እንቁጣጣሽ የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? በእኔ ግምት 99 ነጥብ 9999% የሚሰጠው መልስ የዕንቁ ጣጣ፣ የዕንቁ ችግር፣ ለሴት የሚሰጥ ዕንቁ ችግር ወይም ጣጣ ነው የሚል ነው ። ማለትም በዚህ የተሳሳተ ትርጉም መሰረት ቃሉ ሁለት ክፍል አለው ማለት ነው፤ ዕንቁ ና ጣጣ። ይህ ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ።
የመጀመሪያ ግዙፍ ስህተቱ ዘመን መለወጫ ወይም ቅዱስ ዮሃንስ፣ አዲስ አመት ወይም አክራሚ ለሴቶች ዕንቁ ወይም ጌጣጌጥ የሚሰጥበት በዓል አይደለም ። የጋብቻም፣ የፍጥምጥም ቀን አይደለም። ስለዚህ ትርጓሜውን የሚደግፍ ማህበራዊ ባህል ወይም ፕራክቲስ የለም ።
ለሌላው ግዙፍ ስህተት እንቁጣጣሽ ፣ ጣጣ፣ መከራ፣ ችግር፣ ወዘተ የሚከሰትበት ቀን አይደለም። እንዲሁ ቃሉ የዕንቁና ጣጣ መድብል ሳሆን አንድ የነገር ስም ነው ። ትክክለኛው ትርጉም እነሆ።
እንቁጣጣሽ የአደይ አበባ ስጦታ መለዋወጫ ቀን ነው። የአደይ አበባ ከረምት አብቅቶ የጸደይ፣ የጸዳ የብርሃን፣ የብራ ወራት መጀመሪያ የሚያበስር የኢትዮጵያን ምድር በውበት የሚሸፍን አበባ ነው ። የአደይ አበባ ባለበት ቦታ ከቤት ቤት፣ ከሰው ሰው የሚደረገው እንኩ ፣ እንኩ አበባ ነው ። አበባ በሌለበት ልጆች አበባ በወረቀት ላይ በመሳል ከቤት ቤትና ከሰው ሰው እንኩ፣ እንኩ እያሉ የሚሰጡት አበባ ነው። ይህ ነው የአዲስ አመት እለት ባህል!
ስለዚህ እንቁጣጣሽ ድሮ እንኩታታ ይባል ነበር። እንኩታታ አንድ ቃል ሲሆን እንኩ የሚለው የስጦታ ቃል ወይም ስጦታ መለዋወጥን አመልካች የሂደት ስም ነው። እንኩታታ ማለት ስጦታ መለዋወጥ ማለት ነው ። ይህን እንካ፣ እንኩ፣ እንኩታ፣ እንኩታታ ይባል የነበረውን ቃል ነው በተለምዶ እንቁ፣ እንቁጣ፣ እንቁጣጣ ተብሎ የተበላሸው ።
በአክብሮት አነጋገር እንኩህ ፣ እንኩሽ ይባል ነበር ። ከዚያ ተያይዞ ነው የመጨረሻው ሸ ታክሎበት እንቁጣጣሽ የሆነው ። በአንድ ቃል እንቁጣጣሽ በአደይ አበባ ስጦታ መለዋውጥ የሚከበር እጅግ ታላቁ የደስታ ቀን ነው ።
እንቁጣጣሽ እጅግ ወብ የሆነ ምናልባትም ያበባ ስጦታ ከቤት ቤት የሚሰጡ ልጆችና ልጃገረዶች ሲዘፍኑ የፈጠሩት ውብ ቃል ነው። ትርጉሙ ግን የአደይ አበባ እንጂ የሴት እንቁ አይደለም ። ለዚህ ነው በእንቁጣጣሽ ለሴቶቻችን እንቁ ለመግዛት የማንጨነቀው ። በዓሉም የመላ ቤተሰብ እንጂ የሴቶ ብቻ በዓል አይደለም፤ ለምሳሌ እንደ ቫለንታይን ፣ የናቶች ቀን ወይም እንደ አዳብና የጎረምሶች መተጫጫ ቀን ማለት ነው !
ውብና የኬር እንቁጣጣሽ ለመላው ውብ የኢትዮጵያ ዘር ሁሉ !!!