። ሰው በሰው ላይ እንደዚህ ዓይነት ጭካኔ ሲፈጽም አይቼ አላውቅም” ሲሉ የደረሰውን ጉዳት የሚገልጹት ነዋሪው፤ “ከባድ፤ አስከፊ ጥቃት ነው የደረሰው” ብለዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ በትምህርት ቤቱ ጊቢ ውስጥ ኳስ ጨዋታ ላይ የነበሩት ከ13 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ነፍሰ ጡር እናቶች የጥቃቱ አስከፊነት መገለጫ ናቸው ብለዋል።
ጤና ጣቢያው ላይ በደረሰው ጥቃት የእርግዝን ክትትል እና ምጥ ላይ የነበሩ እናቶች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህን ያረጋገጡት እና ጥቃቱ ሲደርስ ጤና ጣቢያው ውስጥ የነበሩ አንድ ባለሙያ፤ የእናቶች ክትትል ማዕከል ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ መሆኑን ጠቅሰው፤ አምስት ነፍሰ ጡር እናቶች እና ሌሎች ሁለት አስታማሚዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
“ውስጥ የተኙ እናቶች ላይ ነው የወደቀው” ያሉት የጤና ጣቢያው ባለሙያ በጥቃቱ ሦስት ሴት የጤና ባለሙያዎች ላይም የመቁሰል ጉዳት መድረሱን አመልክተው፤ የደረሰውን ጉዳት “መሪር” ሲሉ ገልጸውታል።
ሦስት እናቶችም “በድንጋጤ” ጽንሳቸው እንደወረደባቸው ባለሙያው ተናግረዋል።
https://www.bbc.com/amharic/articles/c5y3l8vkldlo
-
Za-Ilmaknun
- Member
- Posts: 4486
- Joined: 15 Jun 2018, 17:40