ኢሳያስ ፣ አቢይ፣ ወያኔ እና የኦሮሞ ጉዳይ
----
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----
በዚህ ርእስ ላይ ያተኮሩ አንዳንድ የተሳሳቱ ጭብጦች በሶሻል ሚዲያው ላይ ሲንሸራሸሩ እያየሁ ነው፡፡ ስለዚህ የማስተካከያ ሃሳቦችን መጠቆም ተገቢ ነው፡፡
---
አንዳንድ ኦሮሞዎች
ለዐቢይ መጥፎ ምክር እየሰጠ የሚያስጨርሰን ኢሳያስ ነው
የሚል የተሳሳተ ምልከታ ሲያንጸባርቁ አያለሁ፡፡
ሌሎቹም
ኢሳያስ በ1984 ለወያኔ ወግኖ የኦነግን ጦር በካምፕ አስገብቶ እንዳስጨረሰው ሁሉ ዛሬም ከዐቢይ ጋ ሆኖ እየተጫወተብን ነው
ይላሉ፡፡
ሁለቱም ምልከታዎች የተሳሳቱ ናቸው፡፡
በ1984 ኦነግን እና ኢህአዴግን ያደራደሩት የኤርትራ ጊዜያዊ መንግሥት እና የአሜሪካ መንግሥት መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም በዚያ ዓመት ኦነግን ያጋጠመው ሁኔታ የተከሰተው የኦነግ አመራር የወያኔን ባሕሪ በትክክል ስለማያውቅ ነበር፡፡ ኦነጎች በሚያዚያ 1984 በተደረገው የቀበሌ ምርጫ ማሸነፋቸው
በዋናው ምርጫም እናሸንፋለን
የሚል ግምት እንዲወስዱ አድርጎአቸው ነበር፡፡
በመሆኑም ጦራችሁን ወደ ካምፕ አስገቡ የሚለውን ፎርሙላ ለመቀበል አላንገራገሩም፡፡ ታዲያ በወቅቱ የተደረሰበት ስምምነት የኦነግን ጦር ብቻ የሚመለከት አልነበረም፡፡ ስምምነቱ
ሁለቱም ጦሮች ወደ ካምፕ ገብተው የፖሊስ ሃይል የጸጥታውን ስራ ይሰራል፤ እንዲሁም የተወሰነ የሽግግር መንግሥቱ ጦር ህዝባዊ ተቋማትን ይጠብቃል
የሚል ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ወያኔ በአደራዳሪዎቹ ፊት የገባውን ቃል በመክዳት ወደ ካምፕ በገባው የኦነግ ጦር ላይ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ ኦነግ ለዘመቻው ዝግጅት ስላልነበረው ወያኔ ባካሄዳቸው ዘመቻዎች በአብዛኛው ተጎጂ ሆኗል፡፡ (በዚያ ወቅት በሽግግር መንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤት የመከላከለያ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ
ሌንጮ ለታ ነበሩ፡፡ እርሳቸው በህይወት ስላሉ የተፈጠረውን ሁሉ በዝርዝር ሊነግሩን ይችላሉ፤ የኢህአዴግን የ1984 ድራማ በትክክል ለመረዳት ደግሞ የ
ተስፋዬ ገብረአብን “
የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ማንበብ ጠቃሚ ነው)፡፡
የአቢይ መንግሥትም በተመሳሳይ ሁኔታ ከኦነግ ጋር በአስመራ ሲደራደር ከርሞ አመራሩን ወደ ሀገር ቤት ካስመጣ በኋላ ትልቅ ክህደት ነው የፈጸመው፡፡ እኛም ክህደቱን በተጨባጭ መረጃ ስላረጋገጥን ነው አምና ከህዳር ወር ጀምሮ
ኦነግን ማጥፋት አይቻልም
በማለት ስንቃወመው የነበረው፡፡
ታዲያ በሁለቱም ክህደቶች ውስጥ የሻዕቢያም ሆነ የኢሳያስ እጅ የለበትም፡፡ ሻዕቢያ በታሪኩ በአብዛኛው ከወያኔ ጋር ተግባብቶ የማያውቅ ድርጅት ነው፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ከ1980-1983 ባለው ጊዜ በጋራ ሆነው ደርግን የተዋጉት ወያኔ በዘመኑ ባልተጠበቀ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ደርግን መገዳደር የሚችል ትልቅ ሃይል ሆኖ በመውጣቱ ነበር፡፡ ይህም
የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው
በሚል መርህ መሆኑ ነው፡፡
ከዚያ በፊት ግን (በተለይም ከ1975-1980) በከረረ ጸብ ውስጥ ነበሩ፡፡ በሽግግሩ ዘመን ደግሞ ሻዕቢያ ከሁለቱ ድርጅቶች ጠብ ገለልተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ካልተጨበጠ መረጃ ተነስተን ለረጅም ጊዜ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ደጋፊና ስትራቴጂክ ወዳጅ የነበረውን ህዝባዊ ግንባርንም ሆነ አቶ ኢሳያስን ስሕተት ከመቀውስ መቆጠብ ይገባናል፡፡
የውጪ እጅ ነገር ከተነሳ ዘንዳ በ1984 ሆነ በአሁኑ ወቅት ላለው የኢትዮጵያ መንግሥት የአይዞህ ባይነትን ድጋፍ የሚሰጥ ሌላ ስውር ሃይል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አለ፡፡ ይህም CIA (የአሜሪካ መንግሥት) ነው፡፡ ወያኔ በ1984 ኦነግን እንዲከዳ የልብ ልብ የሰጠው፣ ሀገር መምራት አቅቶት በሚንገታገትበት ወቅት ደግሞ
ስልጣን ለሌላ ቡድን አስረክብ
በማለት የተቆጣው CIA መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው (CIA ባይደግፋቸው ኖሮ ዐቢይ፣
ለማ እና
ገዱ የጦር ሃይሉንና የደህንነት ክፍሉን መቋቋም የሚችሉበት ጉልበት አልነበራቸውም)፡፡
-----
ኢሳያስ እና ዐቢይ ወዳጆች ናቸው፡፡ ወዳጅነታቸው ግን በሁሉም ነገር የሚገለጽ አይደለም፡፡ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚጫወተው ሚና የለም፡፡ ዐቢይ በሀገር ውስጥ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚሰራቸው ስራዎች ውስጥም ሻዕቢያ አይካፈልም (ለምሳሌ አቶ ኢሳያስም ሆነ ፊንፊኔ ያሉት የኤርትራ አምባሳደር የ
ምኒልክና የአፄ
ሃይለ ሥላሴ ሃውልት በተተከሉበት የአንድነት ፓርክ ምርቃት ላይ አለመገኘታቸውን ልብ በሉ፤ የኤርትራ ህዝብ ሁለቱን አጼዎች የታሪክ ጠላቶቹ አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ በመሆኑም አቶ ኢሳያስ በዚያ ስርዓት ቢገኙ የኤርትራ ጀግኖች የሞቱለትን ዓላማ ከድተዋል ማለት ነው)፡፡
በሌላ በኩል የኤርትራ መንግሥት ዐቢይ የሚከተለውንና የሚሰብከውን የመደመር ፍልስፍና አይከተልም፡፡ የኤርትራ እና የሻዕቢያ መመሪያ ለሃምሳ ዓመታት በተካሄደው የኤርትራ ህዝብ የነፃነት ትግል የበቀለ “ኤርትራዊነት” የሚሰኝ ርእዮተ ዓለም ነው፡፡ ሁለቱ መሪዎች የተስማሙት ሁለቱን ሀገሮች በሚያገናኙ የጋራ ጉዳዮችና የአካባቢያዊ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ ነው እንጂ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ አይደለም፡፡
----
በአንዳንድ ኤርትራዊያን በኩል የማየውን አንድ ስሕተት ደግሞ ልጠቁም፡፡
ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ዐቢይ በብዙኃኑ የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የተጠላ መሪ ነው፡፡ መላው የኦሮሞ ህዝብ በቀጣዩ ምርጫ ከስልጣን ሊያሰናብተው የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል፡፡ በሶሻል ሚዲያም የሚንፀባረቀው ይኸው ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ወያኔዎችም ዐብይን አይወዱትም፡፡ እነርሱም በሶሻል ሚዲያው ላይ በሚጽፏቸው ፖስቶች ለዐብይ ያላቸውን ጥላቻ እየገለጹ ነው፡፡
ይህ ሲባል ታዲይ በእኛ እና በወያኔ መካከል ግንኙነት አለ ማለት አይደለም፡፡ እኛ አብይን የጠላነው የህዝቡን አደራ ክዶ ሞቶ የተቀበረውን የፊውዳል እና ጨቋኝ የአፄዎች ስርዓት ከመቃብር እያስነሳብን ስለሆነ ነው፡፡ ወያኔዎች ዐብይን የሚጠሉት ግን ስልጣን ማጣታቸው ቁጭት ውስጥ ስለከተታቸው ነው፡፡ በሁለታችን መካከል ምንም ግንኙነት የለም፡፡ እኛ ትናንት ሲገድለን እና ሲዘርፈን በነበረው ወንጀለኛው የወያኔ ስብስብ ተታልለን አይደለም በአብይ ላይ የምንዘምተው፡፡ ወያኔ እኔን ቀርቶ አንዱን የኦሮሞ ገበሬ ማታለል የማይችል በዘበዛ ቡድን ነው፡፡
ስለሆነም ኤርትራዊያን የሁለታችንን ልዩነት እንዲገነዘቡልን እና የወያኔ ደጋፊ አድርገው እንዳይወስዱን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
----
በመጨረሸም፡
የኤርትራና የኦሮሞዎች ህዝቦች ወዳጅነት የተጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በተደራጀ ሁኔታ ለመብቱ መታገል ከጀመረባቸው ዓመታት አንስቶ የኤርትራዊያን ድጋፍ ነበረው (ለምሳሌ በ
ኤሌሞ ቂልጡ የሚመራው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሰራዊት የትጥቅ የጀመረባቸው መሣሪያዎች የተገኙት የ“ህዝባዊ ሃይልታት ኤርትራ” መሪዎች የነበሩት እነ
ዑሥማን ሳሊህ ሳቤ እና ኢሳያስ አፈወርቂ ባደረጉት ጥረት ነው )፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩት ኤርትራዊያን በድርጅቶቻቸው በኩል (ማህበር ሸውአተ፣ ጀብሃ እና ሻዕቢያ) የሚሰጣቸውን ተልእኮ በሚፈጽሙበት ወቅት በገንዘብም ሆነ በሌሎች መንገዶች ሲደግፋቸው ኖሯል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ኤርትራ ነፃ ከወጣች በኋላ ለሃያ ዓመታት ያህል ለኦሮሞ ነፃነት ሃይሎች ቤዝ ሰጥታ ትግላችንን በይፋ ስትደግፍ ነበር፡፡ የሁለቱ ህዝቦች ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በቀላሉ የሚደበዝዝ አይደለም፡፡ እኛ በዚህ ዘመን ያለነው ወጣቶችና ጎልማሶች ይህንን ያማረ ታሪካችንን ጠብቀን ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ አለብን፡፡
ዓወት ንሓፋሽ
Injifannoon ummata bal’aaf
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ሀረር ከተማ