በትግራይ ክልል ከተማ ይሁን በገጠር ውስጥ ጦርነት በመካሄዱ የሰብዓዊ ችግሩ ሁሉንም አካባቢ እንዳካለለ ኣቶ ኣብርሃ ደስታ ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ ትግራይ የገጠማት ችግር በዘመኗ ገጥሟት የማያውቅ ችግር ነውም ብለዋል።
ቢሯቸው ባደረገው ዳሰሰ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልፀዋል።
ኣቶ ኣብርሃ ፥ "..የትግራይ ህዝብ ተፈናቅሏል፤ አብዛኛው ንብረቱ ተዘርፏል፤ ተወስዷል፤ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል፤ አብዛኛው ሰው የአስቸኳይ እርዳታ ያስፈልገዋል፤ በተደረገው ዳሰሳ 4.5 ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልገዋል፤ ከዚህም 2.2 ሚሊዮን ህዝብ ምግብ ብቻ ሳይሆን የምግብ መስሪያም የሌለው ሆኗል፤ ስለዚህ አስቸኳይ እርዳታው ሁለንተናዊ ነው" ብለዋል።
እንደ ኣቶ ኣብርሃ ገለፃ በክልሉ አስፈላጊ የእርዳታ ምግብ አለ ነገር ግን ለማጓጓዝ የፀጥታ ስጋት አለ ፤ አሽከርካሪዎች ይሰጋሉ፤ መንግስታዊ መዋቅርም በመፍረሱ እርዳታውን ለማድረስ ኣስቸጋሪ ሆኗል።
"በጦርነቱ ሁሉም ነገር ስለተነካ ረሃብ ተከስቷል፤ በእኛ በኩል እህል አለ ለማጓጓዝ መንግስታዊ መዋቅር ያስፈልጋል፤ እሱም ፈርሷል፤ እርዳታው ወደ ህዝቡ እንዲደርስ አልቻለም ተቸግረናል" ብለዋል አቶ ኣብርሃ።
Please wait, video is loading...