-8 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል
-በግጭት ምክንያት 5,568 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል
-በአማራ ክልል ድርቅ 85 ሺሕ የቤት እንስሳት ሞተዋል
የምክር ቤቱ አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከልም የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን፣ እየተንሰራፋ ይገኛል ያሉትን ብልሹ አሠራርና የኮንትሮባንድ ንግድን፣ የሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያና የኑሮ ድጎማን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና በኢንቨስትመንት ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን የተመለከቱ ይገኙባቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ መንግሥታቸው ባለፉት ስድስት ዓመታት ባካሄደው አገራዊ ሪፎርም ያልተዳሰሰ ዘርፍ አለመኖሩን፣ በዚህም የተገኘው ውጤት ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ እንደ አገር ማንሰራራት የምትጀምርበት ዓመት እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም. 8.1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ጥቂት አገሮች ተርታ ያሠለፈና በርካታ አገሮችም ዕውቅና የሰጡት እንደሆነ አስታውቀዋል።
በዚህም የተነሳ፣ ‹‹ከብዙ አገሮች ጋር በምናደርገው ግንኙነት የተገኘውን ዕድገት ለማመን የተቸገሩ፣ ምን አግኝታችኋል? ነዳጅ አገኛችሁ ወይ? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት አሉ፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ሪፎርሞቻችንን ጨርሰን አሁን ማንሰራራት የምንጀምርበትና በታሪካችን ዓይተን የማናውቃቸው ውጤቶችን እያየን ትውልድን ወደ ማፅናት ሥራ የምናሸጋግርበት ዘመን መጀመሪያ ይሆናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
https://www.ethiopianreporter.com/135062/