Where is Ethiopia heading?!
ሚኒስትሩ በቅርቡ “አስቸኳይ የሰላም ጥሪ” ያወጡትን ሲቪል ማኅበራት አስጠነቀቁ
Wazema Radio
ዋዜማ ራዲዮ
ዜማ ራዲዮ- በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚንስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የሲቪል ማህበራት ተወካዮችን አርብ ዕለት ሰብስበው በሰጡት ማብራሪያ መንግስት የሲቪል ማህበራቱ ያወጡት መግለጫ ስህተት ነው ብሎ እንደሚያምንና እርምት በማያደርጉት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።
ጳጉሜ 1 ቀን 35 አገር በቀል ሲቪል ማኅበራት “በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል ያለው ጦርነት እና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች” በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት እንዲቀጥልና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብ ያቀረቡት “አስቸኳይ የሰላም ጥሪ” ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የተጋረጠባትን አደጋ ያላገናዘበ፣ በህወሃት የተፈጸመውን ጥፋት ያልገለጸ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ነቅፈዋል።
አርብ ጳጉሜን 4፣ 2014 ከሰዓት በኋላ በኢሊሌ ሆቴል በተደረገውና በአጭር ጊዜ በተጠራው ስብሰባ ከመቶ በላይ የሲቪል ማኅበራት ወኪሎች መገኘታቸው ታውቋል። ስብሰባው ለሚዲያ ዝግ የነበረ ቢሆንም ወደኋላ ላይ የኢቢሲ ጋዜጠኞች ሳይገቡ እንዳልቀሩ ታዳሚዎች ተናግረዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ አለሙ ስሜ ያደረጉት ወቅታዊውን ሁኔታ በማብራራት ቢሆንም ዋና ትኩረቱ ግን መንግስት ሲቪል ማኅበራቱ ባወጡት መግለጫ ላይ የተሰማውን ቅሬታ ና ቁጣ መግለጽ ነበር። ሚኒስትሩ አክለውም ሲቪል ማኅበራቱና ድርጅቶቹ ከህወሃት ጋራ በሚደረገው ጦርነት መንግሥት መደገፍ ካልቻሉ ወይም ካልፈልጉ “ዝም ብለው የተመዘገቡበትን ስራ” ብቻ እንዲያከናውንና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግልጫ ከመስጠት እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል። ከዚህ ውጭ “አንፈቅድም” ብለዋል። ሁሉም በተመዘገበበት መስክ ከመስራት ውጭ፣ “መከላከያ ሲዋጋ ሐሞት የሚያፈስ መግለጫ” ለሚያወጡ “ቶለራናንስ (ትዕግስት)” እንደሌለ የገለጹት አለሙ ስሜ (ዶ/ር) “የሚያጠፋውን ተከታትለን በጋራ እናርማለን፣ ከዚያ ያለፈ እርምጃ የሚያስፈልገውን ለኢትዮጵያ ስንል [እርምጃ] እንወስዳለን” ብለዋል በንግግራቸው ማሳረጊያ።
ዋዜማ ባሰባሰበቸው መረጃ የሲቪል ማኅበራቱ ተወካዮች በሁለት የተከፈለ አቋም እንዳንጸባረቁ ተረድታለች። ጦርነቱን በተመለከተ መንግሥትን ሙሉ በሙሉ የሚደግፉ አስተያተቶችና ጥያቄዎችን ያቀረቡ ተወካዮች ድምጻቸው ጎላ ብሎ ተሰምቷል። ከዚህ አልፎ ለብልጽግ ና ፓርቲ እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፏቸውን ግጥሞች ያነበቡ አንድ የመያድ ተወካይ እንደነበሩ ተሰምቷል። ሲቪል ማኅበራትን “የፈረንጅ ፍርፋሪ ለማግኘት” የሚጥሩ በማለት በከሃዲነት የከሰሱ በመንግስት ደጋፊነታቸው የሚታወቁ ተወካዮችም ድጋፋቸውን በስሜት ከመግለጽ አልተቆጠቡም። ለሚኒስትሩ ትንተናና አቋሞች ድጋፋቸውን በጭብጨባ ሲገልጹ የነበሩ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ነበሩ።
በተቃራኒው የሚኒስትሩ ንግግርና የስብሰባው ድባብ “አስጨናቂና አሳሳቢ” የሆነባቸው እንደነበሩ ካነጋገርናቸው ታዳሚዎች ተረድተናል። በሚንስትሩ አቋም እና በሌሎች አስተያየቶች ያዘኑ አንድ ታዋቂ የሕግ ባለሞያ፣ የሰላም ጥሪ መግለጫውን በፈረሙት ድርጅቶች ላይ የቀረበውን ነቀፋ በመቃወም “ድርጅታችንን ልትዘጉት ትችላላችሁ። ይህ ቀን ግን ያልፋል። ይህ ቀን እንደሚያልፍ አትርሱ…ሁሉም ነገር በሕግ አግባባ ብቻ ቢያዝ ሁላችንንም ይጠቅማል” በማለት ተናግረዋል። ከፈራሚዎቹ ድርጅቶች አንዱ የሆነ ሌላ ድርጅት ባልደረባ የሰላም ጥሪው የትግራዩን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ግጭቶች የሚመለከት መሆኑን፣ ጥሪውም ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ለተሳታፊዎቹ ሁሉ መሆኑን ማስረዳታቸውን ሰምተናል። አንዲት ሴት ተሳታፊ በበኩላቸው፣ ድርጅቶቹ የፓርቲ ወገንተኘነት እንደሌላቸው መናገራቸው ሚኒስትሩ ጉዳዩ የፓርቲ ሳይሆን የአገር ህልውና ጉዳይ ነው የሚል ረጅም ማብራሪያ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል።
Continue reading https://wazemaradio.com/%E1%88%9A%E1%8A ... %E1%88%AA/