By Abrah Desta
===========
"የመንግስት ሥራ ማዕድ ማጋራት አይደለም" ብዬ የፃፍኩ ግዜ "የመንግስት ሥራ ታድያ ምንድነው?" የሚል ጥያቄ ቀርቧል።
5 ዋና ዋና የመንግስት ሐላፊነቶች
1. መንግስታዊ አገልግሎት መስጠት
በያንዳንዱ የመንግስት ቢሮ ሐላፊዎች ያለአድልዎ፣ ያለ ጉቦ ወይም ያለምንም ሙስና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም ዜጋ እኩልና ተገቢ አገልግሎት ይሰጣሉ ወይ? ህዝብ በመንግስት ተቋማት ይረካል ወይ?
2. የዜጎች ደሕንነት መጠበቅ (ፀጥታ)
የመንግስት ሐላፊዎች እያንዳንዱን ዜጋ ደሕንነቱ ተጠብቆ ያለምንም ስጋት በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ዋስትና እየሰጡ ነወይ? ህዝብ መንግስትን ይተማመናል ወይ?
3. ኢኮኖሚ ማረጋጋት
መንግስት የኑሮ ውድነቱን መቆጣጠር ችሏል ወይ? ለወጣቶች ስራ ፈጥሯል ወይ? ኢኮኖሚው የተረጋጋ ነወይ? ሰራተኞች በደሞዛቸው መኖር ይችላሉ ወይ? ዜጎች ተስፋ አላቸው ወይ? ህዝብ መኖር ችሏል ወይ?
4. ሰላምን ማስጠበቅ/ ማስፈን
ዋነኛው የመንግስት ስራ ጦርነትን በማስቀረት ህዝብን ከጦርነት መታደግ ነው። የዜጎችን ህልውና ለመጠበቅ መንግስት ጦርነትን ማስቀረት አለበት። "ጦርነቱን ማን ጀመረው?" የሚል ትርጉም የለውም። ጦርነቱ ማንም ይጀምረው ጦርነቱ እንዳይጀመር የማድረግ ሓላፊነት የመንግስት ነው። ከተጀመረም ማስቆም አለበት።
መንግስት ጦርነት እንዳይጀመር መቆጣጠር ወይም ማስቆም አቅቶት ህዝብ እንዲፈናቀል፣ እንዲራብ፣ እንዲሞት ካደረገና ካስደረገ ሐላፊነቱ አልተወጣምና በፖለቲካ ወድቋል። መንግስት የሚመራውን ህዝብ ሰላም እንዳያጣ መስራት አለበት። ማዕድ ማጋራት የግለሰቦች ወይም የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ስራ ነው።
5. ህዝብን መምራት
መንግስት ከየት ወዴት እንደሚሄድ በግልፅ አቅጣጫ አስቀምጦ ለተግባራዊነቱ መስራት አለበት። የሚመራውን ህዝብ ከችግር ማላቀቅ አለበት። ስለዚህ መሪነት የመንግስት ቁልፍ ተግባር ነው።
(ለሁለቱም የብልፅግና እና የህወሓት መንግስታት ይመለከታል)
Please wait, video is loading...