
በአዲስ አበባ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ዳግም ተሰማ
በአዲስ አበባ ባለፈው ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ቀጥሎ አሁንም ዳግም መከሰቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶክተር ኤሊያስ ሌዊ ለኢቢሲ አረጋግጠዋል።
ዛሬ ጠዋት 1:37 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ ላይ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት አዲስ አበባ ድረስ መሰማቱንም ተናግረዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ባለፈው በተከሰተበት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ሲሆን በሬክተር ስኬል 4.6 አካባቢ እነደሆነም ዶክተር ኤሊያስ ሌዊ ለኢቢሲ ሳይበር አረጋግጠዋል።
ሰሞኑን በተደጋጋሚ በአካባቢው የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴው እንዳልቆመ የተናገሩት ዶክተር ኤሊያስ ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ እንዳልሆነም ተናግረዋል።
ለመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት የሆነው ቅልጥ አለት መሬት ውስጥ መምጣቱ መሆኑ የተናገሩት ዶክተር ኤሊያስ ይሄው እንቅስቃሴ ወደላይ አለመወጣቱን ነው የተናገሩት።
ላለፉት 19 ተከታታይ ቀናት ያህል ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን እና አሁንም ያለውን ሁኔታ እየተከታተልን ነው ብለዋል ዶክተር ኤሊያስ።