Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Thomas H
Senior Member
Posts: 13070
Joined: 27 Jan 2007, 16:30
Location: Kaliti
Contact:

ከልጆቹ : የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበረው ትግራዋይ መአረግ አማረ አብርሃ ማን ነው ?

Post by Thomas H » 07 Nov 2021, 21:38

令人心碎





Via Abrham Meareg ❗️❗️❗️
ከሚወዱትና ሁሌም ከሚናፍቁት ቤተሰቦቹ የተሰጠ የሃዘን መግለጫ
አባታችን ፕሮፌሰር መአረግ አማረ አብርሃ (ዶክተር) ከአባቱ ሃለቃ አማረ አብርሃና ከእናቱ ወይዘሮ ዘውዲቱ ገብረዋሃድ በአክሱም ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው ሌቶ በተባለች ሰፈር በ1953 ዓ∙ም ለቤተሰቦቹ ሁለተኛ ልጅ ሆኖ ይህችን አለም ተቀላቀለ፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአክሱም ከተማ የተከታትሏል፡፡
የተከበረው አባታችን በዕውቀት የታነጸ ጭንቅላቱን ተምሮ ያስተማረበት፣ ያማረበትና የኮራበት ከልጅነት እድሜው ዲፕሎማውን ከሃረማያ ዩኒቨርስቲ በኬሚስትሪ የትምህርት መስክ በ1973 ዓ∙ም አጠናቆ በ1974 ዓ∙ም በጎንደር ክፍለሃገር በወገራ አውራጃ፣ በዳባት ከተማ በሚገኘው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድቦ ያስተማረ ሲሆን፣ በወቅቱ በ1975 ዓ∙ም የካቲት ወር በደርግ ወታደራዊ መንግስት ታስሮ እስከ ታህሳስ 29 1977 ዓ∙ም በጎንደር ባዕታ ወይኒ ቤት የቆየ ሲሆን ከዛም ከእስር ተለቆ በትክልድንጋይና በዳንግላ ከተማዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አገልግሏል፡፡ ከዛም በባህር፟ዳር ከተማ በሚገኘው ጣና ሃይቅ ትምህርት ቤት ለረጅም ግዜ እያስተማረ እራሱን በማሳደግ በክረምት የትምህርት ፕሮግራም የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አራት፟ኪሎ ካምፓስ በመቀጠልም የሁለተኛ ዲግሪውን በተመሳሳይ ዩኒቨርስቲና የትምህርት መስክ የተማረና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መምህራን ማህበር በመቀጠልም በክልሉ ትምህርት ቢሮ በከፍተኛ ኦፊሰርነት ተመድቦ ህዝብና መንግስትን አገልግሎል፡፡
አባታችን በ1990ዎቹ ሁላችንም የተማርንባቸው የ7ኛ፣8ኛ፣9ኛ፣10ኛ ክፍል መማሪያ መጸሃፍትን በአዘጋጅነትና የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል መማሪያ መጸሃፍትን ደግሞ በአርታኢነት የተሳትፏል፡፡
ከዛም በባህር፟ዳር ዩኒቨርስቲ በኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ውስጥ ተቀጥሮ በማስተማር በ2005 ዓ∙ም ከፍተኛ የዕውቀትና ማደግ ፍላጎቱን ለማሳካት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዲግሪውን ተከታትሏል፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ህይወቱን በግፍ እስከተነጠቀበት ቀን ድረስ ለመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎች በማስተማርና ምርምር ዘርፎች እጅግ የላቀ አስተዋጾ እያደረገ ነበር፡፡ አባታችን እረፍትን እንደ ስንፍና የሚጠየፍ፣ መማርና ማስተማርን እንደ ዋና ህይወት ጥሪ በመውሰድ በመንግስት የስራ ሰአትን ጨምሮ ቅዳሜና እሁድን (ዘወትር ከቤተክርስትያን መልስ) ያለ ስስት በስራው ያሳልፍ ነበር፡፡
የበአል ቀናትን ጨምሮ ካለመዛንፍ በየቀኑ 14-15 ሰአታት በቢሮው፣ በቤተ ሙከራውና ላፕቶፑ ላይ በትጋት የሚያሳልፍ ነበር፡፡ ከትምህርት ክፍል ጎደኞቹ ጋር በመሆን ግዙፍ የኬሚስትሪ ቤተ ሙከራ ከብዙ ልፋት በኋላ በማቛቛም ለትምህርት ክፍሉና ለዩኒቨርስቲው እውቅና አስገኝተውለታል፡፡ በዚሁም ተከታታይ ስራዎቹ ምክንያት የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት በመቀጠልም በ2013 ዓ∙ም ወደ ሙሉ ፕሮፌሰርነት ደረጃ አድጓል፡፡
በማህበራዊ ሂወቱም ስራ በጀመረበት የዳባት ከተማ ተወልዳ ያደገችውን እናታችን ከወይዘሮ ንግስት ሃይሉ ጋር በሚያዚያ 13 1977 ዓ∙ም በወግ በመአረግ ትዳር መስርተው የ3 ወንድና የ1 ሴት ልጅ አባት በመሆን ሁለት የልጅ ልጆችን ለማየት በቅቶል፡፡ በህይወታቸውም እጅግ ደስተኛና በፈርሃ እግዚአብሄር ታንፆ የኖረ ህይወታቸውን በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በስጋወ፟ደሙ አጽንተው ለ26 አመታት ቀን ተቀን በስስት ከሚያያት ውድ ባለቤቱ ጋር ወስደው ኖረዋል፡፡
በባህርዳር ከተማ በቀበሌ 13 የመኖሪያ ቤት ገንብተው ለ31 አመታት የኖረና፣ ለሞተው የሚያጽናና፣ ለተቸገረ የሚረዳ፣ አጣሁ ብሎ ተስፋ የማይቆርጥ፣ አገኘሁ ብሎ የማይኮራ፣ ለተራበው የሚያበላ፣ ለተጣላ አስታራቂ፣ ዘወትር ታህሳስ 3 ቀን የምትውለውን ባዕታ ማሪያምን በቤቱ የሚዘክር፣ ከተደሰተው ጋርም የሚደሰት ነበር፡፡ ከቤተሰቦቹ በተጨማሪ አባታችን ለባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች በተለይም ለጎረቤቶቹና ለተማሪዎቹ የተለየ ፍቅርና አክብሮት ነበረው፡፡
በመጨረሻዎቹ የህይወት ዘመናትም መጋቢት 20/2013 ዓ∙ም ጡሮታ የወጣ ቢሆንም ተጨማሪ አመታትን ከዩኒቨርስቲው ጋር ባደርገዉ ስምምነት መሰረት ስራ ላይ ነበር፡፡ በቀሪው የህይወት ዘመኑም በተለየ አቀራረብ ለልጆችና አዋቂዎች እንግሊዝኛን ጨምሮ በአማርኛና በትግርኛ የተጻፉ ተከታታይ ቅጽ መጸሃፎችን፣ የግል የህይወት ታሪኩን (ባዮግራፊ) ጨምሮ 5 ያለቁና በሂደት ላይ የነበሩ የምርምር ውጤቶችን ለማበርከት ሁሉን በእኩል ለፍሬ እንዲበቁ ያለ እረፍት ይሰራ ነበር፡፡
አባታችን ለ40 አመት በአማራ ክልል እድሜውን ያሳለፈና ላልተማረ ያስተማረበት ልጆቹን ለወግ መአረግ ባበቃበት በቀን በ24/02/2014 ዓ∙ም እኩለ ቀን አውርቶ የማይጠግበው አባቱ በቅድስቲቱ አክሱም በሚዘክሩበትና ከዚህ አለም በተለዩበት በጻዲቁ ተክለ፟ሃይማኖት ቀን ከአመታት በፊት ልጆቹ በስጦታ ገዝተን ያበረከትንለት ተሽከርካሪ ወደ ቤቱ ለመግባት የግቢ በር እየከፈተ ባለበት ወቅት ውድ ህይወቱን በአሰቃቂ ሁኔታ በተተኮሱበት ጥይቶች ሊያጣ ችሏል፡፡ በመቀጠልም ኮድ 2 የታርጋ ቁጥር 80771 አአ የሆነች ያሪስ መኪናውን አስነስተው ወስደዋል፡፡
በግፍ የፈሰሰ ደሙ ቢመረመር ደሙን ካፈሰሱት ከገዳዮቹ እና ቆምንለት ላሉት ማህበረሰብ በላይ በተግባር ተቆርቆሪና አሳቢ ሰው እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች፣ የምስክር ወረቀቶች፣ የኢትዮጲያና አማራ ቴሌቨዢን ፕሮግራሞች ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ውዱ አባታችን ዘወትር በግሉና የቤተሰብ የጋራ ጸሎታችን ስናደርግ እንደሚመኘው በኩራት የራሴ በሚለው ከተማ በወግና በክብር መቀበር ተስኖት፣ እንደ ዐይን ብሌን የሚሳሱለት ቤተሰቦቹ ባልተገኙበት፣ ሰፈር ጎረቤት በሌለበት፣ ክርስቲያናዊ ፍትሃተ ጸሎት ሳይደረግለትና በተገደለበት ቦታ ሳይነሳ ለረጅም ሰአታት ወድቆ ቆይቷል፡፡ ሃዘናችንን እጅግ መራር ያደረገውም እንደ ሰው በወግና ስርአቱ መሰረት ዕርማችን ሳናወጣ፣ ሳናለቅስ፣ የቀብር ሂደቱንና ቦታውን ሳናውቅ መቅረታችን ነው፡፡
* እውን አባታችን ሁሉ ሃገሬ! ሁሉ ወገኔ! ባለ ይህ ይገባዋልን?
* እውን አባታችን በዕለተ ዕሮብ ጹሙን በዋለ አንጀቱ በህዝብ ፊት መገደል ነበረበት?
* እውን አንድም ቀን በየትኛውም የጸጥታ ሃይል በክፉ ተነስቶም ይሁን ተበርብሮ የማያውቅና በጸጥታው የተከበረ ቤት ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል ነበረበት?
* አባታችን በመጨረሻ እስትንፋሱ ምን ተሰምቶትና ምን አስቦ ይሆን?
ፍትህንና ሰላምን ከፈጣሪ ብቻ እንጠብቃለን!
ከውድ ቤተሰቦቹ