Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 11594
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

"የአሁኑ ምርጫ በቱርኪሜኒስታን እና ኡዝቤክስታን ከተካሄዱት አስቂኝ ምርጫዎች ጋር ነው የሚመሳሰለው። የአል-ሲሲ እና የሳዳም ሁሴን ምርጫዎች እንኳ ከዚህ ይሻላሉ።" አፈንዲ ሙተቂ

Post by sarcasm » 05 Oct 2021, 07:55

አታካብዱ!
----
አፈንዲ ሙተቂ
----
ብዙ ነገሮችን የማናወራው ለወያኔ ዱላ ላለማቀበል ስለምንጠነቀቅ ነው። ሁሉንም ነገር እንደወረደ ተናገሩ ካላችሁ ግን መዘርገፍ ይቻላል።
-----
ለምሳሌ:

ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ ነበር? አዑዙቢላህ! እንዲህ ዓይነት ምርጫ በሕይወቴ አይቼ አላውቅም። እስቲ በየትኛው ሀገር ነው ፖሊስ በየቤቱ ላይ እየዞረ "የምርጫ ካርዳችሁን አሳዩን" እያለ ህዝቡን የሚወጥረው? አንድ ቀን ብቻ እኮ አይደለም። ብዙ ቀን እየተመላለሱ "ካርዳችሁን አውጡ" እያሉ ህዝቡን ሲደበድቡ ታይተዋል።
በምርጫው አዋጅ ላይ "ለምርጫው ለምን አልተመዘገብክም?" እያሉ ሰውን መደብደብ አለ እንዴ? "ይህ ሰው አልተመዘገበም" እያሉ ለአንድ ሳምንት ሰውን ማሰርስ አለ? የምዝገባው ጊዜ ካለፈ ከወር በኋላ የምርጫ ካርዱን በጅምላ እየመዠረጡ ማደልስ ይፈቀዳል? "ከቀበሌ ምንም አታገኙም" እያሉ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖቻችን ከሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ዘይትና ስኳር የሚገዙበትን ካርድ መንጠቅስ በምርጫው ህግ ውስጥ አለን?

በምርጫው ዋዜማ ተራ የአካባቢ ሚሊሻ አባል እና የቀበሌ ታጣቂ ከፍተኛ ስልጣን ተሰጥቶት ህዝቡን ሲደበድብ፣ ሲያስርና ገንዘቡን ሲዘርፍ ነበር። በደርግና በወያኔ ዘመን ያልተሰራ ግፍ ነው በህዝቡ ላይ ሲፈጸም የነበረው (እኛ ከልምድ እንደምናውቀው ፖሊስና ታጣቂ በምርጫ ሰሞን ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ጨዋ ይሆናሉ)።
ያየነውን እና የደረሰብንን ሁሉ መናገርና መጻፍ እንችላለን። ነገር ግን በዚህ ጊዜ አስፈላጊ አይደለም ብለን በዝምታ ለመገዛት ቁጭ ብለናል።
----
እናንተ የዘመኑ የምድር ጌቶች ሆይ!!
በእናንተ ነገር ብዙ ቆስለናል። እኛ ደካማ በመሆናችን በጉልበት ልትገዙን ቆርጣችሁ ተነስታችኋል። ያው አላህ እስከቆረጠላችሁ ቀን ድረስ ትገዛላችሁ። እርሱ "ተነሱ" ሲላችሁ ደግሞ መነሳታችሁ አይቀርም።
እስከዚያ ድረስ ግን ጸጥ ብላችሁ ብትገዙን ይመረጣል። "እንዲህ ዓይነት ፍትሐዊ ምርጫ ተደርጎ አያውቅም" እያላችሁ ሌላ ተዐብ መዘምዘማችሁን አቁሙልን። ቅጥፈትም ዓይነት አለው እኮ። እንዴ????!!!
----
በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተጭበረበረና ፍትሐዊ ምርጫ ይካሄድ የነበረው በየትኛው ዘመን እንደሆነ ታውቃላችሁ? በኃይለ ሥላሴ ዘመን ነው። በዚያን ጊዜ ተመራጮቹ የህግ መምሪያ አባል ለመሆን ነው የሚፎካከሩት እንጂ መሪ ለመቀየር አይደለም። በህገ-መንግሥቱ መሠረት ንጉሡ የሚሻረው ሲሞት ብቻ ነው። የፓርላማ አባል የሚመረጠው አጼ ኃይለ ሥላሴን በስራ ለማገዝ እንጂ ከወንበሩ ለማንሳት አይደለም። በመሆኑም የምርጫ ፉክክሩም ሆነ ሂደቱ ነፃ፣ ሰላማዊና ያልተጭበረበረ ነበር።

በዘመናችን ካየናቸው ምርጫዎች መካከል በተሻለ ሁኔታ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ የነበረው ምርጫ 97 ነበር። የምርጫው አጨራረስ ቢበላሽም ፉክክሩ ማንንም ቁጭ ብድግ ያሰኘ እንደነበረ ሁሉም ሰው ይመሰክራል።

የአሁኑ ምርጫ በቱርኪሜኒስታን እና ኡዝቤክስታን ከተካሄዱት አስቂኝ ምርጫዎች ጋር ነው የሚመሳሰለው። የአል-ሲሲ እና የሳዳም ሁሴን ምርጫዎች እንኳ ከዚህ ይሻላሉ።
----
በመጨረሻም

ፈጣሪ ለጊዜው ጉልበት ሰጥቶአችሁ ሀገሪቷን እንድትገዙ ፈቅዶላችኋል። ስለዚህ ህዝቡን ዝም ብላችሁ ግዙት ("አገዛዝ" እንጂ "አስተዳደር" በኢትዮጵያ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ አልታየም)። ሀንጀባ፣ ግርግር፣ ሲመት፣ ሹመት፣ ሀራኪሪ፣ ካሚካዚ እያላችሁ ሀተታ አታብዙብን።
-----
Please wait, video is loading...