Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Selam/
Senior Member
Posts: 16930
Joined: 04 Aug 2018, 13:15

ዮናስ አማረ - ህግ አልባው የኦሮሙማ የእንሰሳ ስርዓት!

Post by Selam/ » 21 Aug 2025, 05:03

ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሐመድ እና ዮናስ አማረ ያሉበትን ሁኔታ መንግስት በግልፅ እንዲያሳውቅ ኢዜማ እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ጠየቁ



አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12/ 2017 ዓ/ም፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር፤ ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሐመድ እና ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ “ከሕግ አግባብ ውጪ መሰወራቸውን” በመግለጽ ያሉበትን ሁኔታ መንግስት በግልፅ እንዲያሳውቅ በተናጥል ባወጡት መግለጫ ጠየቁ።

የአሐዱ ሬዲዮ 94.3 “ቅዳሜ ገበያ” ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሐመድ ነሐሴ 5/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሃያሁለት አካባቢ ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች ተይዞ መሰወሩ ተገልጿል። ጋዜጠኛው ከተሰወረ አራት ቀናት በኋላ በጸጥታ ኃይሎች ታጅቦ ቢሮው መበርበሩን ተከትሎ፣ የተያዘው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መሆኑ ተረጋግጧል።

የሪፖርተር ጋዜጣ ጋዜጠኛ ዮናስ አማረም ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም ምሽት ላይ በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ኮንደሚኒየም አካባቢ ጭንብል በለበሱ ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች ከቤቱ ተይዞ መወሰዱን የአካባቢው የጥበቃ አካላት ገልጸዋል።

በሁለት ቀናት ልዩነት በአንድ ሰሞን ተይዘው የተሰወሩት ሁለቱ ጋዜጠኞች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እስካሁን አልተቻለም ሲሉ ኢዜማ እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር በመግለጫቸው ገልጿል። ቤተሰቦቻቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ፖሊስ ጣቢያዎችና ፌደራል ፖሊስ ቢጠይቁም “የለም” የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።

ኢዜማ ነሐሴ 11/2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ “አለአግባብ ከሃላፊነታቸው በላይ ከሚንቀሳቀሱ ወይም ሕግን ከሚጥሱ መካከል የመንግሥትን ሥልጣን የያዙ አካላት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ የሆኑ የመገናኛ ብዙኃንን ከሕግ አግባብ ውጪ በተለያየ መንገድ ማዋከብ ዋናው ነው” ብሏል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበርም በበኩሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ “ጋዜጠኞቹ በወንጀል ተጠርጥረው ቢሆን እንኳን በሕግ አግባብ ተይዘው በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት መቅረብ ሲገባቸው፣ ያሉበት አለመታወቁ በእጅገ ያሳስበናል” ብሏል።

ማኅበሩ “ከሕግ አግባብ ወጪ ጋዜጠኞችን መሰወርና ፍርድ ቤት አለማቅረብ በምንም አግባብ ተቀባይነት የሌለው አደገኛ ልምምድ ነው” ሲል ገልጿል። በተጨማሪም “ይህ አይነቱ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚዲያውን ምህዳር ነጻነት በእጅጉ የሚሸረሽር በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መከላከል አለባቸው” ብሏል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር “የገቡበት ያልታወቁ ጋዜጠኞች በአስቸኳይ ከስወራ ነጻ እንዲወጡ” ጠይቋል። “ጋዜጠኞቹ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ካለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚያስከትል ስወራ ነጻ ወጥተው በሕግ አግባብ ብቻ እንዲዳኙ” ጥሪውን አቅርቧል።

ኢዜማ መንግሥት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ “ተገቢውንና እውነተኛውን መረጃ ለሕዝብ በየጊዜው ለመስጠትና ሐሰተኛ መረጃዎችን ማጋለጥ” ቢልም ከዚያ በማግስቱ እንዲህ ዓይነት ተግባር መታየቱ የተገባው ቃል “ከልብ አለመሆኑን” የሚያሳይ ነው ብሏል።

“በመንግሥት በኩልም በተደጋጋሚ ያለአግባብ ያሠርኩት ጋዜጠኛም ሆነ ዜጋ የለም የሚል ምላሽ ሲሰጥም ተመልክተናል” ያለው ኢዜማ፣ “የዚህ ምላሽ አሳሳቢነት አንድም መንግሥት ድርጊቱን እየፈፀመ ነገር ግን እየደበቀው ከሆነ መንግሥት ሕገወጥ ተግባራትን ሆነ ብሎ እየፈፀመ ነው የሚያስብል ሲሆን በሌላ መልኩ እነዚህ ተግባራት የሚፈፀሙት ከመንግሥት እውቅና ውጪ በሌሎች በተደራጁ አካላት ከሆነ መንግሥት በቅጡ የሀገሪቱን ፀጥታ እና የዜጎችን ደኽንነት እያስጠበቀ አይደለም የሚል ስጋት ዜጎች ላይ እንዲፈጠር ያደርጋል” ብሏል።

ኢዜማ በመግለጫው ላይ “አንፃራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት በሰፈነባቸው ሀገራት የመገናኛ ብዙኃን ዐራተኛ የመንግሥት አካል ተደርገው ይወሰዳሉ” ሲል የመገናኛ ብዙኃን ሚና አስረድቷል። “ይህንንም ተግባራቸውን የሚወጡት መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ እና በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ሕገወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ጭምር ነው” ብሏል።

“ባለፉት ዓመታት ይህ ዓይነት ተግባር በተደጋጋሚ ሲፈጸም ተመልክተናል፤ ባለፉት ጥቂት ወራትም ይኸው ተጠናክሮ ከመቀጠሉም በላይ ዜጎች የፀጥታ አካል ነን በሚሉ ግለሰቦች አንዳንዴም በማን እንደታፈኑ እና የት እንደታሰሩ እንኳን የማይታወቅበት ሁነት በተደጋጋሚ ሲያጋጥም እየታዘብን ነው” ሲል ኢዜማ ገልጿል።

“እነዚህ ሁነቶች በዋነኝነት የሚያመሩት ዜጎች ጠባቂ የለኝም ከሚል ስጋት በገዛ እጃቸው ደኽንነታቸውን ለማስከበር መሞከር ሲሆን በተጨማሪም የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚፈታተኑ ሕገወጦች እንዲበራከቱ በማድረግ የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ እና የዜጎች ደኽንነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የሚከት አስፈሪ ሁነት ነው” ሲልም አስጠንቅቋል።

ኢዜማ “ይህ ነገር ትኩረት እንዲሠጠው እያሳሰበ ይህንን የሚያደርገው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን መንግሥት ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ወደከፋ ችግር ውስጥ ከመግባቷ በፊት ትኩረት ሰጥቶ ማረም እንዲችል ለመወትወት መሆኑን” አመልክቷል።

ሁለቱ ድርጅቶች መንግሥት የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ለማረጋገጥ እና ሕግ የበላይነት እንዲከበር እንዲሁም ጋዜጠኞቹ ያሉበት ሁኔታ በግልፅ እንዲገለጽ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ይህ ዓይነቱ ተግባር በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።


https://addisstandard.com/Amharic/?p=8911&amp=1