
፟-
-
"አብይ አህመድ በሰው ደም የሚጫወት አረመኔ፣ አገር እንዴት እንደሚመራ የማያውቅ አቅመቢስ፣ ክፉ እና በስልጣን ጥም ያበደ አምባገነን መሪ ነው!" አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
ሙሉ ሰነዱን ከዚህ ላይ ያንብቡ
"...በእኔ ድጋፍ እና ትግል ጭምር ስልጣን ለመጨበጥ የበቃው አብይ አህመድ ከሁላችንም ግምት ውጭ በሰው ደም የሚጫወት አረመኔ፣ ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ የተናቀችና የረከሰች አገር ያደረገ፣ አገር እንዴት እንደሚመራ የማያውቅ አቅመቢስ፣ ክፉ እና በስልጣን ጥም ያበደ አምባገነን መሪ ሆኖ ብቅ አለ። የኢትዮዽያ ሕዝብ የለውጥ ምኞትም ዳግም ተኮላሸ። እኔም በዛ የሕዝብ ብሶት በወለደው የለውጥ እንቅስቃሴ ሚና እንደነበረው ሰው በግሌ የሚሰማኝን በሚከተሉት ሶስት ጉዳዮች አተኩሬ ለማቅረብ እፈልጋለሁ።
በመጀመሪያ ደረጃ የአገር እና የህዝብን ችግር በዘላቂነት ይፈታል ብየ የተሰለፈኩበት “የለውጥ” እንቅስቃሴ በቅጥፈትና ቅዤት ተሸፍኖ አቅጣጫውን ሲስት በትግል እንዲስተካከል የድርሻየን ባለመወጣት፣ ከሁሉም በላይ ግን አብይ አህመድን የመሰለ ደካማ እና ክፉ ሰው የኢትዮዽያ መሪ እንዲሆን ድጋፍ በመስጠቴ እና የሱም ተሿሚ ሆኘ በማገልገሌ ልባዊ ጸጸት ይሰማኛል። የዚህ አገዛዝ አካል ሆኘ በሕዝቡ ላይ በተፈፀሙ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ጥቃቶች፣ለደረሱ እልቂቶች፣ መፈናቀሎች፣ አፈናዎች እና ሌሎችም ልዩ ልዩ አካላዊና ስነልቦናዊ በደሎች ሁሉ በአጠቃላይ የኢትዮዽያን ሕዝብ፣ በተለየ ሁኔታ ደግሞ በዚሁ በብልፅግና አገዛዝ ለከፋ ጥቃት ለተዳረገው የአማራ ሕዝብ ልባዊ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
ሁለተኛ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን እና የፖለቲካ መሪ ለአጠፋቸው ጥፋቶች በማንኛውም ጊዜ ሃፊነት መውሰድ አለበት ብየ አስባለሁ። ከዚያም አልፎ በፈፀማቸው ጥፋቶችም ተጠያቂ መሆን የሚገባው መሆኑን በፅኑ አምናለሁ።ስለሆነም እኔም የወቅቱ አገዛዝ ከስልጣን ተወግዶ እውነተኛ የሽግግር ጊዜ ፍትህ በአገራችን የሚሰፍንበት ጊዜ ሲመጣ በሚመለከተኝ ጉዳይ ተጠያቂ ለመሆን ዝግጁ መሆኔን እገልፃለሁ።
ሶስተኛ የኢትዮዽያም ሆነ የአማራ ሕዝብ የደረሰበትን በደል የሚመጥን ካሳ ማናችንም ከፍለን መጨረስ የምንችል አይመስለኝም። ይሁንና በእኔ በኩል ለተበደለው ወገኔ ማድረግ የምችለው የወቅቱን የአማራ ሕዝብ ትግልበመቀላቀል አቅሜ በፈቀደልኝ መጠን በቀሪው ዘመኔ ሕዝብን ለመካስ የምችለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ፍላጎት እና ዝግጁነት ያለኝ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እገልፃለሁ።"
ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሰነድ የተወሰደ
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሰነድ የተወሰደ “ሕዝባዊ ጥያቄን በኃይል መጨፍለቅ አይቻልም” በሚል ርዕስ ለህዝብ ያደረሱት ሙሉ ጽሑፍ ከዝሂህ በታች ቀርቧል!!
*********************
“ሕዝባዊ ጥያቄን በኃይል መጨፍለቅ አይቻልም” ገዱ አንዳርጋቸው
1. መግቢያ
የአማራ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ይዟቸው የተነሳውን ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ለማዳፈን፣ እንዲሁም በመላ ክልሉ ትጥቅ የማስፈታት ግብ ተይዞ በአገዛዙ የተከፈተውን ወታደራዊ ዘመቻ ለመመከት የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏ። ይህንን በሁሉም አካባቢዎች በአጭር ጊዜ የተስፋፋውን ሕዝባዊ አመፅ በወታደራዊ ኃይል ለማፈን እና ሕዝቡ ዳግም የመብት ጥያቄ እንዳያነሳ አንገት ለማስደፋት ሲባል በመላው ኢትዮጵያ በሚኖረው የአማራ ሕዝብ ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ብሄር ተኮር ፋሽስታዊ የሆነ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ መተግበር ከጀመረ ደግሞ እነሆ አመት አለፈው። ባለፈው አንድ አመት ውስጥም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግም የብልፅግና አገዛዝ የአማራን ሕዝብ በማሳደድ ዘርፈ ብዙ ጉዳት አድርሷል።አገዛዙ አማራን ለማንበርከክ በክልሉ ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ያለ የሌለውን አቅም ተጠቅሞ እንኳን አንድ አገሩን አስተዳድራለሁ የሚል ኃይል ቀርቶ ሃላፊነት የሚሰማው የውጭ ወራሪ ኃይል እንኳን ሊያደርገው የማይችለውን አስከፊ ድርጊት በሕዝብ ላይ ፈፅሟል።አሁንም ይኸው በወታደራዊ ኮማንድ ፖስት ክልሉን እና ሕዝቡን የማጎሳቆል የጥፋት ዘመቻ ቀጥሏል። በሌላ በኩል ደግሞ የአማራ ሕዝብም በጀግኖች ልጆቹ እየተመራ የተቃጣበትን ዘርፈ ብዙ ጥቃት ለመመከት አኩሪ ተጋድሎ ሲያደርግ ከርሟል።ባለው ወታደራዊ ጉልበት ተማምኖ የሕዝብን ሰላማዊ ጥያቄ ለማፈንና አንገት ለማስደፋት የጥፋት ዘመቻ የከፈተው አገዛዝ አስካሁን እንደታየው ውጤቱ እንዳሰበው ሳይሆን እንደ ልማዱ በሕዝባዊ ትግል እየተዋረደ እና እየተሸነፈ ይገኛል።
ይህንን ጽሁፌን ማንበብ የጀመራችሁ ወገኖቸ በውስጣችሁ ብዙ ጥያቄ እየተመላለሰ እንደሆነ እገምታለሁ። ስለ ዛሬው እና ስለ ወደፊቱ ብዙ ከማለቴ በፊት በቅድሚያ ስለ እራሴ እዚህ ላይ ቆም ብየ ጥቂት ለማለት እና በውስጣችሁ ይኖራል ብየ የምገምተውን ጥያቄ መልሸ ለማለፍ ልሞክር።
ከ1982 መጨረሻ ጀምሮ የብአዴን/ኢህአዴግ አባል በመሆን በአስፈፃሚነት እና እስከ የክልል ፕሬዘደንትነት በደረሱ የተለያዩ የአመራር ሀላፊነቶች አገሬን አገልግያለሁ። እስከ 2014 አመተ ምህረት አጋማሽ ድረስ ደግሞ የብልጽግና አባል በመሆን በፌደራል መንግስት ለሶስት አመታት በሚኒስትርነት ሰርቻለሁ። የኢህአዴግ አባል የሆንኩት እና የወጣትነት ዘመኔን ያሳለፍኩት ድርጅቱ የሚከተለውን ርዕዮተአለም በመደገፍ እና ለህዝብ የሚበጅ አላማ አለው ብየ ከልቤ በማመን ቢሆንም በውስጡ ያሉ ውስንነቶች በፓርቲ የውስጥ ትግል በሂደት ሊፈቱ ይችላሉ የሚል የጠነከረ ተስፋ እና እምነትም ነበረኝ። በዚህም ምክኒያት ነበር በ2010 ዓ.ም በአገራችን በሕዝብ ግፊት እና በውስጣዊ ትግል በመጣው “ለውጥ” ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረግሁት። በዚያ ለውጥ ከፍተኛ ተስፋ ካሳደሩት ሰዎች መካከልም አንዱ ነበርኩ። ያ “ለውጥ” በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩትን ጠንካራ ጎኖች የሚያስቀጥል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጡ የሚታዩበትን የተለያዩ የፖሊሲ፣ የአስተሳሰብ፣ የአፈፃፀም ድክመቶች እና ችግሮች የሚያስወግድ እውነተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚል ከፍተኛ እምነት ነበረኝ።
ይህ ተስፋየ እውን ይሆን ዘንድም ሁኔታው በፈቀደልኝ መጠን ጥረት ለማድረግ ሞክሬ ነበር። ሆኖም ግን በተለያዩ ምክንያቶች ምኞቴ አልተሳካም። በ”ለውጡ” አሳድሬው የነበረው ተስፋ ብዙም ሳይቆይ አቅጣጫውን ስቶ፣ ለውጥ ሳይሆን ነውጥ እና ቀውስ ሆነና የሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ህይወት ቅርጥፍ አድርጎ የሚበላ ሆነ። ሰዎች በሚይዙት የፖለቲካ አመለካከት፣ በሚከተሉት እምነት እና ብሄራዊ ማንነታቸው እየተለዩ በጅምላ የሚገደሉበት፣ የሚታሰሩበት እና የሚሰቃዩበት ሁኔታ ተስፋፍቶ መንግስታዊ ፖሊሲ ሆነ። የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማቶችን አውድሞ አገሪቱን ባዶ እጇን የሚያስቀር አገዛዝ እንዲፈጠር አደረገ።
በእኔ ድጋፍ እና ትግል ጭምር ስልጣን ለመጨበጥ የበቃው አቢይ አህመድ ከሁላችንም ግምት ውጭ በሰው ደም የሚጫወት አረመኔ፣ ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ የተናቀችና የረከሰች አገር ያደረገ፣ አገር እንዴት እንደሚመራ የማያውቅ አቅመቢስ፣ ክፉ እና በስልጣን ጥም ያበደ አምባገነን መሪ ሆኖ ብቅ አለ። የኢትዮዽያ ሕዝብ የለውጥ ምኞትም ዳግም ተኮላሸ። እኔም በዛ የሕዝብ ብሶት በወለደው የለውጥ እንቅስቃሴ ሚና እንደነበረው ሰው በግሌ የሚሰማኝን በሚከተሉት ሶስት ጉዳዮች አተኩሬ ለማቅረብ እፈልጋለሁ።
በመጀመሪያ ደረጃ የአገር እና የህዝብን ችግር በዘላቂነት ይፈታል ብየ የተሰለፈኩበት “የለውጥ” እንቅስቃሴ በቅጥፈትና ቅዤት ተሸፍኖ አቅጣጫውን ሲስት በትግል እንዲስተካከል የድርሻየን ባለመወጣት፣ ከሁሉም በላይ ግን አብይ አህመድን የመሰለ ደካማ እና ክፉ ሰው የኢትዮዽያ መሪ እንዲሆን ድጋፍ በመስጠቴ እና የሱም ተሿሚ ሆኘ በማገልገሌ ልባዊ ጸጸት ይሰማኛል። የዚህ አገዛዝ አካል ሆኘ በሕዝቡ ላይ በተፈፀሙ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ጥቃቶች፣ለደረሱ እልቂቶች፣ መፈናቀሎች፣ አፈናዎች እና ሌሎችም ልዩ ልዩ አካላዊና ስነልቦናዊ በደሎች ሁሉ በአጠቃላይ የኢትዮዽያን ሕዝብ፣ በተለየ ሁኔታ ደግሞ በዚሁ በብልፅግና አገዛዝ ለከፋ ጥቃት ለተዳረገው የአማራ ሕዝብ ልባዊ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
ሁለተኛ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን እና የፖለቲካ መሪ ለአጠፋቸው ጥፋቶች በማንኛውም ጊዜ ሃፊነት መውሰድ አለበት ብየ አስባለሁ። ከዚያም አልፎ በፈፀማቸው ጥፋቶችም ተጠያቂ መሆን የሚገባው መሆኑን በፅኑ አምናለሁ።ስለሆነም እኔም የወቅቱ አገዛዝ ከስልጣን ተወግዶ እውነተኛ የሽግግር ጊዜ ፍትህ በአገራችን የሚሰፍንበት ጊዜ ሲመጣ በሚመለከተኝ ጉዳይ ተጠያቂ ለመሆን ዝግጁ መሆኔን እገልፃለሁ።
ሶስተኛ የኢትዮዽያም ሆነ የአማራ ሕዝብ የደረሰበትን በደል የሚመጥን ካሳ ማናችንም ከፍለን መጨረስ የምንችል አይመስለኝም። ይሁንና በእኔ በኩል ለተበደለው ወገኔ ማድረግ የምችለው የወቅቱን የአማራ ሕዝብ ትግል በመቀላቀል አቅሜ በፈቀደልኝ መጠን በቀሪው ዘመኔ ሕዝብን ለመካስ የምችለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ፍላጎት እና ዝግጁነት ያለኝ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እገልፃለሁ።
ስለ እራሴ ይህን ያህል ካልኩ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያለኝን የግል ምልከታ እንደሚከተለው ላቅርብ።
2. አገዛዙ እና የአማራ ሕዝብ ትግል ያሉበት ሁኔታ፤
2.1 የብልፅግና አገዛዝ ያለበት ሁኔታ፤
በመጀመሪያ ደረጃ ግልፅ መሆን ያለበት አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኃይል የአንድ ግለሰብ እና ቡድን አላማና ፍላጎት ከማስጠበቅ ውጭ የማንንም የሕብረተሰብ ክፍል ፍላጎት እና ጥቅም የማስጠበቅ አላማ የሌለው ኃይል ነው ብየ አምናለሁ። የብልፅግና ቡድን አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ከ2010 ወዲህ በአገሪቱ ልማትን ሳይሆን ጦርነትን አቅዶ በየተራ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለማዳረስ በትጋት የሚሰራ፣ እራሱ አቅዶ በሚፈጥራቸው ጦርነቶች ምክንያት ለደረሰው የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ሞት፣ በቢሊዮኖች ዶላር ለሚቆጠር የኢትዮጵያውያን ሃብት እና ንብረት ውድመት፣ ለሚሊዮኖች ከቤት ንብረት መፈናቀል እና መሰደድ ተጠያቂ የሆነ አገዛዝ ነው። ለአምራቾች የተመቸ ሁኔታ ፈጥሮ ምርትን ከማሳደግ ይልቅ አገሪቱ እና ሕዝቦቿ በጥረታቸው የአፈሩትን ጥሪት በመቀራመት፣ የተረፈውንም ሸጦ ጦር መሳሪያ በመሸመት ኢትዮጵያውያንን ማለቂያ የሌለው መከራ ውስጥ ያስገባ አገዛዝ ነው የሚል አመለካከት አለኝ።
እጅግ የሚገርመውና የሚያሳዝነው ደግሞ አገዛዙ በየጊዜው ባካሄደው ጦርነት ከደረሰበት ሽንፈትም ሆነ ባደረሰው ዘርፈ ብዙ ጥፋት መፀፀት እና መማር የሚችል አለመሆኑ ነው። ይልቁንም የሚሊዮኖችን እልቂት ያስፈፀመበትን ዘመቻውን አሁንም ያለሃፍረት በህግ ማስከበር ሰበብ የቀጠለ፣ ህዝብን ለከፋ የኑሮ ውድነትና አስከፊ ድህነት የዳረገ፣ በቀጣይም ቀውስን ዋነኛ የአመራር ዘይቤው አድርጎ አገሪቱን ወደ ከፋው ጥፋት ለመምራት ቆርጦ የተነሳ አገዛዝ ነው። ዋና ባህሪውም ቀውስ መፍጠርና ቀውሱን በወታደራዊ ኃይል ለመቆጣጠር እየሞከረ በስልጣን የሚቆይበትን ጊዜ ማራዘም ነው።
የዚህ ኃይል ቁንጮ መጀመሪያ ወደ ስልጣን እንደመጣ በአገራችን የሚታዩ ችግሮችን የሚፈታ መስሎ ቢቀርብም በተግባር አገሪቱን ወደ ቀውስና መፈራረስ አቅጣጫ እየወሰዳት ይገኛል። በስልጣን በቆየባቸው ያለፉት ስድስት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ ላይ ያልደረሰ መከራ የለም። በመሆኑም ይህ አውዳሚ ቡድን ምንም ያህል ሕዝብን ለመደለል ቢሞክርም፣ በእጁ በሚገኙ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያዎቹ አማካኝነት የሌለውን በጎ ገፅታ ለመገንባት እና ራሱ የፈጠራቸውን ችግሮች በሌላ ውጫዊ ኃይል ለማመካኘት ጥረት ቢያደርግም በተግባር ግን ቅቡልነት ያጣ እና በሕዝብ የተጠላ አገዛዝ ሆኗል። ሰሞኑን በወሰደው የውጭ ምንዛሬ መጠንን በገበያ ዋጋ የመወሰን እርምጃ የሚያሳየን የውጭ ኃይሎች ተላላኪ መሆኑን እና ሃላፊነት በጎደለው እርምጃው አሁንም አገሪቱን በሁሉም መስክ ወደመቀመቅ ከማስገባት የማይመለስ መሆኑን ነው።
በሕዝብ ዘንድ እየገጠመው ያለውን ጠንካራ ፖለቲካዊ ተቃውሞ በኃይል ለመቀልበስ የአገሪቱን መከላከያ በመሳሪያነት በመጠቀሙ ሰራዊቱም በእጅጉ ተዳክሟል።ከወገኑ ጋር ሃላፊነት በጎደለው መንገድ እንዲጋጭ በመደረጉ የተሰላቸ፣ የመዋጋት ፍላጎት የሌለው እና የማድረግ አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሟሸሸ የመጣ ኃይል ሆኗል። በብቃት የተደራጀ እና የተባበረ ሃይል ባለመኖሩ ነው እንጅ ስርዐቱ በሁሉም መስክ ተዳክሞ ምንም ማድረግ በማይችልበት ደረጃ ደርሷል። በአሁኑ ወቅት የብልፅግና ቡድን አገር መምራት እንደማይችል በሁሉም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተል አካባቢያዊም ሆነ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተገነዘበው ሃቅ ሆኗል። የአገዛዙ ጦረኛ እና አውዳሚ ባህሪ በአለም አቀፍ ደረጃ በመታወቁም በእርዳታና በብድር ገንዘብ ለማግኘት ያለው እድሉም የበለጠ እየጠበበበት መጥቷል።ብድር እና እርዳታ የሚያገኝ ከሆነም አገርንና ሕዝብን በዘለቄታው ሊጎዱ የሚችሉ የአበዳሪ አካላትን ፖሊሲ በመቀበል ብቻ እንደሆነ የሰሞኑ እርምጃ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ነገር ግን ይህ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ አይታው የማታውቀው እጅግ ደካማ እና እኩይ የሆነ መንግስት በጎ ስራ ለማከናወን አቅምቢስ ቢሁንም በአገር እና በህዝብ ላይ ጉዳት የማድረስ አቅሙ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ ለአንዳፍታም ቢሆን መናቅና መዘንጋት የለበትም። የበለጠ እድሜ ባገኘ ቁጥር አገርን ሊያፈርስ የሚችል ኃይል ስለሆነ በተቻለ ፍጥነት ከስልጣን መወገድ ያለበት አደገኛ አገዛዝ ነው።
2.2. የአማራ ሕዝብ ወቅታዊ ሁኔታ፤
እንደሚታወቀው አሁን በስልጣን ላይ ያለው ራሱን “ብልፅግና” ብሎ የሚጠራው ኃይል ወደ ስልጣን እንደወጣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በእውነተኛ ይቅርታና እርቅ እፈታለሁ የሚለውን የማታለያ ቃል አምኖ የአማራ ሕዝብ የሞቀ ድጋፍ ሰጥቶት ነበር። ነገር ግን በእርቅና ይቅርታ ፍቅርን አምጥቶ ኢትዮጵያን የሰላም፣ የፍትህና የነፃነት አገር ሊያደርጋት ይችላል ብሎ ተስፋ አሳድሮ ዳር አስከዳር የደገፈው ኃይል በተቃራኒው ቀውስ ፈጣሪ ሆኖ አገኘው። በሂደትም ከአገዛዙ በደረሰበት ሁለንተናዊ ጉዳት በመነሳት አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኃይል የህልውናው አደጋ እና ዋነኛ ጠላቱ እንደሆነ በማያጠራጥር ሁኔታ ተገንዝቧል። ከዚህ በመነሳትም የተደቀነበትን የህልውና ስጋት በመቀልበስ ይህንን ፀረ ሕዝብ ኃይል ታግሎ መጣል እንዳለበት አምኖ ወደ ትግል ገብቷል። ለዚህም የሚያሰፈልገውን መራር መስዋእትነት ሁሉ እየከፈለ ይገኛል። በፋኖ ግንባር ቀደም መሪነት እያካሄደ ያለውን የህልውና ትግል ዳር ለማድረስ እና የአገዛዙን እድሜ ለማሳጠር ቆርጦ ተነስቷል።
ይሁን እንጅ የአማራ ሕዝብ እያካሄደ ያለው ትግል መሰረተ ሰፊና ሁሉን አካባቢ ያካተተ ሆኖ ቢጀመርም አሁንም ያልተሻገራቸው በርካታ ውስንነቶች ያሉበት መሆኑን መገንዘብ ይገባል። መላውን ሕዝብ አደራጅቶ በጠራ የአማራ ብሄርተኝነት ዙሪያ አቀናጅቶ በመምራት በኩል የጎላ ውስንነት ይታያል። በአንድ በኩል ከዚህ ቀደም ብዙ ተሞክሮ የከሸፈውን አማራን በኢትዮጵያዊነት ስሜቱ የማዘናጋት፣ የአማራ ታጋዮችን በሃይማኖት፣ በአካባቢ ወዘተ የመከፋፈሉን ኋላቀር አካሄድ በለሆሳስ በማስገባት ትግሉን የሚያደናቅፍ ጎታች አካሄድ አሁንም አለ። በሌላ በኩል የትግሉ እንቅስቃሴ ከታች ወደላይ ሆኖ ከመጀመሩ ነባራዊ ሁኔታ እና ከፋኖ አመራሮች ልምድ ማነስ ጋር ተያይዞ የዚህ አይነቱ ትግል የሚጠይቀውን ውስብስብ ጉዞ የሚመጥን የተደራጀ ብቁ አመራር የመስጠት ውስንነት ይስተዋላል። ሕዝብን በገጠርም ሆነ በከተማ አደራጅቶ ለትግሉ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ በሰው ሃይል፣ በገንዘብ እና በቁሳቁስ እንዲደግፍ በማድረግ በኩል መሰራት ያለበት የፖለቲካ ስራም በበቂ ሁኔታ ገና አልተሰራም።
በአማራ ትግል ዙሪያ ተዋናይ የሆኑ የፖለቲካዊ ሃይሎች ብዙ እና የተለያየ አላማ ያላቸው በመሆኑ በትግሉ አካሄድ ላይ የራሱን ተፅእኖ መፍጠሩ አልቀረም። በዚህም የተነሳ በሚካሄደው የህልውና ትግል የአማራ ኃይሎች የተለያየ አሰላለፍ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። በአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ተዋናይ የሆኑት ኃይሎች የአማራ ፋኖ (ወጣቶችና አርሶአደሮች የጎላ ሚና የሚጫወቱበት)፣ የአማራ ዲያስፖራ፣ የአማራ ባለሃብቶችና የአማራ ብልፅግና ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ የየራሳቸው ሚና አላቸው። ከነዚህ ውስጥ የሕዝባዊ ትግሉ ዋነኛ ተዋናዮች በአማራ ፋኖ ዙሪያ የተሰባሰበው ወጣቱ ትውልድና አርሶ አደሩ ቢሆኑም ዲያስፖራውና የከተማው ነዋሪ ድጋፍም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይሁንእንጅ በነዚህ የትግሉ ተዋናዮች መካከል ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት ገና አልተፈጠረም።
የፋኖ እንቅስቃሴ ጎልቶ የወጣው ስርአቱ በአማራ ሕዝብ ላይ ከዚህ ቀደም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ጥያቄዎችን ማለትም፦ በማንነቱ ምክንያት በግልም ሆነ በቡድን የሚደርስበት የመብት ረገጣ እንዲቆም፣ በሐብትና ንብረቱ እንዲሁም ወረቱ ላይ የሚፈፀም መዋቅራዊ ቅሚያና ውድመት እንዲወገድ፤ በአማራነት እሴቶችና ትውፊቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ማለትም በቋንቋው፣ በእምነቱና በባህሉ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲቀለበሱ፤ በአገሩ በነጻነት የመንቀሳቀስ እና ሰርቶ የመኖር መብቱ እንዲከበር፤ ለሥነ-ልቦናዊ ግንባታው ፋይዳ ባላቸው የወል ተቋማቱ ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ቆመው ህጋዊ ከለላ አንዲያገኙ እና የወሰን አና የማንነት ጉዳዮች ሕጋዊና ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኙ ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎችን በመመለስ ፈንታ አገዛዙ በሕዝቡ ላይ የከፋ ጥቃት ለመፈፀም እቅድ ይዞ መንቀሳቀስ ከጀመረ በኋላ የተቀጣጠለ ትግል ነው።
ይህም ማለት የፋኖ ትግል የተጀመረው ታስቦበት፣ አንድ ወጥ የሆነ ፕሮግራም ተይዞ፣ የተደራጀ አመራር ኖሮት እና ለትግል የሚያስፈልገውን አቅርቦት አሟልቶ አልነበረም። ፋኖ ወደ ትግል የገባው ስርአቱ ከአማራ ልዩ ሃይል ጀምሮ በሂደት በሁሉም አካባቢ ትጥቅ በማሰፈታት አማራን በሁለንተናዊ መልኩ ለማጥቃት እና ለማስጠቃት በተንቀሳቀሰበት ወቅት ነበር። መንግስት በማን አለብኝነት የጥቃት ዘመቻ በከፈተበት ወቅት እንደ ሕዝብ በየአካባቢው በተፈጠረ ተነሳሽነት እና የእምቢተኝነት መንፈስ ትግሉ በመጀመሩ ንቅናቄው የተማከለ አመራር ሳይፈጥር እንዲቆይ አድርጎታል።
ይህ አይነቱ አካሄድ የኃይል አለመመጣጠንን ግምት ውስጥ በማስገባት ጠላትን በየቦታው እየጠዘጠዙ በማሰልቸትና በማዳከም ባለው ጊዜያዊ ወታደራዊ ፋይዳ ምክንያት በወቅቱ ተመራጭ አካሄድ መስሎ ቢታይም የተማከለ የፖለቲካዊ አመራር ያልነበረው በመሆኑ የራሱ ደካማ ጎኖች ነበሩት። ከሁሉም በላይ የተማከለ አመራር ሳይፈጠር መቆየቱ በፋኖ ኃይሎች መካከል በትግሉ አላማ እና ስትራተጂ ላይ አንድ ወጥ የሆነ ግልፅነትና የአመለካከት አንድነት መፍጠር አለመቻሉ ዋናው ውስንነት ነበር።እንዲሁም ሕዝባዊ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ክህሎት አለመዳበሩ፣ የትግሉን ጉዞ የሚያሳልጥ አደረጃጀት እና የአቅርቦት ስርአት አለመዘርጋቱ የፈጠረው ክፍተት ቀላል አልነበረም። በተጨማሪም የተጠናከረ የክትትል እና የግምገማ ባህል አለመኖሩ ትግሉ በብዙ አይነት ኋላቀር አስተሳሰቦች ማለትም በጎጠኝነት፣ በቡድነኝነት፣ በሕዝበኝነት፣ በስልጣን ፉክክር ወዘተ… በመሳሰሉት ችግሮች ምክንያት ውስጣዊ አንድነት እንዳይኖር ለሚያደርጉ የተለያዩ ተግዳሮቶች ተጋላጭ ሆኖ ቆይቷል።
የአማራ ዲያስፖራ የሕዝቡን ትግል ለመደገፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም አሁንም ትግሉን የሚጎትቱ ውስንነቶች አሉበት። በመጀመሪያ ደረጃ ካለው ቁጥርም ይሁን ለትግሉ ሊያደርገው ከሚችለው የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ፣ የሃሳብ አስተዋፅኦ አኳያ መሆን የሚገባውን ያህል የድርሻውን እየተወጣ ነው ማለት ያስቸግራል። ዲያስፖራው ውስጣዊ አንድነት የሌለው እና በቡድን የተከፋፈለ በመሆኑ በፋኖ የትግል እንቅስቀሴ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳረፉ አልቀረም። በተደራጀ የጋራ ሃሳብ ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በተበታተነ አካሄድ ሁሉም ወደየራሱ የመጎተት እና የመከፋፈል ዝንባሌ ይታይበታል። በእኔ ትዝብት የአማራ ዲያስፖራ ከፍተኛ የሆነ እምቅ አቅም ያለው ቢሆንም በአማራ ሕዝብ የትግል አላማ፣ መዳረሻ ግብ፣ የትግል ስልትና ከሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት ላይ በቂ ግልፀኝነት የለውም። ትግሉ የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ ሆኖ በአለም አቀፍ ደረጃም ጭምር መደመጥ ጀምሮ እያለ ወደ የተወሰኑ ሰዎች ስልጣን መቆጣጠር ደረጃ አሳንሶ የማቅረብ፣ ወዳጅና ጠላትን ያልለየ የትግል ስልትና የኘሮፖጋንዳ አቅጣጫ ጉድለት ይታይበታል። በሰከነ መንገድ ሃይል በሚያሰባስብ አቅጣጫ ትግሉን ከመደገፍ ይልቅ የእርስ በርስ የጎንዮሺ መናቆርን የሚያስፋፋ፣ መሬት ላይ ሕዝቡ እያከሄደው ካለው የትግል መንፈስ ባፈነገጠ መልኩ ጀብደኛ ሆኖ የመታየት እና ሌሎችም ውስንነቶች ያሉበት ስለሆነ ማስተካከል ተገቢ ይመስለኛል።
ሌላው የአማራ ሕዝብ እያደረገ ባለው ትግል እንደ አንድ ኃይል ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ባላሃብቱ ነው። ከሚደርስበት መንግስታዊ አድልዎ እና በደል በመነሳት ለለውጥ የሚደረገውን ትግል ለመደገፍ ፍላጎት ቢኖረውም የመወላወል ባህሪይም ይታይበታል። ይህም ማለት በአንድ በኩል ስርአቱ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ሁለንተናዊ ጥቃት ስለሚያሳስበው የሚደረገውን ትግል በገንዘብና በቁሳቁስ ለመደገፍ ይፈልጋል። በሌላ በኩል አገዛዙ በባለሃብቶች ላይ ምክንያት ፈልጎ በሚወስደው ህገወጥ እርምጃ የመሸማቀቅ፣ እንዲሁም የፋኖ ትግል የተቀዛቀዘ ሲመስለው ከመንግስት ባለስልጣት ጋር በመለማመጥ ጊዜን ለማሳለፍ፣ እድል ከተገኘም ተጠቃሚ ለመሆንና ተመሳስሎ ለመኖር ጥረት ሲያደርግ ይታያል።
በቁጥራቸው ጥቂት ቢሆኑም ከአገዛዙ ተጠግተው ተጠቃሚ ለመሆን ሲሉ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተደረገ ያለውን ጭፍጨፋ በገንዘብና በመረጃ በመደገፍ የወንጀል ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችም እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ የአገዛዙ ተስፈኞች ወገናቸው ከፍተኛ ተጋድሎ በሚያደርግበት በዚህ ወቅት ሃብት ለማካበት ሲሉ ከባለስልጣናት ጋር ተጠግተው መሬት ይሰበስባሉ። ያለውድድር ገበያ ለማግኘት ይሞክራሉ። ተወዳዳሪያቸው የሆኑ ባለሃብቶችንም አስወግደው ገበያውን ለመቆጣጠር ወይም አገዛዙን ለማስደሰት ሲሉ ሰላማዊ የሆኑ ባለሃብቶችን በማስፈራራት ያሸማቅቃሉ። የፋኖ ደጋፊ ናቸው በሚል ለአገዛዙ እየጠቆሙ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋሉ።
በአገዛዙ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ተሰልፈው ያሉ የአማራ ብልፅግና ሰዎች ደግሞ የሕዝቡን ትግል በማደናቀፍ የተሰለፉ ኃይሎች ናቸው። በፌደራል ደረጃ ያሉ የአማራ ተወላጆች የመንግስት ደጋፊዎች እና የአገዛዙ ተልእኮ ዋነኛ ፈፃሚዎችና አስፈፃሚዎች ናቸው። የአማራ ሕዝብ በጅምላ እንዲጨፈጨፍ አብሮ በመወሰን በተግባር የጭፍጨፋው አመራር ሰጭ ሆነው የተሰለፉ ናቸው። በክልል ደረጃ ያሉት የብልፅግና ከፍተኛ አመራሮች በተለይም በአስተባባሪ ደረጃ ያሉት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚካሄደውን ጭፍጨፋ በጋራ አቅደው የሚያስፈፅሙ እና ለጭፍጨፋው የፕሮፖጋንዳ ሺፋን የሚሰጡ ናቸው። ከዚያም አልፈው ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለንፁህ መጠጥ ውሃና ለመንገድ ልማት አገልግሎት ስራ ሊውል ይገባው የነበረን የክልሉን በጀት ለጭፍጨፋው ስራ ማስኬጃ በማዋል ሕዝቡ እንዲጎዳ ሆን ብለው የተሰለፉ እና ከዋነኛዎቹ የአማራ ሕዝብ ጠላቶች ተለይተው የማይታዩ ናቸው።
በሌላ በኩል በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚገኘው መካከለኛና ዝቅተኛ የአመራር አካል በአብዛኛው የሕዝቡ ትግል ደጋፊ ነው። እንደውም አገዛዙ በክልሉ ሕዝብ ላይ ጦርነት ከመክፈቱ በፊት ጀምሮ ይህ የብልፅግና አገዛዝ ፀረ አማራ መሆኑን በየመድረኮቹ አምርሮ ሲያነሳ የነበረ እና ስርአቱን በመታገል ጉልህ ሚና ሲጫወት ነበር። በብልፅግና አመራርም እንደ ጠላት የሚቆጠር እና ከፍተኛ ማሸማቀቅ ሲደረግበት የነበረ ኃይል ነው። የፋኖ ኃይሎች ከተሞችን መቆጣጠር በጀመሩበት ባለፈው አመት የክረምት መጀመሪያ ከፋኖና ከሕዝቡ ጎን ቆሞ የነበረ ኃይል ቢሆንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በአገዛዙ በደረሰበት ከፍተኛ የማሸማቀቅ ስራና ከፋኖ ደጋፊ ሚዲያዎችም በኩል በነበረ የበለው-በለው የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ አንገቱን ደፍቶ በፍርሃት የሚኖር፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚደረጉ የደፈጣ ውጊያዎች ሰለባ ሲሆን የቆየ መዋቅር ነው።በመሃል እየዋለለ በአገዛዙም የማይታመን፣ በሕዝቡም የሚጠላ እና በሚከፍለው መስዋዕትነት ደመ ከልብ እየሆነ ያለ ነው።ነገር ግን በአግባቡ ከተያዘ አብዛኛው ከአማራ ሕዝብ ትግል ጎን በመቆም ጠንካራ የፋኖ ደጋፊ ሆኖ ሊነሳ የሚችል ኃይል ነው።
3. የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል በቀጣይ እንዴት ይመራ?
የአማራ ሕዝብ እያደረገ ያለውን ትግል ከግቡ ለማድረስ በመጀመሪያ ደረጃ የትግሉ ዋነኛ ተዋናይ በሆኑት በፋኖ ኃይሎችም ሆነ በሕዝቡ ውስጣዊ አንድነት ለመፍጠር እንዲሁም ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ሆነ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢውን ድጋፍ ለማግኘት የትግሉን ፖለቲካዊ አላማ፣ ስትራተጂ እና አደረጃጀት በጠራ መንገድ ማስቀመጥ የግድ ይላል። የፖለቲካ አላማና ስትራተጂ በየጊዜው እየዳበረ የሚሄድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የትግሉን መነሻና መዳረሻ፣ ወዳጅና ጠላትን በመለየት ወዳጅን የማጠናከር፣ በአንፃሩ ጠላትን የማዳከም ስልት በጠራ አቅጣጫ ሊመራ ይገባል። ትግሉን ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመምራት የግንባር ቀደም ሃይሎች አደረጃጀትና መዋቅራዊ ሁኔታ በግልፅ ሊታወቅ ይገባዋል። ከሁሉም በላይ ትግሉ በፍጥነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገርና ለአሸናፊነት እንዲበቃ ሕዝቡን በተደራጀ መንገድ ማንቀሳቀስ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የአማራ ሕዝብ ትግልን በተመለከተ የጠራ ፖለቲካዊ አቋም ሊያዝባቸው ይገባል በምላቸው አንዳንድ ነጥቦች ላይ ያለኝን የግል አስተያየት ከዚህ ቀጥሎ ለማቅረብ ልሞክር።
3.1. በአማራ ሕዝብ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ መቀልበስ ቀዳሚው የትግሉ አላማ ስለመሆኑ፤
የአማራ ሕዝብ የሕልውና አደጋ ላይ ነው ሲባል ከፍ ሲል በተደጋጋሚ ከገለፅኳቸው በአማራ ሕዝብ ላይ የተደቀኑ እና በተግባር ባለፉት አስርተ ዓመታት ሲፈፀሙበት የቆዩ፣ አሁንም በመፈፀም ላይ ያሉ እና በቀጣይም ሊፈፀሙ የሚችሉ ጥቃቶችን እና አደጋዎችን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።
በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ የፖለቲካ ኃይሎች በአማራ ሕዝብ ግላዊ እና ቡድናዊ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈፅሙ ቆይተዋል። በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት የመንግሥት መዋቅራዊ ድጋፍ በተቸራቸው ቡድኖች በጅምላ በተፈፀሙ ማንነት ተኮር ጥቃቶች የአማራ ሕዝብ በሕይወቱ፣ በንብረቱ እና በማኅበራዊ እሴቶቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስበት ቆይቷል። አሁንም ቦታና ጊዜ ሳይመርጥ የፀረ-አማራነት ጥቃት ከመቸውም ጊዜ በከፋ መልኩ መንግሥታዊ እና መዋቅራዊ ሆኖ እየተፈፀመ ይገኛል።
የአማራ ሕዝብ ያሉትን ድርብርብ ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲያቀርብ ቢኖርም ላቀረባቸው ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ከመስጠት ይልቅ የብልፅግና አገዛዝ በኃይል ለማንበርከክና ለመጨፍለቅ የአገሪቱን ጦር በሙሉ አዝምቶ እየጨፈጨፈው ይገኛል። ባለፈው አንድ አመት በአማራ ሕዝብ ላይ በተከፈተው ሁሉን አቀፍ ጦርነት የብልፅግና ሥርዓትን ፀረ-ሕዝብነትና አረመኔነት በግልፅ ያሳዩ ጥቃቶች ተፈፅመዋል። የብልፅግና ሥርዓት አለኝ የሚለውን ወታደራዊ አቅም በምድርና በአየር አሰማርቶ ሴት፣ ወንድ፣ ሕፃንና ሽማግሌ ሳይል በጅምላ ጨፍጭፏል፤ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፤ የሕዝቡን ሁለንተናዊ እንቅስቀሴ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥም በመገደብ እና ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም በትግራይ ለሁለት አመታት ሲያደርግ እንደታየው ሁሉ ክልሉን የምድር ሲኦል እያደረገው ይገኛል። ይህም በመሆኑ በጠቅላላ በአገሪቱ በእጅጉ የናረው የኑሮ ውድነት፣ መፈናቀልና ድርቅ ከጦርነት ጋር ተደምረው የሕዝቡን መከራ እና ስቃይ እያበዙት መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው።
ነገር ግን የብልፅግናው አገዛዝ የአማራን ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በኃይል ጨፍልቆ ዝም ለማሰኘት እና አማራን በሁሉም መስክ ለማዳከም ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ቢረባረብም የሕዝቡን ቁጣ ይበልጥ እያባባሰው እና ከአገዛዙ ጋር ያለው የመረረ ጠላትነት ስር እንዲሰድ ከማድረግ ውጭ የሚያመጣው ለውጥ አለመኖሩን የእስካሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ አረጋግጧል።
ከዚህ አንፃር የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ቀዳሚ መነሻም ሆነ መዳረሻ አላማው በአማራነት ዙሪያ ተደራጅቶ ብሄራዊ ህልውናውን ለማረጋገጥ መሆን አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ የጠራ መስመር ሳይዙ በተድበሰበሰ ፖለቲካዊ መንገድ ለመምራት መሞከር ሕዝቡን ከማደናበርና ለከፋ ጥቃት ከማጋለጥ ውጭ ሌላ ፋይዳ እንደሌለው በተግባር የታየ ጉዳይ ነው። የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል አልፋና ኦሜጋ በአማራነት ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ መቀልበስና ዘለቄታ ያለው እፎይታ የሚያገኝበትን ስርአት እውን ማድረግ ነው።
የአማራ ህዝብ ትግል የሚያነጣጥረው የህልውና አደጋ በደቀኑበት አገዛዞች ላይ እንጅ የሌሎች ሕዝቦችን መብት እና ጥቅም ለመጋፋት አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ስርአት እንጅ መብቴን ተጋፍቶኛል ብሎ የሚታገለው ሕዝብም የለም። ይልቁንም ሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያየ መልኩ የሚገለፅ በደል የደረሰበት መሆኑን ይገነዘባል። እንዲህ አይነቱ እሳቤው ከሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ህብረትን ፈጥሮ አብሮ ለመታገልና የህልውና ትግሉን ዳር ለማድረስ የላቀ ፋይዳ እንዳለው በፅኑ ያምናል። ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በአማራ ሕዝብ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በክልሉ ውስጥ የሚካሄደው ትግል ወሳኝ መስሎ ይታየኛል።በእኔ እይታ በክልሉ ውስጥ የሚካሄደውን የህልውና ትግል ወደ ላቀ ደረጃ በፍጥነት ለማሸጋገር እና የአገዛዙን እድሜ ለማሳጠር የሚከተሉትን ተግባራት በቅደም ተከተል ማከናወን አስፈላጊ ይመስለኛል።
የመጀመሪያው አማራ ክልልን ሙሉ ለሙሉ ከአገዛዙ ቁጥጥር ውጭ (Ungovernable) እንዲሆን ማድረግ እንደ አንድ ቀዳሚ ስኬት ተደርጎ ሊታይ ይገባል። አገዛዙ አማራ ክልልን ማስተዳደር እንዳይችል ማድረግ፣ በሁሉም የገጠር አካባቢዎች የአገዛዙን የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር የእዝ ሰንሰለት መበጣጠስ ቀዳሚ ተግባር ነው። እስከአሁን በተደረገው እንቅስቃሴ የአገዛዙን መዋቅር የእዝ ሰንሰለትን የመበጣጠስ እና ከታችኛው መዋቅሩ ጋር እንደፈለገ እየተገናኘ የፈለገውን ማስፈፀም እንዳይችል የማድረጉ ስራ በብዙ አካባቢዎች በተለይም በሚበዙት የገጠር ቀበሌዎች በተሳካ ሁኔታ እየተፈፀመ ይገኛል።ይህ በቀሪዎቹ የገጠር ቀበሌዎችም በፍጥነት መሰራት ያለበት ነው። ከዚህ አኳያ በፋኖ መሪነት እስከ አሁን በተካሄደው ትግል በአብዛኛዎቹ የክልሉ የገጠር አካባቢዎች አገዛዙ ከታችኛው የወረዳና የቀበሌ የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅሩ ጋር እንደፈለገ መገናኘት እንዳይችል ተደርጓል።ነገር ግን የእዝ ሰንሰለቱ ተበጣጠሰ ማለት መዋቅሩ ከነጭራሹ ፈርሷል ማለት አይደልም።ከከተሞቹ እየተነሳ መልሶ ለማደራጀት እና የተበጣጠሰውን መዋቅር ለመቀጣጠል ጥረት ማድረጉ አልቀረም።በቀጣይ ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ በክልሉ ከተሞች አገዛዙ እንደፈለገ እያዘዘ የጥፋት መሳሪያ አድርጎ የሚጠቀምበት የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር ሊኖረው አይገባም።ከተሞች ከአገዛዙ ቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይገባል። ይህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሳይቆይ መከናወን አለበት። ምክንያቱም ጠላት አንደፈለገ እየተንቀሳቀሰና ከዚያም እየተነሳ የገጠሩን አካባቢ የሚያጎሳቁልበት እድል ሊሰጠው አይገባም። ሙሉ በሙሉ ከክልሉ ተጠራርጎ እስከሚወጣም ቢሆን ተሸማቆ እንጅ እንደፈለገ እየፈነጨ ለመኖር ሊፈቀድለት አይገባም።
ሁለተኛው ምዕራፍ፣ የብልፅግና አገዛዝ መዋቅር እርስ በራሱ እንዳይገናኝ የማደረጉ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ አገዛዙ ምንም አይነት ድጋፍ በአማራ ክልል ውስጥ እንዳያገኝ ማድረግ በትኩረት መከናዎን አለበት።ብልፅግና የሕዝቡን ትግል ለማፈን የሚገለገልበትን መዋቅር ከዚህ የጥፋት ሃይል በፍጥነት መንጠቅ እና ከታችኛው እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ ከስር እየነቀሉ የመጣል አቅጣጫን ተከትሎ መስራት የወቅቱ ትግል የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በክልሉ ያለው የፖለቲካም ሆነ የፀጥታ መዋቅር ከብልፅግና ቡድን ጋር በፍላጎትም ሆነ በተግባር የሚያስተሳስር ምክንያት የላቸውም። የታችኛው መዋቅር ከብልፅግና አገዛዝ ጉዳት እንጅ የሚያገኘው ጥቅምም የለውም። ሰላሙን አጥቷል። ስርአቱ በወለዳቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጠቂ እንጅ እንደ ላይኛው የፖለቲካና የፀጥታ አመራር ተጠቃሚ አይደለም። ይልቁንም ለሕዝቡ የቀረበ አመለካከት ያለው በመሆኑ በአገዛዙ እንደጠላት ይቆጠራል። ሆን ተብሎ ከሕዝቡ ጋር እንዲጋጭም እየተደረገ በመሆኑ ከዚህ አገዛዝ የሚላቀቅበትን ጊዜ እየናፈቀ ያለ ኃይል ነው። ስለሆነም ቶሎ ብሎ በአንድ በኩል ከአገዛዙ አገልጋይነት እንዲላቀቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሕዝባዊ ትግሉ አጋዠ ሆኖ እንዲያገለግል አሰልጥኖ ማሰማራት ያስፈልጋል። ይህ ከታችኛው የቀበሌና የወረዳ መዋቅር ጀምሮ በሂደት የዞንና የክልል የብልፅግና መዋቅርን በማፈራረስ የብልፅግና ፀረ ሕዝብ ቡድን በክልሉ ምንም አይነት ሕዝባዊም ሆነ መዋቅራዊ ድጋፍ እንዳያገኝ እና እንዲነቀል መደረግ አለበት። ይህንን ሁኔታ መሰረት በማድረግ ክልሉን ከአገዛዙ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማውጣት ተገቢ ነው። ክልሉ ከአገዛዙ ሙለ በሙሉ ነፃ ካልዎጣ በስተቀር አሁን ባለበት ማንም የማያስተዳድረው ሆኖ መቆየት ለጊዜው እንደ ድል የሚታይ ቢመስልም በሂደት ጎጅ ሊሆን ይችላል።አንድም ጠላት አቅሙን አጠናክሮ ትግሉ እንዲጓተት ሊያደርገው ይችላል፣ ወይም በክልሉ ስርአተ አልበኝነት እንዲስፋፋ በር የሚከፍት ይሆናል። በአማራ ክልል ውስጥ የብልፅግና መዋቅርን ማፍረስ ሲባል በዚህ ፀረ ሕዝብ ቡድን የተሰራጩ ለአገር ጠንቅ የሆኑ እሳቤዎችን ጭምር ነቅሎ መጣል እና በአዲስ አስተሳሰብ መተካትንም መጨመር ይኖርበታል። ይህን ለማድረግም ከወታደራዊው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የተጠናከረ የፖለቲካ ስራ በልዩ ትኩረት መከናወን አለበት።
በመቀጠልም ወደ ሶስተኛው ምእራፍ በመሸጋገር በተነቀለው የብልፅግና መዋቅር ምትክ በፍጥነት ሕዝብን ማደራጀትና ለትግሉ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ጠንካራ መዋቅር መፍጠር፣ መገንባትና ስምሪት ውስጥ አስገብቶ ማንቀሳቀስ ይገባል። ይህን መዋቅር አማራ ክልልን ከጠላት ነፃ ለማውጣት ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሀይሎች ጋር ተባብሮ አረመኔውን የብልፅግና ቡድን ሙሉ በሙሉ በአገር ደረጃ ከስልጣን ለማስወገድ እንደ አንድ ቁልፍ የቅድመ ዝግጅት ስራ ተደርጎም ሊታይም የሚገባው ነው።ሶስቱንም ምእራፎች ማለትም የአገዛዙን የእዝ ሰንሰለት መበጣጠስ፣ መዋቅሩን መንጠቅና የሕዝባዊ ትግሉን የሚደግፍ አዲስ መዋቅር የመትከል ስራን በተሳካ ሁኔታ ለማከናዎን የአቅም ግንባታ ጉዳይ ቁልፍ ነው።የፋኖ አመራሮችም ይሁን ሌሎች ትግሉን እንደግፋለን የሚሉ ኃይሎች ሊገነዘቡት የሚገባው ጉዳይ በሁሉም ደረጃ የወታደራዊም ሆነ የፖለቲካ አመራር አቅም መገንባት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ነው።ቀጣዩ ተልኮ ይበልጥ ውስብስብ እና ከባድ በመሆኑ ለዚያ የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ ለነገ የሚባል አይደለም።
3.2. ሁሉን አቀፍ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ መንግስታዊ ስርአት መገንባት የህልውና ትግሉ ቁልፍ አጀንዳ ስለመሆኑ፤
ኢትዮጵያ አገራችን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የመንግስትነት ታሪክ ባለቤት ብትሆንም ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ልማትን ማስፋፋት እና ዲሞክራሲያዊ የሆነ አስተዳደርን ማስፈን ተስኗት አሁንም በቀውስ ውስጥ እየማሰነች ትገኛለች። ለዚህ ዋናው ምክንያት ሁሉን አቀፍ የሆነ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት ባለቤት መሆን አለመቻሏ ነው። ሕዝባዊ እና ዲሞክራሲያዊ መንግስት ሲባልም በመጀመሪያ ደረጃ የሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተሳትፎ በንቃት እና በነፃነት ባረጋገጠ አኳኋን በምርጫ ይሁንታ የተሰጠው፣ በሕዝብ ይሁንታ ስልጣን መያዝ ብቻም ሳይሆን የያዘውን ስልጣን ተጠቅሞ ለሕዝብ እና ለአገር በጎ የሚሰራ፣ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የሚያረጋግጥ፣ የህግ የበላይነት የሚያሰፍን፣ እንዲሁም ልማትን የሚያፋጥን ስርአት ዘርግቶ ተግባራዊ አመራር የሚሰጥ፣ በቀጥታም ሆነ በወኪሎቹ በኩል በሕዝብ ቁጥጥር የሚደረግበት እና ሕዝብ ሳይፈልገው ሲቀር የሚቀየር መንግስታዊ ስርአት ማለት ነው።
ከዚህ አኳያ የአማራ ሕዝብ አሁን እያደረገ ያለው የህልውና ትግል እና ለዚህም እየከፈለ ያለው መራር መስዋእትነት በአገሪቱ ሁሉን አቀፍ ሕዝባዊ እና ዲሞክራሲያዊ መንግስታዊ ስርአት እንዲገነባ የራሱን ድርሻ ለመወጣት እንጅ አዲስ ተረኛ አምባገነኖችን ወደ ስልጣን ለማውጣት አለመሆኑን ማስመር ይገባል። ይህ አይነቱ ስርአት በኢትዮዽያ ሲገነባ ነው የአማራ ህዝብ ህልውና ዋስትና የሚኖረው እና ዘለቄታዊ በሆነ ሁኔታ መብት እና ጥቅሙን ማረጋገጥ የሚችለው። ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ መብት መከበር እውቅና የሚሰጥ፣ ለግለሰቦች ነፃነትና እኩልነት ዘብ መቆም የሚችል ስርአት እውን ሲሆን ነው የጋራ ህልውናችንም ሆነ ጥቅማችን ሊከበር የሚችለው። ይህ አይነቱ መንግስታዊ ስርአት ግን ስለተፈለገ ብቻ በድንገት እውን ሊሆን አይችልም። አሁን ዋናውና ቀዳሚው ትኩረት የኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት የሆነውን የብልፅግና ቡድንን ተባብሮ ከስልጣን ማስወገድ መሆን አለበት። በሂደትም ወደ ዘላቂ ሕዝባዊ እና ዲሞክራሲያዊ ወደሆነ የሃገረ መንግስት ግንባታ ለመሸጋገር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል አካታች ጊዜያዊ የሺግግር መንግስት ማቋቋም እንደ አስፈላጊነቱ የሚታይ ይሆናል።
በዋናነት የአማራ ሕዝብ ዘላቂ ድል ተደርጎ ሊታይ የሚገባው የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ጉልበትን አድርጎ የቆየውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ባህል በመቀየር የስልጣን ምንጭ የሕዝብ የምርጫ ድምፅ የሚሆንበትን ሁኔታ የሚፈጥር ስርአት መትከል ነው። የአማራ ሕዝብ ትግል ስኬታማ ተደርጎ ሊታይ የሚችለውም ከእንግዲህ ወዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው የፖለቲካ ሃይሎች በብቃት በሚወዳደሩበት እና ሕዝብ በንቃት በሚሳተፍበት ምርጫ አሸናፊ በመሆን ብቻ እንዲሆን ማድረግ ሲቻል ነው። ይህም ዘለቄታ ይኖረው ዘንድ የተለያዩ የዲሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባትን ታሳቢ ያደረጉ እርምጃዎችን መውሰድ የግድ የሚል ይሆናል። ይህንን ስኬታማ ለማድረግ ከአገሪቱ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ተደራድሮ አገራዊ ህብረትን እና መግባባትን መፍጠር ያስፈልጋል።
የአማራ ሕዝብ በአገር ደረጃ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች እና ፖለቲካዊ ኃይሎች ጋር ህብረት የሚፈጥረውም ሆነ ተደራድሮ በኢትዮጵያ አካታች ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሰረት የሚያደርገው የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ፣ መብቱንና ዘላቂ ጥቅሙን ለማስከበር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ስለሆነ ነው። በሌላ አነጋገር የአማራ ሕዝብ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን የሚፈልጋት ከዚህ ቀደም ስለ እናት አገሩ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍለት በነበረው የታሪክ አውድ ላይ ተመስርቶ ብቻ ሳይሆን እንደ ሕዝብ በተጨባጭ ሕልውናውን ለማስከበር፣ ዘላቂ መብቱን እና ጥቅሙን ለማስጠበቅ ባለው ተጨባጭ ፋይዳ ላይ ተመስርቶ መሆን አለበት ማለት ነው። በተመሳሳይ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ህብረት ሊፈጥሩ የሚችሉት ለማንም ብለው ሳይሆን ለራሳቸው እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስርአት በአገሪቱ እውን ለማድረግ ፈልገውና አምነው መሆኑን ማስመር ተገቢ ነው።
3.3. አማራን እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ በብቃት ማንቀሳቀስ ለህልውና ትግሉ ወሳኝ ስለመሆኑ፤
የአማራ ሕዝብ በብዛት፣ በኢኮኖሚ ድርሻ፣ በተማረ የሰው ሃይል፣ በመልክአምድራዊ አቀማመጥና በባህል ረገድ በአገሪቱ ከፍተኛ ሚና መጫወት የሚያስችል አቅም ያለው ሕዝብ ሆኖ ሳለ ለምን ለጥቃት ተጋላጭ ሆነ የሚለው ጉዳይ በአግባቡ መታየት አለበት። የአማራ ሕዝብ በሚወዳት አገሩ ጉልበቱን፣ እውቀቱንና ገንዘቡን ተጠቅሞ ሰርቶ ለመኖር እንዳይችል ለምን መከራው በዛበት ብሎ በጥልቀት መጠየቅ የአማራውን ትግል ወደ ፊት ለማራመድ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ ሁሉ በደል ሲደርስበትስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በውስጥም ሆነ በውጭ ለምን ጩኸቱ ሰሚ አጥቶ ቆየ የሚለው ጉዳይም መመርመር አለበት።
እንደ እኔ አስተያየት ምክንያቱ በጥልቀት መታየት ያለበት ሆኖ ለመነሻ ያህል ችግሩን በጥቅሉ ውስጣዊና ውጫዊ ብሎ መመልከቱ ተገቢ ነው። ለጊዜው ውጫዊውን ምክንያት ብዙ ስለሚባልለት ወደ ጎን ትተነው ውስጣዊውን ምክንያት ለማየት እንሞክር። የአማራ ሕዝብ ይህ ሁሉ ጥቃት ሊደርስበት የቻለው በዋናነት እንደ አንድ ሕዝብ ውስጣዊ አንድነት ስለሌለው ነው። የአማራ ሕዝብ ብሄራዊ አንድነቱን ለማጠናከር መተኪያ የሌላቸውን የሕዝቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ ለዘመናት የገነባቸውን እሴቶቹን መሰረት ያደረገ በአማራነት ዙሪያ የተሰባሰበ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተሰራው ስራ እጅግ አናሳ በመሆኑ ነው። በተለይም ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መድረክ በዋናነት የሚዘወረው ብሄርን ማእከል አድርገው በተደራጁና ግልፅ የሆነ አላማ ባላቸው ብሄርተኛ የፖለቲካ ሃይሎች በሆነበት ተጨባጭ ሁኔታ አማራ ጠንካራ ብሄራዊ ህብረት ፈጥሮ አለመንቀሳቀሱ ለአሁኑ በማንነት ላይ የተመሰረተውን ጥቃት በተደራጀ መንገድ ለመመከት አለመቻሉ አንዱ ምክንያት ነው። የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር በወሳኝ መልኩ በብሄርተኝነት ዙሪያ የሚዘወር በሆነበት ሁኔታ ሳይደራጁ ተበትኖ መገኘት እንደ ጠባጫሪ ተቆጥሮ አማራው ለጉዳት ተዳርጎ ቆይቷል። ምንም እንኳን በተለያየ ወቅት በአማራ ማንነት ዙሪያ ብሄር ተኮር አላማ ያላቸው ድርጅቶች ተመስርተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቢሆንም በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ብዙውን ጊዜ አማራው በተለይም ልሂቃኑ በአማራነት መደራጀትን እንደ ማነስና ከኢትዮጵያዊነት ማማ እንደመውረድ አድርጎ ሲመለከት የቆየ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአማራነት ስም መሰባሰብ ሲሞክርም ትግሉን የሚያካሂደው የጠራ ፖለቲካዊ መስመር ሳይዝ እና አላማውን በተደራጀ ሁኔታ ሳይቀምር በተበጣጠሰ መንገድ እየተጓዘ በመቆየቱ እና ሕዝቡንም ግራ እያጋባ የኖረ በመሆኑ ነው። የራሱን ፍላጎት ቀምሮ እና በዚያ ዙሪያ ተሰባስቦ ተጠናክሮ መውጣት ሳይችል ሲቀር እራሱን ከመፈተሽ ይልቅ ለውስጣዊ ድክመቶቹ ውጫዊ ምክንያት እየደረደረ ስለኖረ ነው። በተራማጅ ሃሳቦች ዙሪያ ተደራጅቶ ወዳጅን በማብዛት ላይ ከማተኰር ይልቅ ከሁሉም ጋር የሚያጣላ ተንኳሺና ሁሉን አነዋሪ የሆነ የብሺሺቆሺ ፖለቲካን የሚያራምድ በመሆኑ ነው። ይህ የአማራ ልሂቃን የፖለቲካ ዘይቤ ወደ ህብረተሰቡም ዘልቆ በመግባቱ የተደራጀ ሃይል ሆኖ ራሱን ለመከላከልም ሆነ ወደፊት መራመድ ለመቻል እንቅፋት ሲሆንበት ቆይቷል።
በአማራ ማንነት ላይ ተነጣጥሮ በጠላቶቹ እየተወሰደበት ያለን ጥቃት የህዝቡን ብሄራዊ አንድነት አጠናክሮ ለመመከት ከመስራት ይልቅ ከጠላት ጎን ተሰልፎ አማራን ማጥቃት፣ በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን የህልውና አደጋ አሳንሶ የማቅረብ፣ ወይም ማንነትን መሰረት አድርጎ በህዝብ እና ተቋማት ላይ የሚደርስን ጥቃት ዝም ብሎ የሚመለከት አማራ ሊኖር የቻለበት ምክንያት የአማራ ብሄርተኝነትን በጠራና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማጠናከር መሰራት ያለባቸው ስራዎች ብዙ የሚቀራቸው በመሆናቸው ነው።የሚካሄደውን ትግል በድል አድራጊነት ለመቋጨት አማራነትን እንደ ዋነኛ መደራጃ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም የግድ ይላል። ከዚህ ውጭ ከአማራነት ያፈነገጠ ወይም አማራነትን የሚያደበዝዝ የፖለቲካ እንቅስቀሴ የአማራን ስቃይ ከማስቀጠል በዘለለ የሚያመጣው ፋይዳ የለም። ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው በኢትዮዽያ ህልውና መከበር የሚገኘውን የጋራ ጥቅም ጥያቄ ውስጥ ሳያስገቡ የአማራ ብሄርተኝነትን አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል የሚል አስተያየት አለኝ።
የአማራን ህዝብ እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ እንዲቆም ማድረግ በጠንካራ ፖለቲካዊ አመራር እና ድርጅት ተሰርቶ የሚመጣ እንጅ ስለተፈለገ ብቻ ዝም ብሎ የሚመጣ ወይም በምኞት ብቻ የሚፈጠር አቅም አይደለም። ስለሆነም አማራ ህልውናውን ለመጠበቅ፣ ዘላቂ መብትና ጥቅሙን ለማስከበርም ሆነ በአገር ደረጃ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት በጠራ አላማ ዙሪያ የተሰባሰበ የአማራን ሕዝብ አደራጅቶ የሚያንቀሳቅስ ቁርጠኛ አመራር ያስፈልገዋል። የአማራ ብሄርተኝነትን በመሳሪያነት በመጠቀም በአማራ ማህበረሰብ ውስጥ የሚታዩ ጎታች የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በማረም የአማራን ትንሳኤ እውን ሊያደርግ በሚያስችል አዲስና ተራማጅ የፖለቲካ እሳቤ የሚመራ የተደራጀ ጠንካራ አመራር መኖር የግድ ይላል። አማራን እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ አደራጅቶ በህልውናው ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስም ሆነ ዘለቄታዊ የሆነ ሰላም ሊያስገኝለት የሚችለውን ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት በአገሪቱ ለመትከል በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌላው የኢትዮጵያ ክፍልና በውጭ አገር ጭምር የሚገኘውን ሕዝብ ግምት ያስገባ የአማራ ህብረት ሊኖር ይገባል።
3.4. ከሌሎች የኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር መተባበር ለህልውና ትግሉ መቀላጠፍ እና መሳካት ወሳኝ ስለመሆኑ፤
በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ ባለው የብልፅግና አገዛዝ ህልውናው ፈተና ውስጥ ያልገባ ሕዝብ በአገሪቱ አለ ለማለት ያስቸግራል። በሌላ አገላለፅ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኃይል የሁሉም ሕዝቦች ጠላት በመሆኑ ይህ የህልውና ትግል በአጭር ጊዜ እና በድል አድራጊነት እንዲቋጭ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር መተባበር አለበት። ትብብሩ የተለያየ መልክ እና ደረጃ ሊኖረው ቢችልም የመተባበር መርህ ግን እንደ አንድ የፖለቲካ አላማ ተይዞ ሊሰራበት ይገባል። የትብብሩ ደረጃ በአጠቃላይ የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አላማ ተጋሪነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል ወይም በመሰረታዊ አላማ ላይ ልዩነት ቢኖርም አሁን አገሪቱ ከገባችበት ቅርቃር ለማውጣት በሚያስችሉ መሰረታዊ የጋራ የህልውና ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል።
የአማራ ሕዝብ አሁን ያለውን ፀረ ሕዝብ አገዛዝ ለማስወገድ የሚያካሂደው ትግል ከሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር መተባበር ይኖርበታል ሲባል የአገዛዙን እድሜ ለማሳጠር እና በአማራ ሕዝብ ላይ የተደቀነው ብሄራዊ የህልውና ስጋት እንዲቀረፍ ባለው ፋይዳ ብቻ አይደለም። ይልቁንም አገራችን የብዙ የተለያየ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች አገር በመሆኗ ዘላቂ ሰላም እና ለዜጎች ዋስትና የሚሰጥ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እውን ለማድረግ የሁሉንም ሕዝቦች ይሁንታ ማግኘት የግድ የሚል ስለሆነም ጭምር ነው። በመሆኑም እየተካሄደ ያለው የህልውና ትግል እንዲቀላጠፍ እና ስኬታማ ሆኖ ለሁሉም የሚመች ሃገረ መንግስት ለመገንባት ከሌሎች ፖለቲካዊ ኃይሎችም ሆነ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጎልበት ያስፈልጋል። ይህ መደጋገፍ ከወዲሁ ተጀምሮ በትግሉ ሂደት እየጎለበተ ሲሄድ በውጤቱም የአማራ የህልውና ትግል ለአማራ ትንሳኤ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ህዳሴ እና ህልውናም ትልቅ አጋዥ ኃይል የመሆን እድል ይኖረዋል።
ስለሆነም የወቅቱ የአማራ ሕዝብ ትግል ከሌሎች በአገሪቱ ካሉ ሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ሀይሎች ትግል ጋር በአግባቡ መናበብና መቀናጀት ይኖርበታል። በተለይም አገዛዙ ዋና የትግል ማዳከሚያ መሳሪያ አድርጐ እየተጠቀመበት ያለው የአማራን ሕዝብ ከወንድሙ ከትግራይ ሕዝብ ጋር በዘላቂነት እያጋጨና እያዋጋ በስልጣን ላይ መቀጠል ስለሆነ ይህን ሴራ በጋራ ትብብር ማክሸፍ አስፈላጊ ይሆናል። አፋርን፣ ኦሮሚያን እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ከመሰሉ የጐረቤት ክልል ሕዝቦች ጋርም የትግል ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ነው። በሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫ ያሉ ሕዝቦች የትግል ትኩረት አራት ኪሎ በተቀመጠው ሕዝብ ጨፍጫፊ አገዛዝ ላይ መሆን አለበት እንጅ በፍፁም የጐንዮሽ እና የእርስ በርስ መሆን የለበትም።አገዛዙ እየተዳከመ ሲሄድ እና ራሱ ሆን ብሎ የፈጠራቸውን ፖለቲካዊ ቀውሶች በወታደራዊ ሃይል መቆጣጠር ሳይችል ሲቀር ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት ወደ ኋላ አይልም። በተግባርም የብልፅግናው አገዛዝ የሕዝብ ጫና ሲበረታበት ወደ ብሄርና ሃይማኖት ግጭት ለማስገባት ሲሞከር እንደነበር የምናስታውሰው አውነታ ነው።የተለያዩ ኃይሎች እና ሕዝቦች መተባበር አለባቸው ሲባል አንዱ ምክንያት ይህንን አይነቱን ሃላፊነት የጎደለው የአገዛዙን እኩይ ሃሳብ እና ፀረ ሕዝብ ተግባር ለማክሸፍም ጭምር ነው።
3.5. የአማራ የህልውና ትግል በጎረቤት አገሮች እና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ስለማድረግ፤
የአማራ ሕዝብ በህልውናው ላይ የተደቀነውን የጥቃት አደጋ ለመቀልበስና ፍትሃዊ ለሆነ ስርአት ግንባታ እያደረገ ያለው ትግል ከአህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ከሆኑ ኃይሎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል። አሁን የሚታየውን ያልተጠና እና በግብታዊነት ላይ የተመሰረተ፣ ችግርን ከውጭ ወደ ውስጥ የሚመለከተውን እይታ በማስተካከል አማራን እንደ ብሄር፣ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለቀውስ ተጋላጭ እንድትሆን ያደረጋትን ውስጣዊ ችግር በማስገንዘብ እና እንዲሁም ይህ የኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግር ካልተፈታ በአካባቢው እና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረውን አሉታዊ እንደምታ በማስገንዘብ ከራሳቸው ጥቅም አንፃር እንዲመለከቱት ማድረግ ያስፈልጋል።
በተለይም አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት በአገር ውስጥ በሚፈጥረው ቀውስ በቀጠናው ጭምር ተፅእኖ ከማሳረፉም በተጨማሪ በጎረቤት አገሮች የውሰጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ነው። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ታሪካዊ እሴት በሚፃረር መልኩ እና ካለፉት መንግስታት የፖለቲካ ልምድም ባፈነገጠ አግባብ ኢትዮጵያን የመሰለ ታላቅ አገር አዋርዶ በአዲስ መልክ የከባቢው አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን ለሚጥሩ ኃይሎች ጉዳይ አስፈፃሚ በመሆን አገዛዙ እያገለገለ እንደሆነ ማሳየት ያስፈልጋል። አገራችን በምትገኝበት ቀጠና ኃያላን አገራት በከባቢው የየራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚራኮቱበት ሁኔታ ስለአለ ይህንን ሁኔታ ለትግሉ እንዴት እንደምንጠቀመበት በጥናት ላይ የተመሰረተ አካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ሁኔታውን የአገርን ብሄራዊ ጥቅም ሳይጎዱ ለመጠቀም ግልፅ አቅጣጫ ይዞ መስራት ያስፈልጋል።
ከዚህ አኳያ በቅድሚያ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ማጐልበት ያስፈልጋል። ከጎረቤት አገሮች ጋር ከወዲሁ ጀምሮ በመከባበር ላይ የተመሰረተ መልካም ጉርብትና እና ወዳጅነት ለማዳበር እንዲሁም እየተደረገ ያለውን ትግል በሚችሉት መንገድ እንዲደግፉት ከየሃገራቱ መንግስታት እና ሕዝብ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ማጎልበትን ያለመ ስትራተጂ መተለም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ለዋና ዋና አለምአቀፋዊ እና ቀጠናዊ አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት ወዳጅነታቸውን ለማትረፍ አቅማችንን ግምት ውስጥ ያስገባ ጠንካራ ዲፕሎማሲ እንዴት ልንሰራ እንችላለን? የሚሉ ጥያቄዎችን በተጠና መንገድ በዝርዝር መመለስ ተገቢ ይሆናል። በተለይም አገዛዙን ሰላም ወዳድ፣ ተቃዋሚውን (ፋኖን) ደግሞ ጦረኛ አድርጐ ከሚያሳይ ማናቸውም የተሳሳተ አቀራረብ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
3.6. የህልውና ትግሉ ዋነኛ ስልት በትጥቅ ትግል የተደገፈ ሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መሆን የሚገባው ስለመሆኑ፤
የአማራ ሕዝብን የሕልውና ትግል በአጭር ጊዜ ውጤታማ ሊያደርገው የሚችለውን ስልት ለይቶ በማወቅ የወገንን ኃይል ግንዛቤ ማሳደግ፣ አመለካከቱን በትክክለኛ መንገድ ማነፅ፣ የአደረጃጀት ስርአቱን አጥርቶ መዘርጋት፣ ለትግሉ በሚጠቅም አቅጣጫ ስምሪት መስጠትና በተልዕኮ ላይ በመመስረት ማብቃት ያስፈልጋል። እንዲሁም አሁን የሚካሄደው ትግል የሚመራበትን አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግም ተገቢ ነው።
በአማራ ፋኖ የተለያዩ አደረጃጀቶች እየተመራ ያለው ሕዝባዊ ንቅናቄ ዋነኛ የትግል ስልቱ በትጥቅ የታገዘ ሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መሆን የሚገባው ቢሆንም አሁን አሁን ጎልቶ እየወጣ ያለው ግን የትጥቅ ትግሉ ብቻ ሆኗል። ይህ ሲባል የትጥቅ ትግሉ አሁን ካለበት በላይ መጠናከር ያለበት መሆኑን በመዘንጋት አይደለም። ይልቁንም መድረስ ባለበት ደረጃ ካለመድረሱም በላይ የትጥቅ ትግሉ በአመለካከት፣ በወታደራዊ ክህሎት፣ በአደረጃጀት፣ በአሰራርና በአቅርቦት ረገድ ብዙ የሚጎለው ጉዳይ መኖሩ ሃቅ ነው። እንደውም አንድ ትጥቅ የያዘ የነፃነት ኃይል በፖለቲካዊ አላማና ግብ በሚገባ ካልታነፀ አደገኛ ውጤትም ሊኖረውም ይችላል።ነገር ግን የትግሉን ጊዜ በማሳጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት የሚገባውና በሕዝባዊ እምቢተኝነት ሊገለፅ የሚችለው ትግል ያለ አግባብ ወደ ጐን ተገፍቷል። መጀመሪያ አካባቢ የከተሞቹ ሕዝብ ሰላማዊ እምቢተኛነት እየተጋጋለ መጥቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በአመራር ጉድለትና በጠላት የአፈና እንቅስቃሴ መጠናከር ምክኒያት የመፋዘዝና ጭራሹኑም የመዳፈን አደጋ ገጥሞታል።
በተለይም በወረዳና ከዚያ በላይ ባሉ ከተሞች ለሕዝባዊ እምቢተኝነት የተመቸ ሁኔታ ቢኖርም ይህንን የሚመራ አደረጃጀት ባለመኖሩ ከተሞች የትግሉ ዋና አካል መሆናቸው ቀርቶ የአማራ ጠላቶች መሸሸጊያና መመሸጊያ ሲሆኑ እየታየ ነው። ስለሆነም የከተማው ሕዝብ በአሁኑ ወቅት በኑሮ ውድነት የሲኦል ኑሮ እየገፋ ባለበት፣ ከቦታ ቦታ ሰውም ሆነ ሸቀጥ በማይንቀሰቀስበት፣ በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ በሆነበት፤ የተለየ ሐሳብ ሊኖራቸው ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ወገኖቻችን በገፍ እሰር ቤት ተወርውረው የአገዛዙ ግፍ እየተፈፀመባቸው ባለበት፣ የመንግሥት መዋቅሩ ደምብዦ አገልግሎት መስጠት አቁሞ ወደ ዘረፋ ተሰማርቶ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት የከተማ ኑዋሪዎች እራሳቸውን ከትግል ተሳትፎ አርቀው መታየታቸው ስህተት ነው።
ከአገዛዙ ቁንጮ ጀምሮ በተዋረድ ያለው አመራር በሕዝብ ስቃይ ላይ በሚያፌዙበት በዚህ ወቅት ሕዝብ በቃኝ ብሎ ወደ ሰላማዊ የእምቢተኝነት ትግል መግባት አለበት። በእምቢተኝነት ተነስቶ የዚህን አረመኔና መዝባሪ አገዛዝ እድሜ ለማሳጠር ከመቸውም ጊዜ በላይ ፖለቲካዊ ሁኔታው ተሟልቷል። የቀረው አደረጃጀት ፈጥሮ ሕዝባዊ አመፅ ማቀጣጠል ነው። በከተሞችም ሆነ በገጠር ሕዝባዊ አመፅ በአንድ ጊዜ በሁሉም የአማራ ክልል አካባቢዎች በማቀጣጠል የፋኖን ትግል ለማጠናከርና ወደ ከፍታ ለማሸጋገር መሰራት አለበት። ሰላማዊ እምቢተኛነትን ከትግሉ ውጭ ማድረግ የሚጠቅመው አገዛዙን ነው። ይልቁንም አገዛዙን በሁለቱም የትግል ስልቶች ሌት ከቀን እረፍት መንሳትና ማስጨነቅ ያስፈልጋል። ሕዝቡ በቃኝ ብሎ መነሳት አለበት።
በሌላ በኩል የታጠቀው ኃይልም ቢሆን እስከ አሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ማንም ያልገመተው ውጤት በአጭር ጊዜ ያስመዘገበ ቢሆንም የትጥቅ ትግሉ ጠላትን ለመደምሰስና ጠንካራ የአማራ መከላከያ ሃይል ለመገንባት በሥልጠና፣ በአመራር፣ በአቅርቦትና በአደረጃጀት ማሳደግ ይገባል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ የመደበኛ ሰራዊት ቅርፅ የያዘ የእግረኛም ሆነ የመካናይዝድ ኃይል ግንባታ ያስፈልገዋል። የጠላትን ኃይል አሁን እየተሰራበት ባለው የደፈጣ ውጊያ የማዳከሙ ሥራ እየቀጠለ ሆኖ ጎን ለጎን ደግሞ ከመከላከል ወጥቶ ጠላትን እየደመሰሰ ወደፊት መገስገስ የሚችል መደበኛ ኃይል መዘጋጀት አለበት።
እነዚህ ሁለት ሥራዎች ማለትም በከተማ ሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝንትን በማቀጣጠል የሥራ ማቆም አድማ፣ የጠላትን ኃይል እንቅስቃሴ የሚገድብ የመንገድ መዝጋት፣ የጎዳና ላይ አመፅና ተከታታይ ሰልፍ የመሳሰሉትን ስልቶች በመጠቀምና ከትጥቅ ትግሉ ጋር በማቀናጀት ጠላትን መፈናፈኛ ማሳጣት ይገባል። ይህን በማድረግም ጠላት ያቀደውን በተራዘመ ግጭት ክልሉን የማውደምና ሕዝቡን የማሰላቸት ዓላማን ማክሸፍ እና ሞቱን ማፋጠን ይቻላል። ይሁንና ይህንን ሁኔታ የሚመራ በአግባቡ የተደራጀ ፖለቲካዊ ሃይል ባለመኖሩ ከሕዝባዊ ንቅናቄ ሊገኝ ይችል የነበረውን የሕዝብ አቅም በአግባቡ ማንቀሳቀስ ሳይቻል ቆይቷል። አሁንም ቢሆን ሳይዘገይ የሕዝቡን አቅም ዳር አስከ ዳር የማንቀሳቀስ ስራ በትኩረት መካሄድ አለበት። ይህንን ተልኮ ይዞ የሚሰራ አደረጃጀት በፍጥነት ወደ ስራ ማስገባት አስፈላጊ ነው።
3.7. ጥሪዎቸ እንደ ማጠቃለያ
የአማራ ሕዝብ እያካሄደ ያለው ትግል በማንነቱ ላይ ያተኮረውን የህልውና አደጋ የመቀልበስ ፍትሃዊ ትግል ነው። እየታገለ ያለውም በህልውናው ላይ ጥቃት እየፈፀመበት ያለውን የብልፅግና አውዳሚ ሃይል ነው። በመሆኑም ያለቦታችሁ የተሰለፋችሁ የአማራ ክልል የፀጥታ መዋቅር አባላት፣ በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ የምትገኙ የፖለቲካ አመራሮች በማንነት ላይ አተኩሮ የተከፈተው ፀረ አማራ ዘመቻ ፍትሃዊ ባለመሆኑ ልትቃወሙት ይገባል። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ስርአቱ ለእናንተም ምህረት ሊያደርግላችሁ አይችልም። አሁንም በወገናችሁ ላይ በተከፈተው ዘመቻ ተባባሪ ሆናችሁ ተሰልፋችሁ እያለም በስርአቱ እንዳልታመናችሁ እናንተው ታውቁታላችሁ። ወደፊትም ቢሆን አማራን እንደ ጠላት ቆጥሮ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተው ቡድን እናንተንም በጠላትነት ከመመልከት እና ከማጥቃት በፍፁም አይመለስም። ምክንያቱም ያለቦታችሁ የተሰለፋችሁ ናችሁና ሰልፋችሁን በፍጥነት ከሕዝባችሁ ጋር በማድረግ እንድታስተካክሉ ከራሴ ልምድ የመነጨ ምክሬንና ጥሪዬን በዚህ አጋጣሚ አቀርባለሁ።
ሌላው ጥሪዬን ማስተላለፍ የምፈልገው ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው። አገሪቱ አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት በቀጠናው መንግስታት እና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደ ዋነኛ የሰላም እና የመረጋጋት አጋር እና ምሰሶ ተደርጋ ትታይ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን በጎረቤቶቿም ይሁን በሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት የተናቀችና የረከሰች አገር ሆና እንድትታይ ሆናለች። በመከላከያ ሰራዊት የደረሰው ውርደት ደግሞ የከፋ ነው። የመጀመሪያው የውርደቱ መገለጫ እጅግ ያከብረው ከነበረው የአገሩ ሕዝብ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቱ ነው። የመንግስቱ ጦረኛ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ መሳሪያ በመሆን ከሞላ ጎደል ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በየተራ እየተዋጋ ነው።
የኢትየጵያ መከላከያ ሰራዊት በነበረው ኃይል የዜጎች ደም ያልፈሰሰበት ክልል ኢትዮጵያ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ያስቸግራል። ያ በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ሃይል፣ ግጭት ባለባቸው የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሰላም በማስከበር ዝናን ያተረፈው፣ በግጭት ወቅት ለሲቪሊያን ጥበቃ እና እንክብካቤ በማድረግ ክብር የነበረው፣ ለሰዎች ህይዎት አብዝቶ በመጠንቀቅ የምስጋና ሞገስ ይቸረው የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአሁኑ ወቅት የአንድን ሰው ስልጣን ለመጠበቅ ሲባል በማያሸንፈው ጦርነት ውስጥ ገብቶ ሴቶችን የሚደፍር፣ አርሶ አደሮችን በመደዳ የሚገድል፣ ወጣቶችን በጅምላ የሚረሽን፣ የሲቪሎችን ንብረት የሚዘርፍ፣ የሕዝብ መገልገያ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን የሚያወድም ወዘተ… የረከሰ እና ፀረ ሕዝብ የሆነ ተቋም ሆኗል። እናም መከላከያ ሰራዊት ከራስህ ወገን ጋር በመጋጨት የምትከፍለው ከንቱ መስዋእትነት ከእንግዲህ ይበቃል። ለአለቆችህ ከእንግዲህ ወገኔን መግደልም ሆነ በወገኔ መገደል በቃኝ በላቸው።
በመጨረሻም ለፋኖ አመራሮች እና አባላት የማስተላልፈው ጥሪ የሚከተለው ነው። በአማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ከወገናችሁ ጎን ተሰልፋችሁ ክቡር መስዋእትነት ለመክፈል እያደረጋችሁት ያለው ተጋድሎ የሚያኮራ እና ታሪካዊ ነው። እስከአሁን ባደረጋችሁት የአንድ አመት የትግል ጉዞ ማንም ሊገምተው የማይችለው እመርታ ላይ መድረሳችሁ ወገንን የሚያኮራ ሲሆን በሌላ በኩል ጠላትን የሚያስፈራ ድል መጎናፀፋችሁ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚከታተሉ ሁሉ አስገራሚ መሆኑ አያጠራጥርም። የአንድ አመት ጉዞአችሁ የአማራን ሕዝብ ተስፋ ያለመለመ ውጤት መሆኑ በገሃድ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን አስከአሁን የተጓዛችሁበት መንገድ የአማራ ሕዝብ ከተደቀነበት አደጋ አንፃር ገና በጅምር ደረጃ ያለ እና ብዙ ድክመቶች ያሉበት ትግል ሆኖ ሊታይ የሚገባው ነው። በጅምር ደረጃ ያለ ሕዝባዊ ትግል ብዙ ፈተናዎች ሊገጥሙት እንደሚችል አስቀድሞ የሚታወቅ ነው። ከጠላት ኃይል በላይ አስቸጋሪው ጉዳይ በውሰጣችሁ የሚገጥማችሁ የእርስ በርስ ሺኩቻ ነው። በማንኛውም ትግል በአላማ ላይ የተመሰረተ ውስጣዊ አንድነት አስከሚፈጠር ድረስ ከተለያዩ ፍላጎቶች ሊነሱ የሚችሉ ፈተናዎች ያጋጥማሉ።
በሰሞኑ በፋኖ አመራሮች መካከል እየታየ ያለው ሺኩቻ ሲታይ ግን እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው። በየቀኑ በጅምላ እየተገደለ ያለን ህዝብ ነፃ እናወጣለን ብለው ውድ ህይዎታቸውን መስዋእት እያደረጉ ባሉ የአማራ ህዝብ ልጆች ደም እንደ መቀለድ የሚቆጠር ነው። ይህ በዚህ ጦርነት የአማራን አንገት ለማስደፋት አቅዶ እየሰራ ካለው ዋነኛው የአማራ ጠላት አቢይ አህመድ ጋር ተሰልፎ አማራን እንደ መውጋት ሊይታይ የሚችል ነው። ይህንን አሳፋሪ ጉዳይ ደጋግመን እያነሳን ብንጥለው ትርጉም የለውም። ትልቁ ጉዳይ መሳሳቱ ሳይሆን ከስህተት መውጣት መቻሉ ነው። በሰሞኑ ተግባራችሁ አንዳችሁ በሌላችሁ ሳታመካኙ የየራሳችሁን ድርሻ ገምግማችሁ ተገቢውን ትምህርት እንድትወስዱ ጥሪየን አቀርባለሁ። እያልኩ ያለሁት ልዩነት ለምን ተፈጠረ አይደለም። መታረም ያለበት ልዩነቱን ትግሉን በሚጎዳ መንገድ ለመጠቀም መሞከራችሁ ነው።
በተጨማሪም የአማራን ትግል እንደግፋለን ብላችሁ አንዱን የፋኖ ክፍል ደግፋችሁ ሌላውን የምታንኳስሱ፣ እንዲሁም ቅራኔው እንዲባባስ የምታደርጉ የዲያስፖራ ወገኖቼ የምትሰሩት ክፍፍሉን የሚያባብስ ተግባር ነውና ከድረጊታችሁ ተቆጥባችሁ ለትግሉ ገንቢ አስተዋፅዎ እንድታበረክቱ ጥሪየን አስተላልፋለሁ። በፋኖ አመራሮች መካከል የተከሰተውን አለመግባባት ማባባስ የሚጠቅመው አገዛዙን ነው።ከዚህ አይነቱ የእርስ በርስ ንትርክ የፋኖ ቡድኖችም ሆኑ የአማራ ህዝብ ተጎጅዎች ናቸው።የፋኖ አመራሮች ከሳዩት ድክመት ተገቢውን ትምህርት ወስደው ትግሉን የበለጠ ወደፊት ለማራመድ እንዲችሉ ገንቢ ሚና መጫዎት ተገቢ ነው። ካልተቻለ ደግሞ በእንደዚህ ያለ ወቅት አንድን ቡድን ደግፎ ሌላውን ከመውቀስ ይልቅ ዝም ማለትም ትልቅነት ነው። ሜዳ ላይ የሚገኙት ፋኖዎች ችግራቸውን ራሳቸው እንዲፈቱ ጊዜ እና እድል ስጧቸው።
አመሰግናለሁ!
ገዱ አንዳርጋቸው
ሀምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም “
__