ተጻፈ በያሬድ ጥበቡ
በሽግግሩ ወቅት የኦሮሞ ብሄርተኝነት በኦነግ: በኦፌኮ: በOLA ወዘተ ሲወከል: የትግራይ ብሄርተኝነት በህወሓት በሳልሳይ ወያነ በውድብ ሓርነት ወዘተ ይወከላል:: አማራ ግን ሁሉም ጁንታው ላይ ዘማች ከሆነ እንደገና ከ30 ዓመታት በሗላም በሽግግር መድረኩ ሳይወከል ቀርቶ እንደገና እያለቃቀሰ ሊኖር ነውን?
የአማራ ብልፅግና ክተት ይላል: አብን ክተት ይላል ሆኖም የትግራይን መከላከያ ሃይል ከሚሴ ከመድረስ አላገደውም:: በዚህ ከቀጠለ ህወሓት የትግራይ ጦርነትን አንደኛ ዓመት መታሰብያ አዲስ አበባ ላይ ሳይዘክር አይቀርም:: የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲያደርግ ሲለመን የከረመው የአቢይ አስተዳደር እንደዝያ ሲያንቋሽሻቸው የነበሩት ምእራባውያንን ለምኖ የሰላማዊው ሽግግር መድረክ ላይ ካልተገኘ በቀር: ለድርድር እንኳ ሳይደርስ እየከሰመ ነው::
በሽግግሩ ወቅት የኦሮሞ ብሄርተኝነት በኦነግ: በኦፌኮ: በOLA ወዘተ ሲወከል: የትግራይ ብሄርተኝነት በህወሓት በሳልሳይ ወያነ በውድብ ሓርነት ወዘተ ይወከላል:: አማራ ግን ሁሉም ጁንታው ላይ ዘማች ከሆነ እንደገና ከ30 ዓመታት በሗላም በሽግግር መድረኩ ሳይወከል ቀርቶ እንደገና እያለቃቀሰ ሊኖር ነውን? ትንሽ ብስለት: ትንሽ አርቆ ማስብ: ትንሽ ጉራን መቀነስ የማይችለው ለምንድን ነው? አሁን ባለቀ ሰአት ክተት ዘመቻ መጥራት ከአማራው ህዝብ ጥቅምና ሁኔታ ጋር የሚመጥን ነውን? አቅመቢስና ደካማ ሆኖ ከመኖር ውጪ ምን ይጠቅመዋል?
እንደ ህወሓት አመድ ልሶ ከወደቀበት ይነሳል እንዳልል: አፈር ልሶ ለመነሳት ዓመታትን ያስቆጠር የድርጅትና አመራር ልምድ ይጠይቃል:: አማራ ደግሞ የሚጎድለው እነዚህ ሁለት ብርቅዬ ጉዳዮች ናቸው:: እመው ሲተርቱ ጅብ እስኪነክስ ያነክሳል ይላሉና: የአማራ ብሄርተኝነት አቅሙን አስኪገነባ: አመራሩን እስኪያጠራ: ፍላጎቱን አጥርቶ እስኪያውቅ ድረስ ይሄ አሁን ከተኮፈሰበት ግፋ በለው ውረድ በለው ፈረስ ወርዶ: ወደሽግግር ጉባኤው የሚያስገባውን መላ ቢፈልግ ተገቢ ይመስለኛል::
ከመላዎቹም መሀል:
1ኛ) በወልቃይት ሁመራ ጉዳይ ላይ ከሁለቱም ወገን አላስፈላጊ የህዝብ እልቂት ከመምጣቱ በፊት ከህወሓት ጋር ለመደራደር ቢዘጋጅ
2ኛ) በሽግግር መድረኩ ወቅት ስለሚኖረው ሚና ቁጭ ብሎ ቢደራደር ትገቢ ይመስለኛል::
ይህን ማድረግ እምቢ ብሎ አሁን በያዘው የክተት ጥሪው ከቀጠለ ግን የአማራ ብሄርተኝነት ጉዳት እንዳይደርስበት እፈራለሁ:: በአቢይና እሳያስ ጦርነት አማራው የሚማገደው ለምንድን ነው? እስካሁን የደረሰው ብካይ ይበቃል:: የድርድር አቅማችሁን ሰብስባችሁ የህዝባችሁን እምባ አብሱ:: የተፈናቀለውን ወደቀዬው መልሱ:: ልጆቻቸውን በጦርሜዳ ላጡ አረጋውያን መቋቋሚያ አስቡ ሥሩ:: የሟች ቤተስቦችን አርዱ: አፅናኑ: አቋቁሙ! ምንም ቢሆን ምን ግን ጦርነቱን ለማስቀጠል መሳርያ አትሁኑ:: የእስካሁኑ ጥፋት ይበቃል:: ፈጣሪ ማመዛዝኛ ልቦና ይስጣችሁ:: ከቂምና ጥላቻም ራቁ: ከደመኝነት ስሜት ሆን ብላችሁ ሽሹ:: የተሻለው መንገድ ይሄ ነው: ቀናው መንገድ ይሄ ነው:: አይዞን!
Please wait, video is loading...
