ሩዋንዳ ለሁሉም አፍሪካውያን ከቪዛ ነፃ የጉዞ ፈቃድ ይፋ አደረገች
እንደ አውሮፓ የሼንገን ዞን የሰዎችን በነፃነት መንቀሳቀስ እና መገበያየት ለማሳደግ አህጉሪቱ የያዘችውን ዓላማ ተከትሎ ሩዋንዳ አፍሪካውያን ያለ ቪዛ ወደ ሀገሯ እንዲገቡ መፍቀዷን በትናንትናው ዕለት አስታውቃለች።
ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ከቪዛ ነፃ የጉዞ ፈቃዱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ እምቅ አቅም ያላትና የቱሪዝም መዳረሻ የሆነችው አፍሪካ 60 በመቶው ከአፍሪካ ውጭ ባሉ ጎብኚዎች ጥገኛ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል፡፡
ካጋሜ በ23ኛው የዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ማንኛውም አፍሪካዊ በፈለገ ጊዜ ወደ ሩዋንዳ በአውሮፕላን መግባት እንደሚችልና ምንም አይነት ክፍያ እንደማይከፍልም ገልፀዋል።
"የራሳችንን አህጉራዊ ገበያ መዘንጋት የለብንም" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ "በመጪዎቹ አስርት ዓመታት መካከለኛ አቅማችን በፍጥነት ማደጉን ከቀጠለ አፍሪካውያን የዓለም አቀፉ ቱሪዝም የወደፊት እጣ ፈንታ ይሆናሉ" ብለዋል፡፡
በዚህም ሩዋንዳ ለአፍሪካውያን የጉዞ ገደቦችን በማንሳት አራተኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ትሆናለች ማለታቸውን ኢንዲፔንደንት ዘግቧል።
ጋምቢያ፣ ቤኒን እና ሲሼልስ ሌሎቹ ከቪዛ ነፃ የጉዞ ፈቃድ የሚሰጡ ሀገራት ናቸው።
Source: Facebook
