Please wait, video is loading...
የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች!!
በመስከረም አበራ መጋቢት 2016 ዓም ( የገጽ ብዛት = 94)
መግቢያ
......
ህወሃት እና ኦነግ በመሰረቱት የብሄር ፖለቲካ ዉስጥ አማራዉ ግራ ተጋብቶ የኖረ መሆኑ የሚንፀባረቅባቸዉ በርካታ ገሃድ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ በግሌ የሚገርመኝን ለማንሳት ያህል በኦነግ/ህወሃት የዘዉግ ፖለቲካ ስርዓት ዉስጥ በተለይ በሽግግር ዘመኑ ወቅት አማራዉ በመገለሉ ምክንያት ጥብቅና የሚቆምለት ወኪል በማጣቱ ሳቢያ በየጥጋጥጉ እያለቀ፣አማራ ተብሎ በተከለለዉ ግዛት ዉስጥ ሊከለሉ ይገባቸዉ የነበሩ ግዛቶች (መተከል፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ ራያ፣ ደራ) ለተለያዩ ክልሎች በገፀ-በረከትነት እየተሰጡ ባሉበት ሁኔታ ዉስጥ ተቀምጦ አብዛሃኛዉ የአማራ ልሂቅ ይቆጭ የነበረዉ ኢትዮጵያ ሁለቱንም የባህር በሮቿን አጥታ የባህር በር የሌላት ሃገር በመሆኗ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአማራዉ ልሂቅ የብሄር ፖለቲከኞች አንቀጽ 39ን ተጠቅመዉ ኢትዮጵያን እንደ ዩጎዝላቪያ ታሪክ እንዳያደርጓት የብሄር ብሄርተኛን ሁሉ በማባበል ላይ ተጠምዶ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ ነባራዊ ሃቅ የምንረዳዉ በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የጻፉት ጸሃፊ አማራዉ የብሄር ፖለቲካን መልመድ ባለመቻሉ በብሄር ፖለቲከኞች ብልጫ ተወስዶበታል ማለታቸዉ ሃቅ
መሆኑን ነዉ፡፡
የአማራ ልሂቅ የዘዉግ ፖለቲካዉን መልመድ አለመቻሉ በርካታ ጉዳቶችን አምጥቶበታል፡፡ የመጣበትን ጉዳት ለመረዳት በርካታ ዘመናትን ማስቆጠሩ ደግሞ “በእንቅርት ላይ...............” የሚሉት አይነት ነገር ነዉ፡፡የአማራዉ ልሂቅ የብሄር ፖለቲካዉን ሊለምድ ያልቻለዉ የብሄር ፖለቲካ ከሰዉ አእምሮ በላይ የሆነ ዉስብስብ ነገር በመሆኑ አማራዉ መረዳት አቅቶት አይደለም፡፡ ይልቅስ አማራዉ የብሄር ፖለቲካን መልመድ ያልቻለዉ የብሄር ፖለቲካዉ በዉጤት ደረጃ ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ፖለቲካ የተሻለ አትራፊነትና ምርታማነት የሌለዉ እንደሆነ ስለሚረዳ ነበር፡፡ ይህ የአማራዉ ልሂቅ ፖለቲካዊ መረዳት ስህተት የሌለበት አረዳድ ነዉ፡፡ ለዚህ ማስረጃዉ በአሁኑ ጊዜ የብሄር ፖለቲካዉ ቀሳዉስት ራሳቸዉ አዋጩ መንገድ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እንደሆነ ለአማራዉ _ ለእራሱ _ ለማስረዳት ለእናቷ ምጥ እንደማስተማር ባለ ድካም ዉስጥ የሚገኙ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በየመንግስት ሚዲያዉ ስለ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት የሚሰብኩ የብሄር ፖለቲካዉ ቀሳዉስት ኢትዮጵያን የሚወዷት ስልጣን ላይ ተቀምጠዉ ሲያዩዋት ብቻ መሆኑ አማራዉ የተረዳዉ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማማ ላይ ለመድረስ እንዳልቻሉ ማሣያ ነዉ፡፡
አማራዉ የተረዳዉ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ርዕዮት ስልጣን ላይ ሲቀመጡ የሚያጠልቁት ከስልጣን ሲወርዱ ደግሞ አዉልቀ ጥለዉ የሚያበሻቅጡት አይነቱን አይደለም፡፡ አማራዉ የተረዳዉ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እሳቤ ከስልጣን ወርደዉ ብቻ ሳይሆን በማንንቱ ተነጥሎ እየተገደለ ሳይቀር “ኢትዮጵያ የምትፀና ከሆነ ይሁን” የሚል ጥብቅ እምነት ነዉ፡፡ አማራዉ የተረዳዉ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እሳቤ አማራ ያልሆነ ጠቅላይ ሚኒስቴር ስልጣን ላይ ሲወጣ የኢትዮጵያን ስም እስከጠራና ለኢትዮጵያዉያን ሁሉ ፍትሃዊ ስርዓት ማምጣት ከቻለ የኔዉ ወገን ነዉ ብሎ መቀበል ነዉ፡፡
ጠ/ሚ አብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ በአማራ ክልል የተደረጉ ትላልቅ የፌሽታ ሰልፎች የአማራን ህዝብን ፖለቲካዊ ስነልቦና ግልጽ ያደረጉ ነበሩ፡፡ ሆኖም በአማራዉ ልቦና የታሰበችዉ ኢትዮጵያ ልትመጣ አልቻለችም፡፡ ይልቅስ በብሄርተኞቹ አፍ የምትንቆለጳጰስሞ ኢትዮጵያ ለአማራዉ ይዛ የምትመጣዉ ነገር ከጀኖሳይድ እስከ አፓርታይድ የዘለቀ፣ የበደል ድግስ እንደሆነ ዘግይቶም ቢሆን ተረድቶታል፡፡ ስለሆነም የብሄር ፖለቲካዉን ምንዛሬ ይዞ ወደ ፖለቲካዉ መግባት አማራጭ የሌለዉ ነገር እንደሆነ አዉቆ በዘመኑ ቋንቋ እየተናገረ ይገኛል፡፡
አሁን የአማራዉ ልሂቅ/ህዝብ/ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን በብሄር ፖለቲካዉ ዉስጥ ከጨዋታ ዉጭ የመሆኑ ነገር ያመጣበትን ጉዳት አጢኗል፡፡ በመሆኑም ወቅቱ የሚፈልገዉን የፖለቲካ ምንዛሬ (በብሄር ተደራጅቶ መጫወት ይዞ ለመገኘት ችሏል።
አማራዉ የብሄር ፖለቲካዉን ባልታሰበ ፍጥነት ተረድቶ፣ ባልተጠበቀ መናበብ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ይህ በአማራዉ ልሂቅ/ህዝብ በኩል የታየዉ ድንገተኛ የሚመስል የአማራ ብሄርተኝነት ንቃት፣ መደራጀትና ፈጣን እርምጃ ለወትሮዉ “አማራዉን በማያዉቀዉ የብሄር ፖለቲካ መስመር ወስደን ግራ አጋባነዉ” ሲሉ የኖሩ የብሄር ፖለቲካ ልሂቃንን ግራ አጋብቷል፤ አሁን የግራ አጋቢና የግራ ተጋቢ መስመር ተቀያይሯል፡፡ አሁን በተራቸዉ የአማራዉን ብሄርተኝነት መልመድ ያልቻሉት የአማራ-ጠሉ የብሄር ፖለቲካ ቀሳዉስት ሆነዋል፡፡ የብሄር ፖለቲካዉን እስከወዲያኛዉ አይለምድም ተብሎ የነበረዉ የአማራ ልሂቅ/ህዝብ/ በሚገርም ብቃት የብሄር ፖለቲካዉን ማስኬድ መቻሉ፣ ከጥግ እስከ ጥግ መብቱን ለማስከበር ሞትን ሳይፈራ መነሳቱ ማንንም ግራ የሚያጋባ፣ተአምር የሚመስል ነገር ነዉ፡፡
የአማራዉ ብሄርተኝነት አይመጣም በሚል እርግጠኝነት ላይ የነበሩት የአማራ-ጠሉ ስርዓት አቋቋሚዎች፣ ደጋፊዎችና ባለሟሎች የአማራ ብሄርተኝነት በአጭር ጊዜ ያስመዘገበዉ ዉጤት በእጅጉ አስደንግጧቸዋል። በመሆኑም አማራዉ በማንነቱ ምክንያት የደረሱበት እየደረሰበት ያሉ በደሎች እንዲቆሙ የሚያነሳቸዉን ጥያቄዎች መረዳት የሚችሉበትን የፖለቲካ ቀልብ አጥተዋል፡፡ የአማራ ህዝብ የሚያነሳቸዉን ጥያቄዎች በርጋታ ሰምቶ ለመመለስና ችግሩን ለማስቆም በመምከር ፋንታ መፍትሄ የሌለዉ መንገድ መጓዝን መርጠዋል፡፡ ይህ መፍትሄ አልቦ መንገድ የአማራ ህዝብ የሚያነሳቸዉን ጥያቄዎች በመካድ፣ በማጣጣልና በማራከስ ይገለጣል፡፡
አማራ-ጠሉ ስርዓት የአማራ ህዝብን ጥያቄዎች ከማዳመጥ እና መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የህዝቡ ትግል ምክንያት አልቦ ዝም ብሎ የመተኮስ አምሮት ያመጣዉ የአመፀኝነት አባዜ አድርጎ መፈረጁን ተያይዞታል፡፡ እዉነቱ ግን ሌላ ነዉ፡፡
የአማራ ህዝብ በብሄር ተደራጅቶ ሲታገል ትግሉን ግድ ያደረጉ በርካታ የትግል ምክንያቶችን( Causes ) አንግቦ ነዉ እንጂ ሰላም ጠልቶ፣ የጦረኝነት መንፈስ ተጠናዉቶት ወይም የሚወዳትን ሃገር የማፍረስ አዉዳሚነት ተቆራኝቶት አይደለም፡፡ የኦሮሞ ብልጽግና መራሹ መንግስትም የሚያወራዉን ያህል ሰላም ወዳድነት ካለዉና ኢትዮጵያን ማትረፍ ከፈለገ በቅድሚያ ሊወሰደዉ የሚገባዉ እርምጃ የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች በእርጋታ ለማዳመጥ የሚያስችል የፖለቲካ ስክነትን መላበስ ነዉ፡፡ አሁን መንግስት የያዘዉ ግን ሌላ ነዉ፡፡ በአንድ በኩል ለሰላም ዘብ ቆሜያለሁ ይላል፣ በሌላ በኩል የአማራ ህዝብ እየሞተለት ያለዉን ጥያቄዉን በማጣጣል በተለመደዉ መፍትሄ አልቦ ጉዞ እየነጎደ ነዉ፡፡ የኦሮሞ ብልጽግና መራሹ መንግስት የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች ለማዳፈን፣ ለማጣጣል እና ለማራከስ የሚያደርገዉን መሟሟት ለመረዳት በቅርቡ የሃገራችን ኤታማዦር ሹም ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ታህሳስ 01/2016ዓ.ም ለመከላከያ ቴሌቭዥን እና ሰሌሎች የመንግስት ሚዲያዎች የሰጡትን ቃለመጠይቅ ማየቱ ብቻ በቂ ነዉ፡፡ ይህ የኤታማዦር ሹሙ ንግግርም አሁን ስልጣን ላይ ያለዉ አማራ-ጠል ስርዓት የአማራን ህዝብ ለማዳመጥ ተፈጥሮዉ የማይፈቅድለት እንደሆነ የሚያሳይ ነዉ፡፡
በሃገራችን ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ መንግስት ቢያንስ የህዝብን ጥያቄዎች በትህትና የማዳመጥ ስክነት መላበስ አለበት፡፡ የህዝብን ጥያቄዎች በማጣጣልና በማራከስ የሚጸና ወንበር የለም! ስልጣን ላይ ያለዉ የኦሮሞ ብልጽግና መራሹ መንግስት የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች የሚያጣጥለዉ ከአማራ ጠል ተፈጥሮዉ የተነሳ እንደሆነ ግልፅ ነዉ፡፡ ሆኖም በአማራ ልሂቅ በኩልም ህዝቡን ጥያቄዎች ደርዝ ባለዉ ሁኔታ በፅሁፍ ሰንዶ ማቅረብ አለመቻሉ መንግስት የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች ለማዳፈን፣ ለማጣጣል፣ ለማራከስና ለመካድ እንዲመቸዉ በር ከፍቷል፡፡ ይህን ሰነድ አስፈላጊና አንገብጋቢ ያደረገዉም ይህን በአማራዉ ልሂቅ በኩል ያለዉን ክፍተት በመጠኑም ቢሆን የመሙላት ምኞት ነዉ፡፡
ከላይ በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደተሞከረዉ ካለፉት አመታት ይልቅ ዛሬ ላይ አማራዉ የብሄር ፖለቲካዉ የሚፈልገዉን የፖለቲካ ዘይቤ ተላብሶ መብቱን ለማስከበር የሚችልበት የፖለቲካ ንቃትና የትግል ቁርጠኝነት ላይ ደርሷል፡፡ ይህ እጅግ ተስፋ ሰጭ እምርታ ነዉ፡፡ ሆኖም ለአማራ ህዝብ ስኬት በትግሉ ሜዳ ከሚደረገዉ የከበረ መስዋዕትነት ጎን ለጎን የትግሉን ፖለቲካዊ መሰረት ማዕናት በእጅጉ አስፈላጊ ነዉ፡፡ የአንድ ህዝብ ትግል ፖለቲካዊ መሰረት ከሚጸናበት መንገድ ቀዳሚዉ ህዝቡን ለትግል ያስነሱትን ጥያቄዎች ግልጽ በሆነ መንገድ ሰንዶ በማቅረብ፣ ህዝቡ ስለትግሉ ምክንያቶች(Causes) ተቀራራቢ መረዳት እንዲኖረዉ ማስቻል ነዉ፡፡
የህዝብን ጥያቄዎች ደርዝ ባለዉ መንገድ ሰንዶ ማቅረብ ሲቻል ተገዳዳሪም ብድግ ብሎ የህዝብን ጥያቄዎች ማጣጣል እንዳይችል ይከለክለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአማራ ህዝብ ትግል በአመርቂ ሁኔታ እየተፋፋመ ቢሆንም ትግሉን አስፈላጊ ያደረጉ ምክንያቶችን ሰንዶ የማቅረቡ ነገር ግን እስከዛሬ ድረስ እዉን አልሆነም፡፡ እያንዳንዱ የአማራ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ለትግል መነሳት እንዳለበት የሚያስገድድ በደል እና መጠቃት እንደ ደረሰበት ልቦናዉ ቢነግረዉም ጥያቄዎቹን አብጠርጥሮ በማወቅ ረገድ ተቀራራቢ መረዳት ላይ ተደርሷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ አንድ ህዝብ የሚያደርገዉ ትግል ዉጤታማ እንዲሆን ደግሞ የትግሉ ምክንያት የሆኑ ጥያቄዎችን ወጥ በሆነ ሁኔታ ተረድቶ በአንድ ቋንቋ ማስረዳት መቻሉ ነዉ፡፡
የትግሉ ምክንያቶች በልሂቃን/ምሁራን ተሰንደዉ ሳይቀርቡለት አሁን እያደረገ ያለዉን የመሰለ አመርቂ ትግል በማድረጉ ረገድ የአማራ ህዝብ ቀዳሚዉ ህዝብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በአለማችን የተደረጉ ስኬታማ ትግሎች አመርቂ ዉጤት የሚያስመዘግበት በመጀመሪያ የትግሉ ምክንያቶች በልሂቃን/ምሁራን ተብጠርጥረዉ ተተንትነዉ ቀርበዉ፣ቀጥሎም በቀረቡት የትግል ምክንያቶች ላይ በመመርኮዝ ህዝብን ለትግል የማነሳሳት የቅስቀሳ ስራ በልሂቃን አማካኝነት ተሰርቶ ነዉ፡፡ የአማራ ህዝብ ግን የበደሉ ብዛትና ርዝመት ልቦናዉን ለትግል አነሳስቶት እንጅ ማንም የትግሉን ምክንያት በሰነድ ሰንዶ አቅርቦለት አይደለም ለትግል የተነሳዉ፡፡ ይህ የአማራ ልሂቃንን በእጅጉ የሚያስወቅስ ክፍተት ነዉ፡፡ ሆኖም ክፍተቱን ለመድፈን አሁንም
አልረፈደም፡፡
የአማራ ህዝብ ለሶስት አስርት አመታት የኑሮዉ አካል ሆኖ የዘለቀዉ የማንነት ተኮር በደል ለትግል አነሳስቶት አሁን ላይ የተፋፋመ ትግል በማድረግ ላይ ነዉ፡፡ ሆኖም የህዝቡን ጥያቄዎች ሰንዶ ማቅረቡ የህዝቡ ትግል መነሻዉና መድረሻዉ በሁሉም ህዝብ ዘንድ የታወቀ መግባባት ላይ የተደረሰበት እንዲሆን ያስችላል፡፡ የህዝቡን ጥያቄዎች በዉል ሰንዶ ለማቅረብ የሚደረገዉ ጥረት የአማራ ህዝብ እያለፈበት ያለዉን በደል ምንነት፣ጥልቀት፣ስፋት እና መገለጫ በተመለከተ በህዝቡ ዘንድ ተቀራራቢ መረዳት እንዲኖር ያስችላል፡፡ ይህን የማድረጉ ስራ ቀደም ተብሎ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ በህዝቡ ላይ ያንዣበበዉ አደጋ ነፍስ ዘርቶ እየተራመደ አማራ የተባለ ሰዉ ሁሉ ቤት ከመግባቱ በፊት መግታት ይቻል ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ የአማራ ህዝብ በአማራ ጠሉ ስርዓት የተደገሰለትን የመከራ ፅዋ መራራነት ተጎንጭቶ፣ በአሰቃቂ የሞት ጥላ ስር አልፎ፣በአሳፋሪ የዉርደት መንገድ ተጉዞ ብቻ እንዲረዳዉ ግድ ብሏል፡፡
ከመከራዉ ብቻ እንዲማር የተፈረደበት የአማራ ህዝብ የበደሉን ናዳ በየተራ ካስተናገደና በቃኝ ብሎ ለትግል ከተነሳ በኋላም ቢሆን የአደጋዉን አይነት፣ጥልቀትና ስፋት በእኩል ደረጃ ተገንዝቧል ለማለት ያዳግታል፡፡ ማንኛዉም ህዝብ የሚታገለዉ ባወቀዉ ልክ ነዉ፡፡ በአማራ ህዝብ ትግል ዉስጥ በህዝቡ ዘንድ የትግል ምክንያቶችን የመረዳቱ ነገር ዉስን ከመሆኑ የተነሳ የአማራ ህዝብ ትግል ወልቃይትን፣ራያን፣መተከልን እና ደራን ለማስመለስ ብቻ የሚደረግ የሚመስለዉ ሰዉ ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአማራን ህዝብ ትግል ያነሳሳዉ በወለጋና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረገዉ ግድያ ብቻ እንደሆነ የሚያስበዉ ሰዉም እንዲሁም በርካታ ነዉ፡፡ የአማራ ህዝብ ትግል ምክንያቶችና ጥያቄዎች ግን እነዚህን ጉዳዮችንም ጭመር ያጠቃልላሉ እንጂ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡
የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች ከግዛት ጥያቄዎች፣ከማንነት ተኮር ጭፍጨፋዎች እና መፈናቀሎች ጋር ብቻ አያይዞ የማየቱ ዝንባሌ ለአማራ-ጠሉ ስርዓት ጥሩ የማጭበርበሪያ መንገድ የሚከፍት ነዉ፡፡ ይህም ማለት አማራ ጠሉ ስርዓት የግዛቶቹን ጥያቄ “በህገ-መንግስታዊ መንገድ እልባት ያገኛሉ” በማለት እና ያፈናቀላቸዉን አማሮች “ወደ ቀያቸዉ እመልሳለሁ” በማለት የህዝቡን ትግል ሊያዳፍን ይሞክራል ማለት ነዉ፡፡ የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች በተገቢዉ ሁኔታ ተንትኖ ለህዝቡ ማስረጹ ጠቃሚ የሚሆነዉ ለዚህ ነዉ፡፡
በማንነት ላይ መሰረት ባደረገ መልኩም ሆነ በሌላ መንገድ ተደራጅቶ በሚደረግ ትግል የህዝብን በደሎች እና ጥያቄዎች ነቅሶ አዉጥቶ በሆኑት ልክ በመተንተን ለህዝብ ማቅረብ ዋነኛዉ የትግሉ ምዕራፍ ነዉ፡፡ በሃገራችን ስኬታማ ትግል ያደረገዉ ህወሃትም ሆነ የትግል አጋሩ ኦነግ ይህን ምዕራፍ በአመርቂ ሁኔታ አልፈዉታል፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ቡድኖች የትግላችን ምክንያት ነዉ ብለዉ በተነተኑት የማታገያ ማኒፌስቶ እና የተለያዩ የትግል ሰነዶች ሃሰተኛ ትርክቶችን ያለምንም የሃላፊነት ስሜት እዉነት አስመስለዉ እስከማቅረብ ሄደዋል፡፡ ኦነግ፣ህወሃት እና የሌሎች የብሄር(ዘዉግ) ድርጅቶች ልሂቃን ሃሰተኛ ትርክትን የትግል ምክንያት አድርገዉ ማቅረባቸዉ ከሞራልም ከህግም አንጻር የሚያስጠይቃቸዉ ነዉ፤ ሆኖም ህዝባቸዉን ለትግል ለማነሳሳት ሲሉ የትግል ምክንያት ያሉትን (ሃሰቱ ቢበዛም) በወማ ሰንደዉ ያቀረቡበት እጅግ የታሰበበት እና የተቀናጀ አካሄድ ግን ከአማራ ልሂቃን ጋር ለዉድድር እንኳን የማይቀርብ ነዉ፡፡
እነዚህ ልሂቃን ሃሰተኛ ትርክትን እንኳን ያለምንም ሃፍረትና ማቅማማት እዉነት አስመስለዉ አቅርበዉ፣ ህዝባቸዉን አታግለዉ፣መንበረ ስልጣን ለመያዝ ሲበቁ እጅግ ግልጽ የሆነዉን በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረገዉን ማንነት ተኮር በደል ሰንዶ አቅርቦ ማታገያ ማድረግ ያቃተዉ የአማራ ልሂቅ ከእራሱ በቀር ማንንም መዉቀስ አይችልም፡፡ ለረዥም ዘመናት የዘለቀዉን በአማራ ህዝብ ላይ የተደረገና እየተደረገ ያለ በደል ተንትኖ ወደ ህዝቡ ማስረጽ ሳይችል የኖረዉ የአማራ ልሂቅ ከአሁን በኋላ የሚያደርገዉ አስተዋጽኦ የቀደመ ዳተኝነቱን የሚያካክስ፣ ርብርብ በሚመስል ሁኔታ የሚደረግ መሆን አለበት፡፡ የአማራን ህዝብ ትግል አይቀሬ ያደረጉ ጥያቄዎችን ምንነት፣ ስፋትና ጥልቀት በአመርቂ ሁኔታ የማቅረቡ ስራ የበርካታ ምሁራንን የተባበረ አስተዋጽኦ የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም ለመነሻ ያህል የሚሆኑ ሃሳቦችን በዚህ ሰነድ ለማንሳት ይሞከራል፡፡
ይህን የመነሻ ሃሳብ ሰነድ ለመጻፍ አስፈላጊ ያደረገዉ የኦሮሞ ብልጽግና መራሹ መንግስት የአማራን ህዝብ ትግል ምክንያት አልቦ ለማድረግ እያደረገ ያለዉ ጥረትና በአማራዉ ልሂቅ በኩልም የትግሉን ምክንያት እስከዛሬ ሰንዶ ማቅረቡ ስላልተቻለ ለመንግስት ፍርደ-ገምድልነት በር ከፍቷል ተብሎ መታሰቡ ነዉ፡፡ በዚህ እሳቤ አነሳሽነት የተዘጋጀዉ ይህ ሰነድ የመነሻ ሃሳብ ለመስጠት ያህል የቀረበ እንጅ በራሱ ምሉዕና መዳበር የማይፈልግ የተዋጣለት አይደለም፡፡
ሙሉውን ከዚህ ላይ ዳውሎድ በማድረግ ያንብቡ!
*
*