አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የክልሉ መንግሥት ጉዳዮች ኮሙኒኬሽን አስታወቀ። በክልሉ 263ሺህ ተፈናቃይ ዜጎች እንዳሉም ተመላክቷል።
የአማራ ክልል መንግሥት ጉዳዮች ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በክልሉ በተለያየ ጊዜ የተፈናቀሉ እንዲሁም ጦርነቱ በፈጠረው ችግር ሳቢያ ወደ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በአሁን ወቅትም ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ 263ሺህ ዜጎች በክልሉ ውስጥ ይገኛሉ።
የተፈናቀለ ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ያላመረተና ችግር ውስጥ የገባ እርዳታ የሚፈልግ 11ነጥብ6 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሩን የገለጹት አቶ ግዛቸው፤ ይህም በኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንዳለውና ክልሉም በዚህ ደረጃ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን አስታውቀዋል።
አቶ ግዛቸው፤ በተለያየ መንገድ ከዋግኅምራ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ ከአላማጣና ከኮረም ተፈናቅለው ወደ ቆቦ የመጡ፤ በተመሳሳይ በሰሜን በኩል ተፈናቅለው ወደ ደባርቅ የመጡ እንዳሉ ጠቅሰዋል። በልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ክልሉ የመጡበት አጋጣሚም እንዳለም ጠቁመዋል። በድምሩ በአሁን ወቅት በክልሉ 263ሺህ ተፈናቃይ ዜጎች እንዳሉና አጠቃላይ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥርም 11ነጥብ 6 ሚሊዮን እንደሆኑ አመላክተዋል።
ተፈናቃዮች ብዙ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፎና ተቃጥሎ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሰው፤ ይህ የክልሉን ልማት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ችግር እንዲገጥመው ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል።
የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ቁሳቁስና አልባሳት እንዲሁም ምግብን ጨምሮ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሰጥ እያደረገ ቢሆንም፤ ድጋፉ በቂ እንዳልሆነና ተረጂዎችን ማርካት እንዳልቻለም ገልጸዋል። ነገር ግን ዜጎች ለከፋ አደጋ እንዳይዳረጉና ሕይወታቸውን የሚያቆዩበትን ድጋፍ ለማድረግ ተሞክሯል ብለዋል። ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ሌሎችም ረጂ ድርጅቶች በስፋት ለሰብዓዊ ድጋፉ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ አቶ ግዛቸው ገለጻ፤ ይህ ሁሉ ሰው ሠርቶ የአካባቢውን ልማትና ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ የራሱ የሆነ ድርሻ የነበረው ቢሆንም አሁን ላይ ከሥራ ውጭ ሆኗል። እነዚህን ዜጎች ማገዝ ስለሚገባ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልጋል። እነዚህ ሰዎች የሚረዱት ምናልባትም ሌላ ልማት ሊለማ የሚችለበትን ሀብት በመጠቀም በመሆኑ ኢኮኖሚ ይጎዳል። በመንግሥት ላይም ጫና ይፈጥራል። ሕዝቡን ለማቋቋም ከፍተኛ የሆነ አቅም ይጠይቃል።
ጫናው እንዳይበረታ ለማድረግ ከጎረቤት ክልሎች ጋር ተመካክሮ በመሥራት ቀጠናውን ሰላም ማድረግ እንደሚገባ አቶ ግዛቸው አመልክተው፤ ለሰላም መድፍረስና ለዜጎች መፈናቀል መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በጋራ በመመካከር መሥራት ትልቁ መፍትሔ እንደሆነና ለዚህም ሁሉንም ሰው የመፍትሔው አካል ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም
https://www.press.et/ama/?p=68884