በባህላዊ አጠራሩ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ቀን እንቁጣጣሽ እንለዋለን ። እንቁጣጣሽ ምን ማለት እንደ ሆነ እዚህ ፎረም ላይ ደጋግሜ የጻፍኩበት ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ አልገባም ። ነገር ግን የእንቁ ጣጣ፣ የሴት ጌጥ ጣጣ ማለት አይደለም ።
በአገው ድምጽ እንቁጣጣ የተባለው ደሮ እንኩታታ ይባል ነበር ። እንኩታታ እንኩ እንኩ ተባብሎ የስጦታ መለዋወጫ እንኩታታ እለት ማለት ነው ። ይህ በአዲስ አመት እለት የሚደረገው የስጦታ ልውውጥ እንቁ (የከበረ ድንጋይ) ሳይሆን የአደይ አበባ ነበር ። ወንድ ልጆችም ፣ ሴት ልጆችም ከቤት ቤት እየዞሩ እንኳን አደረሳችሁ እየዘፈኑ የአደይ አበባ ይሰጡ ነበር ።
የአደይ አበባ በሌለበት ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ደሞ ልጆች የአደይ አበባ ምስል በወረቀት ላይ በመሳል በየቤቱ እየዞርን እንሰጥ ነበር ። ያንን የአበባ ስጦታ ለውውጥ እንኩ እንኩታ ነው እንኩታታ ብሎም እንቁጣጣሽ የምንለው ።
ይህ የአበባ እንኩታታ ከክርስትናም በፊት የነበረ ባህልና ስርዓት ነው ።
ጥያቄው ወንጌል በኢትዮጵያ ከመሰበኩ በፊት የተለያዩት የኢትዮጵያ ጎሳዎች ይህን አዲስ ዓመት ቀን ምን ብለው ይጠሩት ነበር ? እዚህ መጣጥፍ ላይ ስለ ጉራጌ አክራሚ ብቻ ትንሽ ልበል ።
በጉራጌዎች በተለይ ክስታኔ ጉራጌዎች ዘንድ እንቁጣጣሽ 'አክራሚ' ይባላል። ከማንኛውም በዓላት የላቀ እጅግ የተከበረው ፣ መንፈሳዊ፣ ከብቶች እንኳን ከቤት ከበረት የማይወጡበት ፣ ምንም ነገር ፈጽሞ የማይሰራበት፣ እጅግ እጅግ ክቡር ቀን ነው ።
አክራሚ የሚለው ቃል የተሰራበት ስረቃል (ኢቲሞሎጂ) ና ስነፈለግ (ፊሎሎጂ) ዝርዝር ውስጥ አልገባም ። በአማርኛ 'ክረምት' እና የመከር (የመሀር) ወራት ከምንለው ጋራ የተያያዘ ነው ። በጉራጌኛ ክረምት 'ክርማን' ይባላል ። እሱም እርጥብ፣ የዝናብ፣ የዉሃ፣ የልምላሜ አረንጓዴ ግዜ ማለት ነው።
ስለዚህ አክራሚ የክርማን (የክረምት) መጨረሻ ማለት ነው ።
አክራሚኛ (እንቁጣጣሻችን) አንድ ሳምንት ብቻ ቀርቶታል !!!
እስቲ እናንተ በምትመጡበት አካባቢና ባህል ቀኑና አከባበሩ ምን እንደ ሚባልና እንዴት እንደ ሚከበር ጀባ በሉን !!!
የኬር አክራሚ ዬኩንልነ