Ethiopian Reporter
20 January 2021
ሳምሶን ብርሃኔ
በዓመት ውስጥ ብር ከዩሮ €34% ከፓውንድ £ ደግሞ 28.6% ተዳክሟል

መንግሥት ከዶላርና መሰል የውጭ ምንዛሪ መገበያያዎች አንፃር የብር ምንዛሪ ዋጋን እንዲዳከም ማድረጉ፣ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያስከትላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናገሩ።
በተለይ በስፋት በአገር ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው የብር ዋጋ ከውጭ ምንዛሪዎች አኳያ መዳከሙ የዋጋ ጭማሪ ያስከተለ ሲሆን፣ ይህ የሚቀጥል ከሆነ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሊያመጣ እንደሚችል ባለሙያዎች ከወዲሁ እያስጠነቀቁ ነው።
በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ብር ከዶላር አኳያ በ24 በመቶ፣ ከዩሮ አኳያ 34 በመቶ፣ እንዲሁም ከፓውንድ አኳያ ደግሞ 28.6 በመቶ ተዳክሞ የመሸጫና የመግዣ ዋጋው ወርዷል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግሥት ፍላጎትና አቅርቦትን መሠረት ያደረገ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት መተግበሩን ተከትሎ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የኑሮ ውድነት ሊያባብስ እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ፖሊሲ አውጪዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት በበኩላቸው ዕርምጃው፣ ‹‹ያለ ቅጥ የጨመረውን የብር ዋጋ›› በመቀነስ የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ያለመ ነው ሲሉ ቆይተዋል።
በሌላ በኩል የብር ዋጋ መዳከሙ የፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ መግዣ ዋጋ እንዲጨምር በማድረጉ፣ አገር ውስጥ እየተመረቱ ያሉ ምርቶች እንዲወደዱ ምክንያት ሆኗል። ጭማሪው እንደ ዘይት ባሉ ከውጭ ሙሉ ለሙሉ የሚገቡ ምርቶች ላይ የባሰ ሲሆን፣ ይህም የኑሮ ውድነት እያስከተለ መሆኑን ማውቅ ተችሏል።
ብርን ማዳከም ለምን አስፈለገ?
በ2003 ዓ.ም. አንድ ዶላር ከባንኮች ለመግዛት 17 ብር ብቻ በቂ ነበር። ከአሥር ዓመታት በኋላ ግን የብር ዋጋ በ130 በመቶ በመዳከሙ አንድ ዶላር ለመግዛት ከ40 ብር በላይ ያስፈልጋል። በእነዚህ ወቅቶች የብር ዋጋ በመንግሥት ከአምስት ጊዜ በላይ እንዲዳከም ተድርጓል። ታዲያ ይህንን ዓይነት ዕርምጃዎች የተወሰዱት፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ያላትን ተፎካካሪነት ለመጨመር ቢሆንም ውጤቱ አስደሳች አልነበረም።
በሥልጣን ላይ እያሉ ሕይወታቸው ካለፈው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አሁን ሥልጣን ላይ እስካሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ድረስ፣ የብርን ዋጋ ማዳከም ወጪ ንግድን ለመጨመር መፍትሔ ተደርጎ ቢወሰድም የተገኘው ውጤት እንደተጠበቀው አልነበረም። ባለፉት አሥር ዓመታት ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ፈቅ ያላለ ሲሆን፣ ከውጭ የሚገባው ምርት በአማካይ 15 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል። ከአራት ዓመታት በፊት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ብር በ15 በመቶ እንዲዳከም ሲደረግ ይስተካከል ተብሎ ቢሆንም፣ በወጪ ንግድ ገቢ ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ ሳይታይ የዋጋ ግሽበትን አባብሶት አልፏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ብር የሚዳከምበትን መጠን ይቀንሳል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ ተለዋዋጭ እንዲሆን በመደረጉ ይበልጥ ሊጨምር ችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልክ እንደ ቀዳሚ የኢትዮጵያ መሪዎች ይህ የወጭ ንግድ ገቢ ይጨምራል ብለው ቢያቅዱም ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ንቅንቅ አላለም።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ መንግሥት ይህን ዓይነት ዕርምጃ የሚወስደው ብር ሲዳከም በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ምርት ይረክስና ከውጭ የሚገባ ምርት ዋጋ ይጨምራል ይላሉ፡፡ ይህም የወጪ ንግድ ገቢን ያሳድጋል በሚል ዕሳቤ ቢሆንም፣ ነገር ግን የአገሪቱን አቅም ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ‹‹በተለይ ኢትዮጵያ ከውጭ ከምታስገባቸው ምርቶች ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዙት በአገር ውስጥ መመረት ስለማይችሉ፣ ብር ከዶላርና ከሌሎች የውጭ ምንዛሪዎች አንፃር ሲዳከም የዋጋ ግሽበት ማስከተሉ አይቀሬ ነው፤›› ይላሉ።
በእርግጥ ያለፈው በጀት ዓመት የብሔራዊ ባንክ መረጃ ሲታይ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች ውስጥ 15 በመቶ የሚሆነው ነዳጅ ሲሆን፣ ወደ 30 በመቶ የሚሆኑት አገር ውስጥ በስፋት በሕዝቡ ፍላጎት መጠን የማይመረቱት እንደ ዘይትና ስንዴ ያሉ የፍጆታ ምርቶች ናቸው። በተመሳሳይ ለፋብሪካዎች የሚውሉ ማሽነሪዎችን ጨምሮ የካፒታል ዕቃዎች ወደ 29 በመቶ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፣ ወደ 22.4 በመቶ ድርሻ ያላቸው ደግሞ በከፊል ያለቁ ምርቶች ናቸው።
እነዚህ ምርቶች በአገር ውስጥ ሳይመረቱ ብርን ማዳከም የሚጠቅሙ ምርታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለሚልኩ አገሮች እንደሆነ የሚያወሱት አቶ ወሰንሰገድ፣ ‹‹ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በእነዚህ አገሮች በጥሬ ዕቃነት የሚውሉ በመሆናቸው ዕሴት በመጨመር መልሰው ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የበለጠ ትርፋማ እንደሚሆኑና ኢትዮጵያ ደግሞ ኪሳራ ላይ እየወደቀች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ብር ሲዳከም የኢትዮጵያ ምርት ይረክርስላቸዋል፣ የሚልኩት ምርት ዋጋ ደግሞ ይጨምርላቸዋል፤›› የሚሉት ባለሙያው፣ ‹‹ከዚህም ማን አተራፊ፣ ማን እየከሰረ እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።
በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ብር በመዳከሙ ምክንያት አምራቾች እየተጎዱ መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹አምራቾች ጥሬ ዕቃዎችን በብዛት ከውጪ የሚያስገቡ ስለሆነ፣ ዓለም አቀፍ መገበያያዎች ከብር አንፃር ዋጋቸው መጨመሩ የምርት ወጪያቸው እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል፤›› ይላሉ፡፡ ችግሩ በዚህ አያበቃም። በተለይ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚያመርቱ አምራቾች የምርት ወጪ ሲጨምር የሚሸጡት ዕቃ ላይ ዋጋ እንዲጨምሩ እንደተገደዱ ይነገራል። ይህም የዋጋ ግሽበት እንዳባበሰ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል ለብር መዳከም እንደ ምክንያት የሚነሳው ባለፉት አሥር ዓመታት ከፍተኛ መጠን ያለው ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲገባ መደረጉ ነው። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) እንደሚሉት፣ መንግሥት የበጀት ጉድለትን ለመሙላት ገንዘብ ማተምን እንደ አማራጭ ለዓመታት በመውሰዱ ምክንያት፣ የብር የመግዛት አቅም እንደተሸረሸረና ከሌሎች ገንዘብ አንፃር ያለው ዋጋ እንዲዳከም ምክንያት ሆኗል። ይህ መንግሥት መር ከሆነው የብር ዋጋ ቅነሳ ጋር ተዳምሮ የበለጠ የዋጋ ግሽበት ሊያመጣ እንደሚችል ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው ብር የተዳከመበት መጠን ከፍ ባለባቸው ዓመታት የዋጋ ግሽበት ከፍ ሊል ችሏል። ለምሳሌ በ2012 ዓ.ም. ዓመታዊ የብር ምንዛሪ መቀነስ (Depreciation) ከ20 በመቶ በላይ በነበረበት ወቅት ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ከ12.6 በመቶ ወደ 19.9 በመቶ ከፍ ብሏል። የምግብ ዋጋ ግሽበት የበለጠ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ ከ13.1 በመቶ ወደ 23.1 በመቶ ጨምሯል።
የመፍትሔ ሐሳብ
መዋቅራዊና የአቅርቦት ችግሮች ሳይፈቱ ብርን ማዳከም አይበጅም የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ፣ እስካሁን በተገኘው ውጤት የወጪ ንግድ ገቢን መጨመርና የገቢ ንግድ ወጪን መቀነስ የሚቻለው እነዚህ ተግዳሮቶችን በመፍታት እንደሆነ ገልጸዋል። የሎጂስቲክስ፣ የኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ እጥረት፣ ቢሮክራሲና ሌሎች መዋቅራዊ ችግሮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ዋሲሁን፣ ብርን የበለጠ ማዳከም ለኢትዮጵያ ዓይነት ኢኮኖሚ የማይበጅ ነው ይላሉ።
የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በየወቅቱ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች፣ ‹‹የብር ዋጋ ከሌሎች ዓለም አቀፍ መገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለ ቅጥ ከፍ ያለ ነው፤›› በማለት፣ መንግሥት በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ሊተገብር እንደሚገባ በተደጋጋሚ ይሞግታል።
በዚህም ሳያበቃ ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት ሥርዓቱ ከመንግሥት መር ወደ ገበያ መር ሊቀየር እንደሚገባ በማውሳት፣ ኢትዮጵያ ፍላጎትና አቅርቦትን መሠረት ያደረገ ተንሳፋፊ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ካልተገበረች፣ በ2020 በፈንዱ የፀደቀላትን የሦስት ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ፓኬጅ እንደማታገኝ ግልጽ አድርጓል። መንግሥት በበኩሉ ከሁለት ዓመታት በኋላ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ እንዳቀደ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አቅርቦት መር የሆነ የምጣኔ ሀብት ሥርዓት ለመከተል ማሰቡን አስታውቋል፡፡
ይህንን የተረዱት አቶ ወሰንሰገድ፣ ‹‹አይኤምኤፍ ብድር ለመስጠት የመዋቅራዊ ለውጥ ፕሮግራሞችን መተግበር እንደ ቅደመ ሁኔታ ማስቀመጡ ለማን እንደሚቆም ማሳያ ነው፤›› በማለት፣ መንግሥት ውሳኔውን በድጋሚ ሊያጤነው እንደሚገባ ይናገራሉ። በተለይ የአይኤምኤፍ የገንዘብ ምንጮች ትልልቅ የውጭ ድርጅቶችና ሀብታም አገሮች በመሆናቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች በፕሮግራሙ በሚያስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ እንደማይጨነቅላቸው ማሳያ ነው በማለት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይሁን እንጂ የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰሩ ዓለማየሁ ገዳ መንግሥት በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉ ምርቶችን በመለየት፣ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን የመተካትና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ እሴት የመጨመር ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባው ጠቁመዋል። ተንሳፋፊ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ለኢትዮጵያ እንደማይበጅ የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ የገንዘብ ፖሊሲ ወጪ ንግድን ለማሳደግ መዋል እንደሌለበት ተናግረዋል።
ኢኮኖሚስቱ አቶ ዋሲሁን በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ተንሳፋፊ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ልትከተል የሚገባት የውጭ ምንዛሪ ክምችቷን ካሳደግችና ሌሎች ለወጪ ንግድ አለማደግ ምክንያት የሆኑ ማነቆዎችን (ማለትም መዋቅራዊ ችግሮችና የአቅርቦት ክፍተቶችን) ከፈታች ነው፤›› ብለው፣ ብርን በከፍተኛ መጠን ማዳከም ለጊዜው በረድ ሊደረግ እንደሚገባ ምክራቸውን ለግሰዋል።
https://www.ethiopianreporter.com/article/21053