ም/ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የአሜሪካን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አቶ ደመቀ ለልዩ መልዕክተኛው መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎች ላይ ገለጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። በዚህም አቶ ደመቀ፤ በአፍሪካ ህብረት መሪነት በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ አማካኝነት ለተጀመረው የሰላም ጥረት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ተደራዳሪ ቡድን አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል። ም/ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተኩስ አቁም ስምምነቱ፣ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ ተጀራሽነት እና ሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉም ለልዩ መልዕክተኛው ገልፀዋል።
መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ሙሉ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ባለበት ወቅት የህወሓት ቡድን በተቃራኒው እያሳያ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል የሚፈጥር በመሆኑ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቡድኑ ላይ ጫና ሊያሳርፍ ይገባል ማለታቸውንም ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
