የፌዴሬሽን ምክር ቤት በኢፌዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 61 የተመሠረተ፣ በአገራችን ክልሎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውክልና የሚረጋገጥበት የፌዴራል ምክር ቤት ነው፡፡ በዚህ ምክር ቤት እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ቢያንስ በአንድ ተወካይ የሚወከል ሲሆን ለያንዳንዱ አንድ ሚሊየን ሕዝብ ተጨማሪ አንድ ወኪል ይኖረዋል፡፡ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባላት የሚመረጡት በክልል ምክር ቤቶች አማካይነት ነው፡፡ ምርጫው በቀጥታ አሊያም ደግሞ በተዘዋዋሪ ሊካሄድ ይችላል፤ ይህም ማለት የክልል ምክር ቤቶች አባላቱን በራሳቸው ወይም በቀጥታ በሚደረግ ሕዝባዊ ምርጫ እንዲመረጡ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በ5ኛው የምክር ቤት ዘመን፣ ምክር ቤቱ በአጠቃላይ 153 አባላት የነበሩት ሲሆን 76 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም ተወክለዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 እና በአዋጅ ቁጥር 251/93 መሠረት በርካታ ሀገራዊ አንደምታ ያላቸውና ልዩ የሆኑ ወሳኝ ሥልጣንና ተግባራት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 ላይ ተሠጥተውታል፡፡
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የመወሰን ሥልጣንም የምክር ቤቱ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ማንነቴ አልታወቀልኝም፣ የራስ በራስ የማስተዳደር መብቴ ተሸራርፏል፣ ቋንቋዬን፣ ባህሌንና ታሪኬን የማሳድግበት ሁኔታ አልተመቻቸልኝም፣ በአጠቃላይ በፌዴራል ሕገ መንግሥት የተደነገገው መብቴ አልተከበረም ወይም በማንኛውም ሌላ ምክንያት አድልዎ ተፈጽሞብኛል በማለት ለሚያቀርበው ጥያቄ ውሳኔ ይሠጣል፡፡ ከዚህም ባሻገር ብሔር ብሔረሰቦች ለሚያቀርቡት ክልል የመሆንና የመገንጠል ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምላሽ ይሠጣል፡፡
ሌላው የምክር ቤቱ ሥልጣን የሕዝቦችን እኩልነትና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ለመተግበር አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመመካከር የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ ባህል እና ንቃተ ሕገ መንግሥት ለማዳበር የሚያስችሉ የተለያዩ ዝግጅቶች በየወቅቱና በየአካባቢው ያከናውናል፡፡ በየደረጃው ያሉት የትምህርት ተቋማት በሕዝቦች መካከል እኩልነትና አንድነትን የሚያጠናክሩ የትምህርት ዓይነቶች በሥርዓተ ትምህርታቸው ማካተታቸውን ይከታተላል፤ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃንም ለጉዳዩ በቂ ሽፋንና አምድ መመደባቸውን ይከታተላል፤ ለሕዝቦች እኩልነትና አንድነት መጠናከር እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ አመለካከቶችና አዝማሚያዎች በማጥናትና በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ቀይሶ የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያስፈጽሟቸው ያደርጋል፡፡
በክልሎች መካከል ወሰንን በሚመለከትም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች የሚነሱ እንዲሁም በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶች በስምምነት ሊፈቱ ካልቻሉ የመጨረሻ መፍትሔ የሚያገኙትም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከዚህ አንፃር የሚነሱ አለመግባባቶችን ለማስወገድ የሚረዱ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ የግጭት መከላከያና ማስወገጃ ስልቶችን በማጥናት የአሠራር ሥርዓትና ስልት ይዘረጋል፡፡ ተቋማዊ ይዘትና አደረጃጀት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለት መካከል የሚከፋፈሉበትን፣ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመሮች መወሰንም ሌላው የምክር ቤቱ ሥልጣን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ ተጨባጭነትና ተቀባይነት ያለው በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ፍትሃዊና ውጤታማ የገቢ ማከፋፈያ ቀመሮችን የማዘጋጀትና የገቢ ክፍፍሉ ክልሎችን ከድጎማ በማላቀቅና የክልሎችን የተመጣጠነ ዕድገት በማምጣት ረገድ ያለውን አንደምታ በማጥናት ማስተካከያዎችን የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
ከላይ ከተገለጹት ሥልጣንና ተግባራት በተጨማሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር አስፈላጊ የሆኑ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ይለያል፤ #ማንኛውም ክልል ሕገ መንግስቱን በመጣስ #ሕገ_መንግስታዊ ሥርአቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀፅ 3 (8) ተሰጥቶታል ።
