የዛሬ ሰልፍ ምን ፋይዳ አለው? ምን ትርጉም አለው? በሰሚና ተመልካች ልብና አንጎል ውስጥ ምን አይነት ሃሳብና ስሜት ይቀሰቅሳል? መልሱ ብዙ ነው።
አንድ፣ የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ስሜት ላይ የአድዋን ንቃተ ህሊና ይጭራል። የኢትዮጵያዊያን ነጻ ሕዝብነት መለኪያ ፓራድይሙ አድዋ ነው ። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ወጣት ትውልድ የሚበቅለው እንደዚህ ነው፣ በችግር ግዜ፣ በለውጥ ግዜ፣ በጦርነት ግዜ ማለት ነው ።
ሁለት፣ ላይ ላዩን ብቻ ላየው ሰው ይህ ሰልፍ የአሜሪካን ሃሳብ ለማስለወጥ የተደረገ ቢመስልም ትልቁ ትልቁ መልዕክት ኢትዮጵያ የዘመናችን ፓን አፍሪካን ንቅናቄ ያወጀችበት ቀን ሆኖ ሊታሰብ ይችላል ። ኢትዮጵያ ጣሊያንን በጦር እምቢ ብላ አፍሪካን በነጭ ከመወሰድ አድናለች ። ዛሬ ደሞ የገነነውን የኢኮኖሚና ካልቸር ቅኝ ግዛት እምቢ ብላ ግዙፍ የሆነ ያፍሪካ ወጣት ትውልድ መሪነት ለኩሳለች ።
በባይደን አስተዳደር ላይ ኢትዮጵያ ያነሳቸው ቅዋሜና የሕዝብ ንቅናቄ የፓን አፍሪካ አጀንዳ ማወጃ ነው። ኢትዮጵያ ባፍሪካ አንድነት፣ በአፍሪካ አገሮች፣ በአፍሪካ ወጣት መሃልና ዘንድ ይህን የዘመናችን ከጅ አዙር ቅኝ ተገዥነት ጉዳይ ማንሳት አለባት ። ትልቁ ዲፕሎማሲ ፈረንጅ መለመን ሳይሆን አፍሪካን ማደራጀትና መምራት ነው ።
ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል ይባላል! አፍሪካ የአለም 5ኛ ሃያል አህጉር ናት ። ኢትዮጵያ ይህን ግዙፍ ሃልይ መቀስቀስ፣ ማስነሳት፣ ማስተባበና መምራት የዘመኑ ተልዕኮዋ ነው ። ይህ ሁሉ ዳግማዊ አድዋ ነው ።
ያገባኛል የሚል የሕዝቡን መፈክሮች በማጥናት ያገሪቱ ፖለቲካ ግንዛቤ ምን ላይ እንደ ሆነ መለካት ይችላል። አሁን ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቱርክ፣ እና ሌሎች ባፍሪካ ቀን ፖልቲካ ሙሉ በሙሉ እንዲገቡ ተጋብዘዋል። አሜርካ አፍሪካን ብቻውን እንደ ማይገዛ ተነግሮታል ። ጥቅሙን የሚያውቅ ሃይል ስለሆነ የሚመቸውን ፖሊሲ መያዝ ይችላል ። በዕቀባ ኢትዮጵያን ማንበርከክ እንደ ማይቻል ግን ተነግሮታል ። ስንዴ ለመሰፈር የሚበረከክ ሕዝብ በህይወት መኖሩ ፋይዳ የለውም ።
ይህ ነው ነጻ ሕዝብ የመሆን ትርጉም ! ያ ደሞ የኢትዮጵያ ጂን የተሰራበት ህዋስ ስለሆነ!
በአንድ ቃል ኢትዮጵያዊያን ከአሜርካ ስንዴ ሱስ ነጻ ሆነው ለረጅም የምዕራብ እቀባ ተዘጋጅተው የራሳቸው ሕይወት በራሳቸው ለማሸነፍ መትጊያ ዘመን ደርሰናል! ችግር ፈጠራን ያስተምራል! ፈተና ጀግንነትን ይወልዳል ።
ሌላ ቦታ እንዳልኩት የአሜሪካ ጠላትነት አግዚአብሄር ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ያዘነበው በረክት ነው !