1) የፌደራል መንግስቱ ሕጎቹን የማስከበር ግዴታ አለበት። ይሁንና ትህነግ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ ጥሶ ምርጫ አደርጋለሁ እያለ ነው። ትህነግ አደርገዋለሁ የሚለው ምርጫ ሕግን በመጣስ ብቻ አይደለም። በየቀኑ በፌደራል መንግስቱ ላይ እየዛተ እንደመንግስት እንደማይቆጠር ለማሳየት እየጣረ ነው። ይህ ደግሞ በቀጣይ ሌሎች ክልሎች ከፌደራል መንግስቱ እንዲያፈነግጡ ምሳሌ ለመሆን የሚያደርገው ነው። የፌደራል መንግስቱ ይህን ክልላዊ ውርጋጥነት ካላስቆመ በስተቀር በቀጣይነት ሌሎች ክልሎች ከምንም ተነስተው የፌደራል መንግስቱን አሰራር ጥሰው የፈለጉትን ቢያደርጉ የማስቆም ሞራልም አቅምም አይኖረውም።
2) የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደሕንነት፣ ንብረት የማፍራትና ሌሎች መብቶች መጠበቅ ያለበት የፌደራል መንግስቱ ነው። የክልል መንግስታት የዜጎችን መብቶች ሲጥሱ የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ የሚገባባቸው አሰራሮች ተቀምጠዋል። ትህነግ ወልቃይትና ራያ ላይ ሰብአዊ መብት ጥሰት ከሚባለው አልፎ የዘር ማጥፋትና ዘር ማፅዳት ወንጀል በመፈፀም ላይ ነው። ይህ ወንጀል ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ሀገራት ሲፈፅሙት የዓለም መንግስታትም ጭምር ለማስቆም ይገባሉ። የፌደራል መንግስት ይህን ወንጀል የክልል መንግስታት ሲፈፅሙት ዝም ብሎ ሊመለከት አይችልም። ማስቆምም ግዴታው ነው።
3) ትህነግ በተለየ ሁኔታ የጦርነት ነጋሪት በመደለቅ ላይ ይገኛል። ይህ የጦርነት ነጋሪት በዋነኛነት በፌደራል መንግስቱም ላይ ነው። የፌደራል መንግስቱ ይህን እቡይነት ጣልቃ ገብቶ ማስቆም መንግስታዊ ግዴታው ነው።
4) በቅርቡ በግልፅ አንቀፅ 39ን ተጠቅመው ሀገር ለመሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ይህ መብት ነው ተብሎ የተቀመጠ ቢሆንም አካሄዱን ግን በግድና በእልህ፣ በጦርነትና በድንፋት ጀምረውታል። ይህን አካሄድ ማስቆም ያልቻለ የፌደራል መንግስት ሉአላዊነትን ሊያስከብር አይችልም።
5) ትህነግ አሁን እየሄደበት ያለውን አካሄድ ከአሁኑ መቅጨት ያልቻለ የፌደራል መንግስት ለራሱም መረጋጋት ሊያመጣ አይችልም። በዋነኛነት ትህነግ ሕገወጡን ምርጫ የሚያደርገው ከመስከረም 30 በኋላ ሕጋዊ መንግስት የለም ብሎ ለመታገል እንዲያመቸው ነው። ይህ ትግል የሚደረገው ትግራይ ላይ አይደለም። ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል እንጅ። እስካሁን ባለው ፅንፈኞችን ደግፎ፣ አሰባስቦ እየታገለ ያለው ትህነግ ምርጫ አድርጎ "ሕጋዊ ነኝ" ካለ በኋላ ሕገወጥ የሚለውን የፌደራል መንግስቱን በምን መንገድ እንደሚታገለው ግልፅ ነው።
የፌደራል መንግስቱ እስካሁን ሲያሳየው ከነበረው መለሳለስ ወጥቶ ሕግ ካስከበረ ለነገም ሀገር የሚገጥማትን ችግር በከፊል መቀነስ ይቻለዋል። በቀደመው ተወዛጋቢነቱ ከቀጠለ ደግሞ ትህነግ ለሌሎችም የልብ ልብ በሚሰጥ መልኩ ይቀጥልበታል። ምርጫ አደረኩ ካለ በኋላም ዋነኛው ስራ የፌደራል መንግስቱን ስልጣን በመወዝወስ ብቻ አያበቃም። ኢትዮጵያን በማቃጠል "የፈረሰችው ሶማሊያ ውስጥ የተረጋጋች ሶማሊ ላንድ ተፈጥራለች፣ እኛም የእሷን ምሳሌ እንከተላለን" ያሉትን ይቀጥሉበታል። የፌደራል መንግስቱ ምርጫ አንድ ነው። ሕግን አስከብሮ መንግስት መሆን አሊያም ኢትዮጵያን ትህነግ ለሚለኩሰው እሳት አሳልፎ መስጠት! ሁለተኛውን መንገድ መከተል አወዳሚ መሆኑ ግልፅ ነው።