
በትግራይ ክልል በህወሓት አመራሮች መካከል ያለውን የሥልጣን አለመግባባትን ተከትሎ አንድ የፓርቲው አባል በአምስት ታጣቂዎች በመታገዝ በዋና ከተማዋ መቀለ የሚገኝ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራን ተከትሎ ለሰዓታት የዘለቀ ውዝግብ ተከስቶ እንደነበር የጣቢያው ሠራተኞች እና ፖሊስ ለቢቢሲ አረጋገጡ።
ረቡዕ ጥር 21/2017 ዓ.ም. ረፋድ ላይ አንድ የፀጥታ ኃላፊ እና አምስት ታጣቂዎችን ይዞ ወደ መቀለ 104.4 ኤፍ ኤም ጣቢያ የደረሰው ግለሰብ ጣቢያውን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት መክሸፉን የጣቢያው ሠራተኞች ቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአምስት ታጣቂዎች ጋር ወደ ጣቢያው ያመራው ግለሰብ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ የሚባል የህወሓት አባል ሲሆን፣ ጣቢያውን ለማስተዳደር በመቀለ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ረዳኢ "ተሹሚያለሁ" እንዳለ ተገልጿል።
ዶክተር ረዳኢ በዶክተር ደብረጽዮን በሚመራው የህወሓት ክንፍ ለመቀለ ከንቲባነት የተሾሙ ሲሆን፣ በክልሉ ጊዜያዊው አስተዳደር ግን ሕገወጥ ከንቲባ ተደርገው ይወሰዳሉ።
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የሬዲዮ ጣቢያው ሠራተኛ አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ የተባለው ግለሰብ በታጣቂዎች ታግዞ ወደ ጣቢያው ከዘለቀ በኋላ የተቋሙን ማህተም ከፀሐፊዋ በመንጠቅ ለሠራተኞች ማስታወቂያ መለጠፉን ተናግረዋል።