በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤደንጎሮ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችና የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። አስተያየታቸውን ለዶቼቬለ የሰጡ ነዋሪዎች ባለፈው እሁድ ከአጎራባች ክልል ተሻገሩ ያሏቸው ታጣቂዎች ፣አራት ሰላማዊ ሰዎችንና ሦስት የፀጥታ ኃይሎችን በጥይት ገድለዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ በአቤደንጎሮ ወረዳ በታጣቂዎች ጥቃት ምክንያት ወደ ሰባት ሺ የሚደርሱ ነዋሪዎችም መፈናቀላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡ ሰዎቹ የተፈናቀሉት በወረዳው አራት ከሚደርሱ ቀበሌዎች መሆኑንም ገልጸዋል።
ባለፈው ቅደሜ ከ100 በላይ የቁም እንስሳትም በታጣቂዎች መወሰዳቸውን እና የአርሶ አደሮችም መኖሪያ ቤትም መቃጠሉን ቱሉ ዋዩ ከተባለ የወረዳው ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ አብራርተዋል፡፡ እንድ አስተያየት ሰጭ እንዳሉት ታጣቂዎች እህልና ሱቅ አቃጥለዋል፤በዚሁ የነተሳም ከሆማ ጋለሳ፣ሎሚጫ፣ጋራሮ ቀበሌን ጨምሮ ከአራት ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ጫካ ውስጥ ነው ያሉት ብለዋል።
ከአቤዶንጎሮ ወረዳ ቱሉ ዋዩ ከተማ በመሸሽ በዞኑ ዋና ከተማ ሻምቡ እንደሚገኙ የነገሩን ሌላ ነዋሪም ሰኞ እለት እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ በቱሉ ዋዩ ከተማ ተኩስ እንደነበር በሰላማዊ ሰዎችና ፀጥታ ሐይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፤የታቀጠለው ቤት ብዛትም እስካሁን በቁጥር አለመለየቱንም ተናግረዋል።
በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤዶንጎሮ ወረዳ የተከሰተውን ጸጥታ ችግር አስመልክቶ ዶቼቬለ ማብራሪያ የጠየቃቸው የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከተማ ዋቁማ በአካባቢው የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ የፀጥታ ኃይሎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል። አሁን ተረጋግቷል ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪው በተከሰተው የጸጥታ ችግር በሰው እና ንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ግን አለመግለጻቸውን ነጋሳ ደሳለኝ ከአሶሳ ዘግቧል።
-
MINILIK SALSAWI
- Senior Member
- Posts: 11413
- Joined: 24 Aug 2012, 12:02
- Contact: