Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 11594
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

Eth Construction Companies Ask for Government Bailout Due to Lack of $ ForEx & Inflation

Post by sarcasm » 31 Dec 2020, 09:33

የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች መንግሥት ይታደገን እያሉ ነው

27 December 2020

ሲሳይ ሳህሉ

በኢትዮጵያ በተለያዩ የግንባታ ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በገበያ ዋጋ ግሽበትና በገንዘብ አቅርቦት አለመኖር፣ ሠራተኞች ከመቀነስ ጀምሮ ሥራ የማቆም አዝማሚያ እየታየባቸው ስለሆነ መንግሥት ይታደገን እያሉ ነው፡፡

ኩባንያዎቹ ከመንግሥት ጋር በርካታ ትልልቅ አገራዊ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ተዋውለው ሥራ ቢጀምሩም፣ መንግሥት የመደበውን በጀት ስለማይለቅና ለዋጋ ግሽበትና ለውጭ ምንዛሪ እጥረት ምንም ዓይነት ማካካሻ ባለመስጠቱ እየከሰሩ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አምሐ ስሜ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የፋይናንስ አቅርቦት እጥረትና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በአገር ውስጥ በበቂ አለመኖር፣ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተዳምሮ በርከት ያሉ የሥራ ተቋራጮች ሠራተኛን ከመቀነስ ጀምሮ ከአምስት ወራት በላይ ደመወዝ ያልከፈሉ እንዳሉ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

አምሐ (ኢንጂነር) መንግሥት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ቀርቦ በመነጋገር እየገጠማቸው ያለውን ችግር በመረዳት፣ ተቋራጮች የገቡበትን ቀውስ ለመፍታት ዝግጁ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ዘርፉ እየፈጠረ ያለውን ዕድል በትክክል በመረዳት ለሥራ ተቋራጮች ተመጣጣኝ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ፣ ምቹ የኮንስትራክሽን አደረጃጀትና መመርያ በማዘጋጀት ተገቢውን አገራዊ ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

ከ2,000 በላይ የሥራ ተቋራጭ አባላት እንዳሉት የሚነገርለት ማኅበሩ፣ ከአደረጃጀትና ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን የዳሰሳ ጥናት አድርጎ በቅርቡ ለመንግሥት እንዳቀረበም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዛምራ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ስለተባለው ጉዳይ ሲናገሩ፣ ችግሩ ሰንበት ያለ እንደሆነና ከዓመታት በፊት የብር የመግዛት አቅም ከዶላር ጋር ዝቅ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሥራ ተቋራጮችም በዚህ ሰበብ ለደረሰባቸው የፕሮጀክቶች የዋጋ ግሽበትና ክስረት ማካካሻና ካሳ ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ለሚያሠራቸው ፕሮጀክቶች በወቅቱ ክፍያ አለማግኘት፣ ተከታታይ የዋጋ ግሽበትና የብድር አቅርቦት አለመኖር የሥራ ተቋራጮችን እንቅስቃሴ የገደበ ከመሆኑም በላይ፣ ለኪሳራ እየዳረገን ነው ብለዋል።

ዛምራ ኮንስትራክሽን ባለፉት ሁለት ወራት ደመወዝ መክፈል እንዳልቻለ፣ ወደፊትም የመክፈል አቅሙ አጠራጣሪ በመሆኑ መንግሥት ጉዳዩን በሚገባ ተከታትሎ መፍትሔ ያፈላልግልን ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ የነበራቸው የእቴቴ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋ ታደሰ፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ እየከፈለ ያለው ዋጋ በመንግሥት የአሠራር ችግር ከግብዓት አቅርቦት አለመኖርና ከዋጋ ግሽበት ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ የዋጋ ግሽበቱ አገራዊ ቢሆንም ‹‹የግንባታ ሥራ ተቋራጮች እየገጠማቸው ያለውን ማነቆ መንግሥት የረሳው ይመስላል፤›› በማለት የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከውጭ መጥተው ግንባታ ለተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች ከሚያደርገው ድጋፍ በትንሹ እንኳ ማድረግ አልቻለም ብለዋል፡፡

እቴቴ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከ2,000 በላይ ሠራተኞች እንደነበሩት አስታውሰው፣ አሁን ከ400 የማያንሱ ሠራተኞች መቀነሳቸውንና ችግሩ ከቀጠለ ለቀሩት ሠራተኞች ለመክፈል አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ተስፋ ገለጻ አብዛኛዎቹ ሥራ ተቋራጮች የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን እየገነቡ መንግሥት የሠሩበትን ክፍያም ሆነ ሌላ ወጪያቸውን ለመክፈል አልቻለም፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ መሐንዲሶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር)፣ በአሁኑ ጊዜ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴው ሲታይ ብዙዎች ሥራ እንዳቆሙ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ማግኘት የነበረባቸውን ክፍያ ባለማግኘታቸው ምክንያት መካሰስ የጀመሩም እንዳሉ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ የኮንስትራክሽን ግብዓት ዋጋ ግሽበትና አቅርቦት እጥረት ከኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተዳምሮ እንደ ትልልቅ ፋብሪካዎች የሚቆጠሩ የሥራ ተቋራጮች ያሉበት ሁኔታ ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን፣ መንግሥት ከድርጅቶቹ ጋር በመሆን ያለውን ችግር በመፍታት ለአገር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ እንዳለባቸው፣ እግረ መንገዱንም ተቋራጮችም ችግራቸው ሊፈታ ይገባል ብለዋል።


https://www.ethiopianreporter.com/index ... icle/20840