Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 11594
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

የአዲስ አበቤው የዛሬ ውሎ ( ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም )

Post by sarcasm » 08 Aug 2021, 18:40

የአዲስ አበቤው የዛሬ ውሎ
ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም
ዛሬስ ገና የቤታችንን ግቢ ሳልለቅ ነው፤ የአዲስ አበቤ አጀንዳ እግር ተወርች የያዘኝ:: ጡረተኛው አባየ ነው፤ ሸበቶ ጢሙን እያፍተለተለ፤ የዘወትር የጥዋት ፀሓይ መሞቂያ ወንበሩ ላይ ተኮፍሶ፤ የሆነ ሬድዮ ይጎረጉራል:: ሲያቀብጠኝ ነገር የጀመርኩት እኔው እራሴ ነኝ፤ "አባየ የምን ሬድዮ እያፈላለግክ ነው፤ ጁንታው ሬድዮ ጀመረ እንዴ?" አልኩት:: እንደቢጤዎቹ የ1950 እና 1960ዎቹ ትውልዶች፤ "ፖለቲካ ጦርነት" የሚሉ ወሬዎችን ማነፍነፍ ይወዳል::

"...ምን ባክህ ዝም ብየ ነው፤ ህዝቡ ላሊበላ፣ ወልድያ፣ ንፋስ መውጫ፣ ሰመራ ሲል፤ በትውስታ 36 ዓመታት ወደኋላ ነጎድኩ" ኣለኝና ትረካውን ቀጠለ:: እራሴው የክምር ስር እሳት ቆስቁሸ መች ሊለቀኝ:: ደግሞም ጨዋታውን አቋርጦት የሚሄድ አይደለም፤ ቀልቡን ሰብሰብ አድርጎ በጥሞና የማያዳምጠው ሰውም ኣይወድም፤ ደሙ ነው የሚፈላው:: በግዴ የግቢያችንን ዛፍ ተደግፌ ማዳመጥ ጀመርኩ::

"...በ1977 ድርቅ የማውቃቸው የሰሜን ቦታዎች እነ ባራት፣ መቄት፣ አርቢት፣ ገርገራ፣ ፍላቂት፣ ደብረዘይት፣ እያለ በጋይንት ምድር በጨጨሆ መድሃኒዓለም አድርጎ እስከ ንፋስ መውጫ ይዘልቃል" ብሎ ጀመረ::

"...ከወዲህም መስቀለኛዋን ጋሸና ከተማ መሃል አስፍሮ ዙሪያዋን በላሊበላ፣ በመቅደላ፣ በወገልጤና፣ በአምባሰል ተራራዎች ተከባለች:: የሁሉም ማስተሳሰሪያ ጋሸና ነች:: በዚያ አስከፊ የረሓብ ወቅት ለዕርዳታ ስራ በእነዚህ አካባቢዎች ተመላልሸባቸው ስለነበር፤ በርካታ ትውስታዎች አሉኝ:: የሕዝቡ ጥንካሬ ታታሪነት አልበገር ባይነት ግን ለየት ያለ ነበር::

"...እነዚህን አካባቢዎች አስተሳስሮ አቆራርጦ፣ ከወልድያ ወደ ደብረታቦር ወሮታ የሚዘልቀው ኣስፋልት፤ ከዚያ የድርቅ ወቅት በፊት በቻይናዎች የተገነባ ገደላገደል የበዛበት መንገድ ነው:: ከንፋስ መውጫ በኋላ ወደ ደብረታቦር ወረታ ያለው መንገድ እንኳን ገደላማውን ምድር ካለፍክ በኋላ ስለሆነ የተሻለ ነው:: ርቀቱም ያን ያህል ነው፤ ኣስፋልት ይዞ ለሚዘዋወር ባለመኺና ከመቶ ሃያ ኪሎሚትር ስትሆን፤ ለእግረኛው እያቆራረጠ ሰማንያም አትሆንም..." እያለ በህሊና ሲያስጎበኘኝ፤ "ኣባየ ይቅርታ የስራ ሰዓት ደረሰብኝ" ብየ ግንባሩ ላይ ስሜ አፈተለኩ::

የአባየን የ36 ዓመታት የሰሜን ትውስታ እያላመጥኩ ፤ ከታኪሲ ታክሲ እየተገላበጥኩ፤ የተሳፋሪውን ሁለገብ አገራዊ የጭንቅ፣ የመከራ፣ የጦርነት ዕልቂት፣ የኑሮ ውድነት፣ የአገር ክህደት መፍረስና መበታተን፣ ወሬ እያዳመጥኩ፤ መስሪያቤት ደረስኩ:: አባየ በጥዋቱ በስብሰባ ለክፎኛል ልበል፤ አስቸኳይ የሰራተኛው ሁሉ ስብሰባ ተጠርቷል::

አዳራሽ ለስብሰባ ተብሎ ከገባን ይኸው እንደተጣድን አራት ሰዓት ሞላን:: ማን ሊለቀን፤ ሊለቁን አልቻሉም "መግባት ቀላል ይሆናል መውጣት ግን ኣይቻልም" ያለው ጁንታው ለስብሰባም ነበር እንዴ? ብዬ ገና ከማሰቤ፤ ሰብሳቢው ሰውዬ፤ "ጁንታው" ሲል፤ ያሰበኩትን የሰማኝ መስሎኝ ዓይኔ ፈጠጠ:: እነዚህ ሰዎች እኮ ከስቺዌሽን ክፍላቸው ሁነው ማን ምን ያስባል? ምን እያደረገ ነው? ብለዉ እየተመለከቱን ይሆናል::
ስብሰባው "ለኢትዮጵያችን የትም! መቼም! በምን" የሚል አሰልቺና በድግግሞሽ የታጀበ ስብሰባ ሲሆን፤ በዚያ ላይ ደግሞ የሰብሳቢው ፉከራና ስድብ አይጣል ነው:: "በዚህ የህልውና ዘመቻ፤ ገንዘብ ያላዋጣና አገራዊ ጥሪ ያልተቀበለ፤ ከጁንታው ለይተን አናየውም!" ብሎ፤ በዛ በሲጋራና አልኮል በበለዘ ዓይኑ ደጋግሞ አጉረጠረጠብን!

ከአጠገቤ ያለው ባልደረባዬ የሰውዬውን ዛቻና ስድብ ተመልክቶ፤ "አረ!" ኣለ:: "እነዚህ ሰዎች ከዛ ሲገርፏቸው ጊዜ እኛን ምን አድርጉ ነው የሚሉን! መንግስትና ተሳፋሪ ሊወርዱ ሲሉ፤ ስድብ ስድብ ይላቸዋል" አለ አንገቱን እንዳቀረቀረ::

"አረ ዝም በል! እዛ ማንም የገረፋቸው የለም:: በራሳችን ጊዜ ነው ለታክቲክ የወጣነው፤ ጁንታውን ወደ መሃል አገር ስበን ካስገባነው በኋላ ከበን እናነጋግረዋለን ብለዋል" ስለዉ፤ አቋረጠኝ::

"እዚህ አፍንጫችን ስር እስኪደርሱ ነው የምትጠብቁት! ከዛ አምባሳደር ሲኒማ ጋር ሲደርሱ እናንተ በፒያሳ በአራት ኪሎና በቄራ በኩል ከባቹ ልታነጋግሯቸው! አይደል!" አሾፈብኝ:: “አረ አንተዬ በቃ ዝም በል!ሰውየው ወደእኛ አካባቢ እያማተረ ነው” ስለዉ ባሰበት:: ጥሩነቱ ከኋላ ጥግ ይዘን መቀመጣችን በጀን::
"ምነው እፍረት የሚባለው ነገር ጠፋ! ውሸት ዓይን አውጣነት ድርቅና፤ በአገር ሙሉ አንሰራፋ፤ ስሩም ሰፋ" እያለ ቀጠለ::

"እልቅ ስለአከራየ ልንገርህ" አለኝ:: መቸም ዘንድሮ የሚበላው ስለተወደደ ወሬ ማላመጥና ማጣጣም ላይ በርትተናል፤ ተመስጨ አንዱን ጆሮየን ሰጠሁት::
"እንደ ገዱ አንዳርጋቸውና ልደቱ አያሌው የትውልድ ቀያቸው በጁንታው የተያዘባቸው አከራየ፤ ትናንት ማታ ገፅታቸው ተለዋውጦ አካኪ ዘራፍ ሲሉ አምሽተው፤ ጥዋት ስነሳ እግቢው ውስጥ ዘና ብለው አየኋቸውና፤ ፈራተባ እያልኩ፤ 'ደሕና አደሩ ጋሸ' አልኳቸው::

"...ፈጣሪ ይመስገንም አላሉኝም፤ በተቀመጡበት እግራቸው መሬቱን እያንኳኳ፤ "ተወኝ እስቲ! ቅቤው ጉድ ሰራን" አሉኝ:: የእኔ ነገር አፌ አልያዝ እያለ ይፈጥንብኛል:: "ምን ለፍልሰታ ቅበላ ቅቤ ተገዝቶ ነው? ሰው እንኳንስ ቅቤ ለመብላት ለማየትም ዋጋው አይነካም እያለ ነበር" ከማለቴ፤
"አንተ ደግሞ ሁሌ አራምባና ቆቦ ትዘባርቃለህ" ብለው ገሰፁኝ:: እንኳንም አስቆሙኝ:: በ10ሺ ብርም ስለማይገኘው አንድ ኩንታል ጤፍ፤ ኢምፖርት ተደርጎ ነው መባል ስለደረሰው የኛው ድሮ ስለምናውቀው በርበሬም ልተርክ ነበር:: አከራየ ምን እንደሚሉ ሳይገባኝ፤ ብልፅግናዎች በይሆናል አገር እንመራለን እንደሚሉት፤ እኔም የውስጤን ለቀቅኩት::

"...ጋሸ ገስፀው እንዳስቆሙኝ ቀጠሉበት፤ "አያሌው ሞኙ፣ ሰው አማኙ፣ ሰው አማኙ"እያሉ ያቀነቅኑ ጀመር። "አንተየ አገር ቤት ካሉት ዘመዶቻችን በወሬ ወሬ ጉዳችንን ሰማነው:: አብይ ቅቤው እየተጫወተብን ነው! ትግሪዎቹ ቅቤው እንደሚያጠለሻቸው ሳይሆን፤ በገቡበት ዘራፊውን እየቀጡ፤ ሰላሙን እያረጋጉ፤ የሰው ንብረት አይነኩ፤ አገሬውንም ካልነካቸው አይነኩት ከነጠብመንጃው ወደ እርሻህ ዝለቅ፤ አካባቢህን እራስህ እያስተዳደርክ በሰላም ኑር ብለውታል" እያለ ይተርካል::
የእሱ ትረካ ሳይቋጭ ሌላው ከጎኔ ያለው የሰው ሃይል አስተዳደር ለጠቅ አደረገና፤ "ይህ ስብሰባ፤ ለመፈክር ነው ወይንስ፤ አሁን ይሄ ሰራተኛ ወደ ዘመቻ ይከታል ብለው ነው? አሁን ማን ይሙት፤ ለግምገማ ተሰብሰብ ስትለው 'አበል አለው ወይ?' የሚል ህዝብ እኮ ነው" በማለት ጥያቄውንም መልሱንም እራሱ ዘጋው::
እኔም የሰብሳቢውንና የእኛ የተሰብሳቢዎችን የዓላማም የግብም አለመገናኘት እያሰብኩ እየገረመኝ ሳለ፤ አንዱ ባልደረባችን፤ "ሰላሳ ሶስት... ሰላሳ አራት..." እያለ በለሆሳስ ሲያጉተመትም ሰማሁት:: ግር ብሎኘ ብጠይቀው፤ "ሰብሳቢው ስንት ጊዜ ጁንታ እንዳለ እየቆጠርኩኘ ነው" አለኝ:: "ምን ሊያደርግልህ" ብለው፤ "ስንተኛው ላይ ሲደርስ ስብሰባውን እንደሚቋጨው ለማወቅ፤ ለጠቅላላ እውቀት" አላለኝም!

"ኦሆ! ስራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል" ተብሏል እኮ ስለዉ፤ "ይልቅ አስጠፋኸኝ፤ አሁን 37ኛ ነው 38 ኛ" ከማለቱ፤ ከፊታችን ስብሰባውን በንቃት የሚከታተለውና አንገቱን እያወዛወዘ አንዳንድ ነጥቦችን በማስታወሻ የሚመዘግበው ተሳታፊ፤ ፊቱን አኮሳትሮ ወደእኛ ዞር ብሎ፤ "ትቀልዳላቹ እንዴ! አርባ ሶስት ላይ ደርሷል" ብሎት እርፍ። እንደማስታወሻ አያያዙ የበለፀገ ነበር የሚመስለው::

ሰብሳቢውም አሰልቺ ንግግሩን ቀጠሏል፤ "ህብረተሰቡ በፌስቡክ ወሬዎች እንዳይታለል! የህግ ማስከበሩ ሂደት ጁንታው እስኪደመሰስ ተጠናክሮ ይቀጥላል! መንግስት ከአሸባሪ ቡድን ጋር አይደራደርም! አሸባሪው ከሚያሰራጨው የሃሰት መረጃ ተጠንቀቁ..." ይላል::

ይህን ንግግር እንዳዳመጥኩ፤ ከፊት ለፊታችን ያለው ባለማስታወሻው ባልደረባችን ምን እንደሚፅፍ ገርሞኝ፤ አንገቴን አስግጌ ማስታወሻውን ብመለከት፤ "እኔ እኮ እነዚህ ሰዎች ያስቁኛል። እንዴት አድርገው ቢያስቡንና ቢንቁን ነው? እኛ እኮ መረጃውን የምንሰማው በጦርነቱ መከራውን እያየ ካለው ህዝብና ሰራዊት ነው" ይላል::
እንዳያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ! አሰልቺው ስብሰባም ተቋጨ! በግዴታ የአንድ ወር ደመወዛችንን ለጦርነት እንድንቀማ ተስማምተን ወጣን:: ተሰብሳቢው አዲስ አበቤ፤ በውስጡ የሚንቀለቀለው ንዴት ፊቱን አቅልቶታል ብቻም ሳይሆን፤ ኣፍሞታል:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ ካለ ሕዝብ ጋር ወሬ መጀመር፤ መቋጫው አያምርም ብዬ፤ ዝምታን ተከናንቤ ወደ ቤት አቀናሁ::

አዲስ አበቤው ነኝ፤ የነገ ሰው ይበለን!
Please wait, video is loading...