Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
TGAA
Member+
Posts: 5747
Joined: 07 Apr 2019, 20:34

“ያመኑት ፈረስ፣ ጣለ በደንደስ” ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት (ኢሙንሕ) የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ . ምስጋና የሚገባዉ እውነታዊነት

Post by TGAA » 20 Mar 2022, 00:08

“ያመኑት ፈረስ፣ ጣለ በደንደስ”
ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት (ኢሙንሕ) የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

ከአራት ዓመት በፊት ጠ/ሚ አብይ አመድ “እኔ አሻግራችኋለሁ!” ሲለን ወዴት ብለን ባለመጠየቃችን ዛሬ ሃገራችንና ወገናችን እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ሰሞኑን ሃገራችን “ከፈተና ወደ ልዕልና” በመሄድ ላይ ናት፤ አላዲን እንደጋለበው ስጋጃ ምንጣፍ ከስበት በላይ እየሰፈፈች ነው የሚል ተረት ተረት እየሰማን ነው። ልዕልና የተባለው ተምኔታዊ ቃል ሃገሪቱ የወደቀችበትን አዘቅት ስፋትና ጥልቀት ግንዛቤ ውስጥ ፈጽሞ ያላስገባ ከመሆኑም በላይ የሕዝቡን የመረዳት ችሎታ መስደብ ነው ብለን እናምናለን። ሃቁ ግን ባለፈው አራት ዓመት ሃገራችን በድቅድቅ የጨለማ ዘመን ውስጥ እየኳተነችና እየተደናበርች ነው።

ትእግስተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሃትን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ ከሥልጣኑ ካሰናበተው በኋላ የጠበቀው የሚልዮኞችን መፈናቀል ነበርን? የሴቶች ልጆቹንና የእናቶችን መደፈር ነበርን? የከተማዎችን መቃጠልና መደምሰስ ነበርን? የእምነት ቤቶችን መፈራረስና መርከስ ነበርን? የወገኖች በተለይም የአማራው በማንነት መታረድና በእሳት መጋየት ነበርን? መስዋዕትነት የተከፈለው የሃገሪቱን ሃብት፣ ሥልጣኑን፣ ሥራውን አንድ ዘውግ ብቻ እንዲቆጣጠረው ለማድረግ ነበርን? የጋራ እሴቶቹ የሆነኝ ተብሎ ተደርምሰው የረዥም ዘመናት ታሪክ ያላት ውድ ሃገሩ ኢትዮጵያ እንደአዲስ ተቦክታና ተላቁጣ የአንድ ዘውግ ቅርጽ ብቻ ይዛ እንድትወጣ ነበርን? ዛሬ በጠ/ሚ አብይ አህመድ መሪነት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀመ ያለው ይኸ ነው። በዘር ነዳጅ እየተንቀሳቀሰ ያለው የጥፋት ባቡር እየተግለበለበ ባለበት ትናንት ድል በለለበት ስለ”ድል” ዛሬ ደግሞ ሰላም በለለባት ሃገር ስለ”ልዕልና” የሚወራው ለመሆኑ ምንን ዋቢ በማድረግ ነው የሚለው የሁላችንም ጥያቄ መሆን አለበት ብለን እናምናለን።

ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ቅድም አያቶቻችን የተቀዳጁትን የአድዋን ድል በዓል የባህልና የስፖርት ሚንስትሩ በአድዋ ድልድይ ሥር ይከበራል ብሎ ሲበይን ለመሆኑ ስለአንዲት ሁላችን የምናውቃት ኢትዮጵያ እያሰበ ነበርን? እንዳልሆነ መልሱን አጥተነው አይደለም። የአድዋን ድል በዓል በቦታው ያከበረውን አዲስ አበቤን በሚቀጥለው ቀን የፀጥታና የደህንነት ሃይሎች እየለቀሙ እሥር ቤት ወርውርውት ፍርድ ቤት እየተመላለሰ በመጉላላት ላይ ይገኛል። የኛ ጉድ ማቆሚያ የለውም። ትናንት ሽብርተኛውን ሕወሃትን ለማስቆም ጥሪ ተደርጎለት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለውና በመክፈል ላይ ያለው ፋኖ ዛሬ በሚያሳዝን ሁኔታ በመንግሥት ትዕዛዝ በአማራ ክልል እየተሳደደና እየተለቀመ በመረሸን ላይ ይገኛል። ይህ በፋኖ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ከየአቅጣጫው ብዙ መከራ በማስተናገድ ላይ ያለውን የአማራን ሕዝብ ለማንበርከክ የሚደረግ ጥረት ስለሆነ ድርጅታችን አጥብቆ ያወግዛዋል። ጥያቄው ለዚህና ለመሳሰሉት ታላቅ መንግሥታዊ ክህደቶች የሕዝቡ ምላሽ ምን ይሆን ነው። ወደድንም ጠላንም ዛሬ ኢትዮጵያ የምትኖረው በተውሶ ሰዓት ነው ማለት ይቻላል።

ዛሬ ወገናችንን የኑሮ ውድነት የቁምስቅሉን የሚያሳየው በሃገሪቱ ሰላም በመጥፋቱ የአቅርቦት ችግር ስላለ ብቻ ሳይሆን አንድ ዘውግ ብቻ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በቁጥጥሩ ሥር ስላዋለውም ጭምር ነው። በማንነቱ ምክንያት ከሥራው በመባረሩ ቤተሰቦቹን የሚያስተዳድርበት የገቢ ምንጩ የደረቀበትን ቤቱ ይቁጠረው። ወገናችን ላለፉት 10 ዓመታት የታገለው ከሕወሃት የከፋ ሥራዓት ለማስተናገድ አልነበረም። ሕወሃትን ከሥልጣን ያወረደው ትግሬ በመሆኑም አልነበረም። ፍትህ ስለተጠማ እንጂ! ሃቁን ለመናገር ለወገናችን በኢትዮጵያ የሚምለውና የሚገዘተው የጠ/ሚ አብይ አህመድ ጉዳይ “ያመኑት ፈረስ ጣለ በደንደስ” ከሆነበት ሰነባብቷል።

ዛሬ በሃገራችን ሕዝቦቿን ሙሉ በሙሉ የሚወክል፣ ዳርድንበሯን የሚያስከብር፣ የዜጎቿን ሰላምና ደህንነት የሚያረጋግጥ መንግሥት አለ ለማለት አይቻልም። መለወጥ ባለበት በሃገሪቱ ሕገመንግሥት ውስጥ እንዲከበር የተደነገገው በመንግሥትና በእምነት ተቋማት መካከል ያለው ልዩነት በጠ/ሚንስትር አብይ አህመድ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲጣስ እያየን ነው። መንግሥት በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ሆነ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ በሁለቱ ታላላቅ እምነት ተከታዮች መካከል ችግር ለመፍጠር መሟሟቅ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። በቅርቡ ጠ/ሚንስትሩ በመላ ዓለም ለሚገኙ ሙስሊሞች የኢድን በዓል ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያደረገው ጥሪ በእምነት ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው ብለን እናምናለን። መንግሥት ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር ያለውን ጉዳይ አግባብ ባለው መንገድ መጨረስ ሲገባው ለፖለቲካ ፍጆታ ሲል በኢድ በዓል አሳቦ የሙስሊሙን ማህበረሰብ እፍትጊያው ውስጥ ጎትቶ ለማስገባት መሞከሩ ግልጽ የሆነ የሕገመንግሥት ጥሰት ነው። አጥብቀንም እንቃወማለን። ጠ/ሚንስትሩ ጥሪውን ያቀረበው በተለይም የአብሮነት ጠር የሆነውን ጥንፈኛውን የሰለፊ ክንፍ ለማስጠጋት ወይም ለማስደሰት አስቦ እንደሆነ መገመት ይቻላል። በበኩላችን ጠ/ሚንስትሩ ሃላፊነት እንደማይሰማው የማህበራዊ ሚድያ አክቲቪስት የፈለገውን እስከተናገረ ድረስ አገሪቱን መምራት ይችላል የሚል እምነት የለንም።

ጠ/ሚንስትር አብይ አህመድ ለዚህ ሁሉ መከራ መንስኤ የሆነውን የሕወሃት ሕገመንግሥት እንዲለወጥ እንደማይፈልግ በተደጋጋሚ ሲናገር ተሰምቷል። የወገናችን ትዕግሥት ለከት ሊኖረው ይገባል። ወገናችን ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ ሕገመንግሥቱ እንዲለወጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ካላደረገ ሃገራዊ ግዴታውን እየተወጣ ነው ለማለት አንደፍርም። ጣት መቀሰር ብቻውን ግብ ሊሆን አይችልም። ወገናችን ለተተኪው ትውልድ የሚያስተላልፋት ኢትዮጵያ ካልኖረች በታሪክ ተጠያቂው አሱም ጭምር ይሆናል። አሁን አገሪቷ እንድትጠፋ በምትወሰድበት ፍጥነት ላይ የወገናችን ዝምታ ሲጨመርበት ነገ የሚያድናት ኢትዮጵያ ላትኖር ትችላለች የሚል ጠንካራ ስጋት አለን። ለዚህ ነው ዛሬ ላይ ወገናችን ከተቆራኘው ትዕግሥቱ መላቀቅና ላለፈው 10 ዓመት ያካበተውን የሰላማዊ ትግል ተመክሮ ሥራ ላይ እንዲያውል ጥሪያችንን የምናቀርብለት!! በበኩላችን እንደሙስሊም ድርጅት “ዘረኝነት ጥንብናትና ራቋት!” የሚለውን ሃይማኖታዊ መርሃችንን መቼም ቢሆን ለድርድር አናቀርበውም።

ፍትህ ያሸንፋል!

አላሁ አክበር!

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት (ኢሙንሕ)