By Abraha Desta
==========
በጦርነቱ ምክንያት የብዙ ወጣቶች ህይወት እየተቀጠፈ ነው። ንብረት እየወደመ ነው። ረሃቡ፣ መፈናቀሉ አለ። የሀገር ኢኮኖሚ እየተሽመደመደ ነው። የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ አጀንዳ ሆነናል። ጦርነቱ ከቀጠለ ችግሮቹ ተባብሰው ይቀጥላሉ። ከቆመ ይቆማሉ።
ሁሉም ወገን ጦርነቱ እንዲቆም ይፈልጋል። የፌደራል መንግስት፣ ህወሓት፣ ተጋሩን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ጦርነቱ እንዲቆም ይፈልጋሉ። ልዩነቱ "እንዴት" ላይ ነው።
የፌደራል መንግስትና ደጋፊዎቹ "ፀረ ኢትዮጵያ" ያሉትን ህወሓትን ቶሎ "አጥፍተው" ጦርነቱ እንዲቆም ይፈልጋሉ። ህወሓትና ደጋፊዎቹ "ፀረ ትግራይ" ያሉዋቸውን ሐይሎችን ቶሎ "ደምስሰው" ጦርነቱ እንዲቆም ይፈልጋሉ። ጠላትን ለማጥፋትና ለመደምሰስ ግዜ እንደሚወስድና ሌሎችን ለማጥፋት ስትሄድ ራስን መጥፋት እንዳለ፣ ሌሎችን ለመደምሰስ ስትመጣ ራስን መደምሰስ እንደሚኖር አይረዱም። ጠላትህ ማጥፋት ስለፈለክ ብቻ አታጠፋውም። ለማሸነፍ ስትነሳ (1) ጦርነቱ ይቀጥላል፤ ችግሩም አብሮ ይቀጥላል። (2) ልትሸነፍም ትችላለህ።
አሁን ምን ሊፈጠር ይችላል?
(1) ፌደራል መንግስት አሸንፎ መቀለ ይገባል?
(2) ህወሓት አሸንፎ አዲስ አበባ ይገባል?
(3) ሁለቱም ይሸነፋሉ? ወይም አይሸናነፉም?
(4) ሁለቱም ያሸንፋሉ፤ ጦርነቱ ተቋርጦ ድርድር ይጀመራል?
(1) የፌደራል መንግስት በጦርነት እንዲያሸንፍ (ሀ) ጦርነቱ ይቀጥላል፤ ጦርነቱ ከቀጠለ ሞቱ፣ ውድመቱ፣ ረሀቡ፣ መፈናቀሉ ይቀጥላል። ይህን ሁሉ ከቀጠለ ምን ማሸነፍ ይባላል? (ለ) መቀለ ገብቶ ማንን ያስተዳድራል? ማንስ ይቀበለዋል? መቀለ እስኪገባ ድረስ የሚኖር እልቂት አስባችሁታል? መከላከያ መቀለ ስለገባ ጦርነቱ ሊቆም ይችላልን? በፍፁም ጦርነት ሊቆም አይችልም!
(2) ህወሓት ቢያሸንፍ (ሀ) እስኪያሸንፍ ስንት ግዜ ጦርነት ያካሂዳል? ጦርነቱ ብዙ ግዜ ይወስዳል። ሞቱ፣ መፈናቀሉ ወዘተ ተባብሶ ይቀጥላል። ህወሓት አዲስ አበባ እስኪደርስ የትግራይ ህዝብ በረሀብ አያልቅም? ህዝብ በረሀብ ካለቀ ጦርነት አሸነፍኩ ይባላል? (ለ) ህወሓት አዲስ አበባ መጥቶስ የአዲስ አበባ ህዝብ ይቀበለዋል? ሰላም ይኖራል? በፍፁም ሰላም አይኖርም!
በመሸናነፍ ሰላም አይኖርም፤ ጦርነቱም አይቆምም።
(3) ሁለቱም ወገኖች ባይሸናነፉስ? ወይም ሁለቱም ቢሸነፉስ? ሁሉም ተገዳድለው ሐይላቸው ጨርሰው ተዳክመው ቢቆሙስ? ሁለቱም ዓቅማቸው እስኪጨርሱ ድረስ ከተዋጉ (ሀ) ጦርነቱ ብዙ ግዜ ቆየ ማለት አይደል? እናም ብዙ ውድመትና እልቂት ይደርሳል። ብዙ ችግር ከደረሰ መጨረሻ ጦርነቱ ቢቆም ምን ዋጋ አለው? (ለ) ሁለቱም ከተሸነፉ ሀገራችንና ህዝባችን መንግስት አልባ ሆነ ማለት አይደል? እንደ ሀገረ ሶማልያ ሆንን ማለት ኮ ነው።
ጦርነቱ ከቀጠለ አሸናፊ አይኖርም።
(4) ልዩነታቸው በድርድር ለመፍታት ቢስማሙስ? ሁለቱም ወገኖች አሸነፉ ማለት አይደል? ለመደራደር ፍቃደኛ ሆነው ሁለቱም አሸናፊ ቢሆኑ (ሀ) ጦርነቱ ቶሎ ይቆማል። እልቂቱና ውድመቱ ይቆማል። የተፈናቀሉ ወደየቀያቸው ይመለሳሉ፤ የተራቡ ይመገባሉ። ሀገርና ህዝብ ከውድቀት ይድናል። (ለ) ሁለቱም ሲያሸንፉ የጦርነቱ ተሸናፊ ስለማይኖር ከቀጣይ የጦርነት አዙሪት እንወጣለን። አሸናፊው አንድ ሲሆን ሌላኛው ተሸናፊ ይሆናል። ተሸናፊ ካለ በቀጣይ ለበቀል ስለሚዘጋጅ ሌላ ዙር ጦርነት መኖሩ አይቀርም!
ከቀጣይ የጦርነት አዙሪት የሚያስወጣ፣ ሁለቱም አሸናፊ የሚያደርግ እና ጦርነቱን ቶሎ ሚያስቆም እንደውጤቱም ህዝባችንና ሀገራችንን ምናድንበት መንገድ ድርድር ነው። በጦርነቱ የአንድ ወገን አሸናፊ አይኖርም፤ መኖርም የለበትም!
ድርድር አስፈላጊ ቢሆንም ድርድር ስላልን ብቻ ድርድር ሊሳካ ይችላል ወይ? ድርድር እንዲሳካ ቢያንስ ሁለት ነገሮች ያስፈልጉናል።
(1) ሁለቱም ወገኖች ስቶልሜት ወይ ዴድሎክ ደረጃ ላይ መድረስ አለባቸው። መፈታተሽ ይኖርባቸዋል። ሁለቱም ወይ አንዱ "አሸንፋለሁ" የሚል እምነት ካለው ድርድር አይሳካም። ለድርድር እንዲቀርቡ ሁለቱም ተመጣጣኝ ዓቅም ሊኖራቸው ይገባል። አሸንፋለሁ ብቻ ሳይሆን ልሸነፍ እችላለሁ ም ብለው የሚያስቡበት ደረጃ መድረስ አለባቸው። አስታውሱ፦ በግ እና አንበሳ ሊደራደሩ አይችሉም።
አሁን ዴድሎክ ላይ ናቸው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ የማደራደር ዕድሉ አሁን ነው። መከላከያ መቀለ ከገባ ወይም ህወሓት ወደ አዲስ አበባ ከመረሸ ድርድሩ አይሳካም ወይም ጤናማ ድርድር አይሆነም።
(2) ሁለቱም ወገኖች ዴድሎክ አጋጥሟቸውም የቲፎዞ ነገር ካለ ድርድሩ ላይሳካ ይችላል። ሁለት ሰዎች ተጣልተው እየተደባደቡ ሳለ ገላጋይ ገብቶ ሊለያያቸውና ሊሸመግላቸው ወይ ሊያስታርቃቸው ይችላል። ፀቡ በሁለቱም ወገን ብዙ ሰው (ቲፎዞ) ያካተተ ከሆነና ገላጋዮቹ ከፀበኞቹ ያነሰ ቁጥር ቢኖራቸውስ? ጭራሽ ሰላም ወዳድ ገላጋዮቹ እንደ "መሃል ሠፋሪ" ቢታዩና ባይሳካስ? ከፀቦኞቹ ጎን የተሰለፈ ብዙ አጨብጫቢ ቲፎዞ ቢኖርስ? ፀበኞቹ ዴድሎክ ላይ ሆኖውም በአጨብጫቢዎች ቅስቀሳ ሼም ይዟቸው ህይወታቸው እስኪያልፍ ሊደባደቡ ይችላሉ።
ስዚህ ጦርነቱ ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን የገላጋይ ቁጥር ከፀበኞች ቁጥር እንዲበልጥ የሰላም ሙቭመንት መጀመር ይኖርብናል። ሰላም ወዳዶች አናሳ ሆነናል።
ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ የሚሆኑበት የድርድር መንገድ እንዲከተሉ ግፊት እናድርግ!
ሰላም!
Please wait, video is loading...