መረን የለቀቀ እልህና ድንቁርና በየፊናችን ቀን ከሌሊት ሰብከን በኤርትራ በኩልም ጊዜ ሲጠብቅ የነበረ ለማመን የሚያስቸግር ጥግ አልባ የብቀላ ጥማት ተጨምሮበት የፖለቲካ ልዩነትን በሃይል ለመፍታት በተካሄደ እጅግ አውዳሚ የይዋጣልን አስከፊ ጦርነት ትግራይ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወድማለች።
በውጤቱም፣ በየቀኑ ሴቶች ይደፈራሉ፣ ንፁሃን ሰዎች ይገደላሉ፣ ፋብሪካዎች ሆን ተብሎ ይወድማሉ፣ ገበሬው ምርቱንና ከብቱን አጥቷል፣ ሰዎች በሰላም ወጥተው መግባት አቅቷቸዋል፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት ጨምሮ በከፍተኛ ወጪ የተሰሩ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ወድመዋል፣ የመንግስትና የግለሰብ ጥቃቅን ንብረት ሁሉ በየቀኑ ይዘረፋል። በአጭሩ ህዝብ እያለቀሰ ነው።
ይባስ ብሎም ህግ ለማስከበር ተብሎ በተካሄደ ጦርነት ህግ በአደባባይ ተጥሶ የአማራ ክልል መንግስት ምእራብ ትግራይንና ከፊል ደቡብ ትግራይን ሲቆጣጠር የኤርትራ መንግስትም የአለም አቀፍ ህግ ጭምር በመጣስ የአንዲት ሉአላዊት አገር ድንበር ጥሶ ያለማንም ከልካይ ምስራቅ ትግራይንና ሰሜን ምእራብ ትግራይን በከፊል ተቆጣጥሮ ይገኛል። በዚህም ምክንያት ከሁለት ሚልዮን በላይ ዜጎች ቤት ንብረታቸው ጥለው በየቦታው ተሰደው በችጋር እየተገረፉ ይገኛሉ።
ሲጠቃለል፣ አዲስ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት በቅርቡ በአቀረበው የአስቸኳይ እርዳታ ጥሪ መሰረት በተካሄደው አስከፊ ጦርነት ምክንያት በትንሹ 4.5 ሚልዮን ህዝብ ማለትም 75 ፐርሰንት የትግራይ ህዝብ በላቡ ያፈራውን ንብረት በጠራራ ፀሃይ ተዘርፎ በችጋር ወደ እልቂት እያመራ መሆኑን ያመለክታል።
በቀላል ቋንቋ መድሃኒት ሳይጨምር ምግብ ብቻ በወር አንድ ሚልዮን ኩንታልና አምስት ሚልዮን ሊትር ዘይት አከባቢ ይፈለጋል። ችግሩ በአንድ አመት ውስጥ ለማስተካከል ቢሰራ'ኳ መድሃኒት ሳይጨምር በትንሹ 12,000,000 ኩንታል እህልና 60,000,000 ሊትር ዘይት ያስፈልጋል። ይህ ማለት በጣም በትንሹ ከአንድ ቢልዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋል።
እናስተውል!? ህዝብ ወደ እልቂት እያመራ ነው። ፖለቲካው እንደርስበታለን። ችግሩ ከመንግስትም አቅም በላይ እጅግ ግዙፍ እንደመሆኑ መጠን በየአከባቢው የምናደርጋቸው ጥረቶች እንደተጠቁ ሆኖው መንግስትና ያገባናል የምንል አካላት በሙሉ የረሃብ ፖለቲካ ረገብ አርገን በከፍተኛ ርብርብ ትላልቅ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችን በማስተባበር ስራቸውን በነፃነት እንዲሰሩ አሁኑኑ መፈቀድ አለበት።
https://www.facebook.com/tadesse.yemane ... 9972323986
