"የሕወሓት ፖሊሲዎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ምስቅልቅል ውስጥ የከተቱ ነበሩ"፦ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ
******************
(ኢ.ፕ.ድ)
ሕወሓት ሲጠቀምባቸው የነበሩ ፖሊሲዎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ምስቅልቅ ውስጥ የከተቱ እንደነበሩ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ተናገሩ።
ፖሊሲዎቹ ለሥራ እጦት፣ ለዋጋ ግሽበት እና አካታች ላልሆነ የዕድገት መጠን ሀገሪቷን የዳረጉ መሆናቸውን ነው አምባሳደር ጊታ የገለጹት።
አምባሳደሯ በቅርቡ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በኢትዮጵያ ያለው የመሬት ፖሊሲ አርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት የነፈገ ነውም ብለዋል።
በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት ጁንታ መካከል የተካሄደውን ግጭት በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ደግሞ፣ "ጦርነቱ በሕወሓት ጁንታ ቀስቃሽነት የተጀመረ ነው፤ የሕወሓት ቡድን ከሁለት አሥርት ዓመታት ተኩል በላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ በብቸኝነት ተቆጣጥሮ ነበር" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት እና ኢኮኖሚውን ክፍት ለማድረግ ቃል መግባታቸውን የገለጹት አምባሳደር ጊታ፣ "እንደዚህ ዓይነቱን የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር የአማካይ ኢትዮጵያውያንን አኗኗር ለማሻሻል የሚረዳ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የወጠኗቸውን ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ የጀመሩትን ሪፎርም አሜሪካ ትደግፋለች" ሲሉም አክለዋል።
ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ውዝግብ በተመለከተ ደግሞ፣ አሜሪካ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ የታዛቢነት ሚናዋን መጫወት እንደምትቀጥል እና ኢትዮጵያ እና ግብፅ ፍሬ የሚያፈራ ውይይት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ እንደምታበረታታ ገልጸዋል።
"እንደዚህ ዓይነቱ ግዙፍ የኃይል እምቅ አቅም ላይ ከስምምንት መድረስ ለሁሉም ሀገራት የአሸናፊነት አካሄድ ይሆናል" ሲሉ ነው የገለጹት።
"እኛ ከሌሎች ሰላም ወዳድ ሀገራት ጋር በመሆን ኢትዮጵያ እና ግብፅ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መግፋታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል አምባሳደር ጊታ።