
ከህወሓት የተረዳነው ባህሪ አንዱ፣ ህወሓት ማለት የተወሰኑ ቡድኖች ናቸው:: ህወሓት ከህዝቡ ጋር የለም:: ምናልባት የተወሰነ ህዝብ ነው ከህወሓት ጋር ያለው፡፡የተወሰነ ህዝብ ደግሞ በመቐሌ ከተማ እና ዙሪያዋ ያሉ ጥቂት ሰዎችን የሚመለከት ሲሆን፤ ሌላው ቀርቶ ወደ አድዋና አክሱም ስንሄድ እውነት ለመናገር ህዝቡ የሚያሳዝን ህዝብ ነው::

ሰፊው የትግራይ ህዝብ አንደኛ፣ በአሁን ጊዜ በዚህ ዘመን ለእግሩ እንኳን ጫማ የሌለው ህዝብ ነው:: ልብስ በረከሰበት በዚህ ወቅት ልብስ እንኳን መልበስ ያልቻለ ህዝብ ነው::

ይህ ደግሞ ጥቂት የህወሓት አመራሮችና አባላት ገንዘቡንም ለራሳቸው፤ አገሩንም የራሳቸው አድርገው እንደያዙት የሚያሳይ ነው፡፡:

የትግራይ ህዝብ በኢኮኖሚው አሁንም ወደኋላ የቀረ ነው:: የኢኮኖሚው ችግር ደግሞ ከምግብ እስከ አልባሳት በሚፈልገው ልክ እንዳያገኝ ያገደው ህዝብ ነው::

ከዚህ በተቃራኒው ግን ጥቂት የህወሓት አባላትና ወደ ህወሓት የሚጠጉ ሰዎች ግን የናጠጠ ኑሮ ይኖራሉ፡፡

ጥቂት የህወሓት አመራሮችና እነርሱን ተጠግተው ያሉት ግን በጣሙን ከህዝቡ የራቀና ሊነጻጸርም በማይችል የናጠጠ ኖሮ ውስጥ ነው ያሉት:: በትላልቅ ሆቴሎች ነው የሚዝናኑት:: ህዝቡ ግን አሁንም ጭንቀት ውስጥ ነው ያለው::

እኔም ትግሬ ሁሉ የተጠቀመ፤ ትግሬ ሁሉ የህወሃት አባል የሆነ አድርጌ ሳይ የነበረበት ሁነት የተሳሳተ መሆኑን አይቼ በመገንዘብ፤ ይሄን ምስል ያስያዘኝ የህወሓት አሳሳች የሴራ ምስል መሆኑን በተግባር አረጋግጫለሁ፡፡

መቐሌ ካለው የህወሓት ስብስብ ጋር ያለን አጋርነት በፋይናንስ ነው:: እኛ ወደመቐሌ ስንሄድ የአውሮፕላን ትኬት ተልኮልን፣ ሆቴል ተይዞልን፣ ሌሎችም አስፈላጊ ወጪዎች ተሸፍኖልን የሁሉንም ፓርቲዎች አበል፣ የአዳራሽ ኪራይ፣ ትራንስፖርት፣ ሆቴል፣ ምግብና ሌሎችን ወጪዎች የሚሸፍነው ህወሓት ነው፤

እኛ ከገዢው ፓርቲ ጋር መደጋገፍም ሆነ ተቃውሞ ቢኖረንም በአገር ጉዳይ አንድ በመሆናችን የህዳሴ ግድቡ የሁላችንም ጉዳይና ፕሮጀክት እንደመሆኑ ይሄንን የሚመለከቱ ማናቸውንም ጉዳዮች ብሎም ከውጪ የሚመጡ ተቃውሞዎችን ከመንግስት ጎን ሆነን ለመከላከል ነው፡፡

ስለ ህዳሴው ግድብ ያገባናል ብለን ሁላችንም ፓርቲዎች ስንናገር፤ ህወሓት ስለሱ ጉዳይ መንግስትን እንጂ እኛን አይመለከትም ማለቱ ነው::

ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሀብት ስለሆነው ግድብ አያገባንም ብሎ መናገር አግባብነት የሌለው ነገር ነው፣

ለጨፍላቂነቱ ማረጋገጫ የሚሆነው ደግሞ፤ እነዚህ ሁሉ ፓርቲዎችና ምርጫ አናካሂድም በሚሉበት ወቅት ህወሓት አካሂዳለሁ ማለቱ የራሱን የበላይነት ለማንጸባረቅ የሚያደርገው ድርጊት ነው::

ህወሓት የዘረፈውን ወደ አውሮፓና መሰል አገሮች ከማሸሽ የዘለለ ለህዝቡ የሰራለት ነገር የለም::

በተለይ በትግራይ ያለው የገጠር ህዝብ ስለ ህወሓት መሰሪነትና ተንኮል በደንብ ተረድቷል:: የትግራይን ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠል የሚያደርገውንም አካሄድ ተገንዝቧል:: ይሄን የተገነዘበ ህዝብ ደግሞ ህወሓትን በቃህ ሊለው ይገባል::

የትግራይ ተወላጆችና የትግራይ ህዝብ ደግሞ በዚህ ረገድ ትልቅ ድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል:: የትግራይ ወጣቶች፣ የትግራይ ምሑራን፣ በትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ህወሓትን በቃህ ሊሉት ይገባል::

የትግራይ ህዝብ የህወሓትን አመራሮች እዚህ ጋር በቃችሁ ሊሏቸው ይገባል፡፡እነዚህ አመራሮች የራሳቸውን ሀብት አካብተዋል:: ይህ ሀብት ደግሞ በመቐሌ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ጭምር ከህንጻ እስከ ተሽከርካሪ የሚገለጽ ሀብት ነው:: በክልሉ ደግሞ ለእለት ጉርሱም ሆነ ለእግሩ ጫማ እና ለሰውነቱ ልብስ መለወጥ ቀርቶ ማሟላት ያቃተው ህዝብ (በተለይ ገጠሩ) ተፈጥሯል::

እነዚህ አመራሮች እውነትም ለዚህ ህዝብ ታግለንለታል ካሉ ያ ህዝብ ነጻ መውጣት ነበረበት:: ቢያንስ ትንሽ እንኳን መሻሻል ማሳየት ነበረበት::

ህወሓት 27 ዓመት ኢትዮጵያን ሲገዛና ሀብቱን እንደፈለገው ሲያሽከረክር ለእኛ ለትግራይ ህዝቦች ምን አደረገ? ብለው ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው:: ምክንያቱም እነዚህ ቡድኖች ዛሬ ችግር ሲመጣ ወደዛ ተሰበሰቡ እንጂ አካባቢውን እንኳን ሄደው አይተው የማያውቁ ብዙዎች ናቸው::

እናም በዚህ መልኩ አካባቢያቸውን በልማት ማገዝ ቀርቶ በአካል ሄዶ መመልከት ሳይችሉ የኖሩ አመራሮች፣ ዛሬ ችግር ሲገጥማቸው ወደ ህዝቡ ገብተው ህዝቡን ለሌላ ጭንቀት ይባስ ብሎም ከሌላው ህዝብ ለመነጠል የሚያደርጉትን ጥረት በግልጽ ይታያል::

የትግራይ ህዝብ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ሁሉ የሚፈልገውን ፓርቲ ደግፎ የነጻነት አየር መተንፈስ መቻል አለበት፡፡
Ø ህወሓት እንደሚያወራው ለብሔር ብሔረሰቦች የሚሰራው ስራ የለም:: ይልቁንም ለራሱ ጥቅምና ስልጣን ማስቀጠያ በሚያመች መልኩ እንጂ ለክልሉ ህዝብም ሆነ ለክልሉ የተሻለ እድገት ሲል ያከናወነው ነገር አይታይም::

የትግራይ ህዝብ በድህነት ውስጥ ያለ፤ የነጻነት አየርን በወጉ ያላጣጣመና በአፈና ውስጥ ያለ፤ ዛሬም ቢሆን ከስጋት ያልተላቀቀ ህዝብ ነው::

በመንደር ካሰብን እንደ ህወሓት ተመልሰን እንገባለን:: እናም እንደዛ ማሰብ የለብንም:: እኛ የተለያየን ቢሆንም ለአንድነት ነው የምንታገለው::

ህወሓት ምርጫ ይካሄድ ብሎ የሚያወራው ለህዝቡ አስቦ አይደለም፤ ለራሱ ነው:: ይሄም ለራሱ አፍኖ በያዘው አካባቢ ለቀጣይ አምስት ዓመት ቀጣይ ኮንትራት ለማግኘት እና ያንን ዋስትና ለመያዝ ነው:: ይሄ በዚህ ጊዜ ምርጫ ይካሄድ ማለት ደግሞ ለህዝብ አለማሰብ ነው::

ስለ ምርጫ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለይበት ሁኔታ የለውም:: የትግራይ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ እስከሆነ ድረስ ህወሓት ብቻውን ተነስቶ ምርጫ ላካሂድ ማለቱ ለምንድን ነው? የሚለው በራሱ መታየት ያለበት ነው::
ምንጭ አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም
