ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ተገናኝተው፣ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ክልል መውጣትን በተመለከተ መወያየታቸው ተገለጸ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እንዳሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን፣ የኤርትራ ጦር ከሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በፍጥነት መውጣት አስፈላጊነት ላይ ተነጋግረዋል።
ህወሓት እና የፌደራል መንግሥቱ በደቡብ አፍሪካ በደረሱት የሰላም ስምምነት መሠረት የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ የሚወጡት ከህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ መፍታት ጋር ጎን ለጎን ነው።
ስምምነቱ ይህንን ቢልም እስካሁን ድረስ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ስለመውጣቱም ይሁን የመውጣት ጅማሮ ስለመኖሩ በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።
የውጭ ጉዳይ ኃላፊው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራ ጦር መውጣትን በተመለከተ መነጋገራቸው፤ የኤርትራ ኃይሎች አሁንም በትግራይ ክልል መኖራቸውን ያመላከተ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከብሊንከን ጋር ያደረጉትን ንግግር አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “ውጤታማ ውይይት አድርገናል። ሰላም ለማስፈን ለምናደርገው ጥረት አሜሪካ ስላደረገችው ትብብር አመስግኛለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።
Continue reading https://www.bbc.com/amharic/articles/cv29l0xzg8yo