Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Ejersa
Member
Posts: 3978
Joined: 05 Nov 2019, 10:39

ወያኔ እንዴት ራሷን በ15 ቀን ሲጥ አድርጋ እንደምትገድል እዩልኝ!

Post by Ejersa » 10 Apr 2020, 17:40

የኢፊድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጁን ሰምተን ዞሮ ስንል ከወደ ትግራይ ተመሣሣይ ዜና ተሰማ። ህወሓቶች አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ ከሳምንታት በፊት በትግራይ ክልል ላወጡት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ዝርዝር (ተጨማሪ) የአፈፃፀም መመሪያ ማውጣታቸውን ገለፁ። እያንዳንዱ ክልል በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ የህዝብ ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ወረርሽኝ ሲከሰት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የማወጅ ስልጣን አለው። ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ ለትግራይ ክልል ቀርቶ ከኢትዮጵያም፣ አፍሪካም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተ ወረርሽኝ ነው። የትግራይ ክልል ከሁሉም ክልሎች ቀድሞ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያነሳሳቸው የተለየ ምክንያት የለም። ከዚያ ይልቅ ልዩነቱ ያለው "ህወሓት" የሚባል ጨጎጊት የሆነ የማፊያ ቡድን ላይ ነው። ለምሳሌ ከሁሉም ክልሎች ቀድሞ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያወጀው የትግራይ ክልል ቢሆንም የአዋጁ አፈፃፀም የሚመራበት መመሪያን አላዘጋጀም። ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ አዘጋጅቼያለሁ ቢል እንኳን የአዋጁን አፈፃፀም በበላይነት የሚቆጣጠር "ቦርድ/ኮሚቴ" አላዋቀረም።

በዚህ መሠረት ከሳምንታት በፊት ተንቀልቅለው ያወጡት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን፤ አንደኛ ተግባራዊ አልተደረገም፣ ሁለተኛ፦ አድርገናል ካሉም (መቼም ውሸትና ጉራ ልማዳቸው ነው) በክልሉ ህገመንግስት ላይ በተደነገገው መሠረት አፈፃፀሙን በበላይነት የሚቆጣጠር ቦርድ/ኮሚቴ አላቋቋሙም። በምትኩ ያዋቀሩት ምንድነው? ኮማንድፖስ "ሞኝ ሰው አንድ አይነት ጨዋታ ነው የሚችለው" አለ መለስ ዜናዊ። ገና "የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ" ሲባል ዓይናቸው ላይ መጥቶ ድቅን የሚለው ኮማንድ ፖስትና ጥይት ነው። ከምሬ እኮ ነው። የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ብለው ተንቀዥቅዠው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጥተው ኮማንድ ፖስት በአቋቋሙ ማግስት አንድ ምስኪን ወጣት ነው መቀሌ ላይ በጥይት የገደሉት።

የኢፊድሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በሚያካሂደው ስብሰባ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን እንደሚያፀድቀው ሲሰሙ ደግሞ ሌላ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ወደ ከውጪ ሀገር ሆነ ከሌሎች ክልሎች የሚገቡ ሰዎች በሙሉ "ለ14 ቀን ኳራንቲን እንዲደረጉ ወስነናል" አሉ። ወደ ትግራይ ክልል የሚገቡ ሰዎች ለ14 ቀን ኳራንቲን እንዲደረጉ መወሰን መብታቸው ነው። ነገር ግን የፌደራሉ መንግስት ያወጣው አዋጅ የበሽታውን ስርጭትና ሁኔታ እያየን የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይወስናል ብሏል። ክልሎች በራሳቸው ያወጡት አዋጅና የፌደራሉ መንግስት ያወጣው አዋጅ የሚጣረሱ ከሆነ ምን ይደረጋል ተብለው የተጠየቁት የፌዴራል ዋና አቃቤ ህጉ በክልል ደረጃ የሚወጡ አዋጆች ከፌደራሉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ጋራ የሚጣረስ መሆን እንደሌለበት ገልፀዋል። በዚህ መሠረት ወደ ትግራይ ክልል የሚሄዱ ሰዎች ለ14 ቀናት ኳራንቲን የሚደረጉ ከሆነ በተመሣሣይ ከትግራይ ክልል ወደየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚጓዙ መንገደኞች በራሳቸው ወጪ ለ14 ቀናት ራሳቸውን ኳራንቲን ለማድረግ ወስነው መምጣት አለባቸው። ስለዚህ ከትግራይ ክልል ተነስቶ በወልዲያ፣ በሰመራ፣ በጎንደር፤ በአውሮፕላን ሆነ በመኪና፣ በፈረስ ሆነ በበቅሎ፣... የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ተገታ ማለት ነው። ስለዚህ ከውጪ ሀገር ሆነ ከመሃል ሀገር ወደ ትግራይ ክልል የሚገባ ሸቀጣሸቀጥ፣ ነዳጅ፣ የኢንዱስትሪ ምርት፣ ሰው፣ ከበት፣ ዶሮ... ወፍ የለም። በዚህ መልኩ ለአንድ ወር ከዘለቀ ትግራይ ራሷን በራሷ አፍና ገደለች ማለት አይደለም? ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የVOA ጋዜጠኛ ላነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የህወሓት ባለስልጣን "የፌዴራሉ መንግስት ያወጣው አዋጅ ግልፅ አይደለም። ዓላማው በራሱ በሽታን ለመከላከል አይመስልም" ብሏል። እኔ የምለው እነዚህ ሰዎች መቼ ነው የሚሰለጥኑት? መቼ ነው እንደ ምክንያታዊ ፍጡር ነገሮችን አርቆ ማሰብና ማገናዘብ የሚጀምሩት? እንደው እድሜ ልክ የፖለቲካ ደንቆሮ ሆነው እስከመቼ ይዘልቁታል?

ከውጪ ሀገር ሆነ ከሌሎች ከልሎች የሚገቡ ሰዎችን ኳራንቲን እናደርጋለን ሲሉ የአማራና አፋር ክልሎች ተመሣሣይ እርምጃ ቢወስዱ በሶስትና አራት ሳምንት ውስጥ ራሳቸውን ሲጥ አድርገው ገደሉ ማለት አይደለም? አሁን እንዲህ ሲሏቸው "የትግራይ ህዝብ ለራሱ አያንስም" ብላ ብላ ቅብርጥስ ማለታቸው አይቀርም። ነገር ግን እንኳን የትግራይ ክልል በሀገሪቱ ከዳር እስከ ዳር የተንሰራፋው የኦሮሚያ ክልል ያለ #መርካቶ አንድ ወር አይኖርም። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልቡ ያለው አራት ኪሎ ሳይሆን መርካቶ ነው። አንድ ክልል ከአራት ኪሎ ተጣልቶ እንደምንም ተገዳድሮ ሁለትና ሶስት ወራት ትንፋሹን ሊያራዝም ይችላል። ነገር ግን ከመርካቶ ጋር የተቆራረጠ ክልል የደም ቧንቧው የተቆረጠ ነው። ህወሓት ሺህ ግዜ ቢፍጨረጨር የትግራይ ህዝብ ያለ ስኳር ሻይ አይጠጣም፣ ዘይት የሌለው ወጥ አይበላም፣ ያለ ጤፍ እንጀራ "ፈታ" ብቻ እየበላ ሶስት ቀን አያድርም። እናንተን እንደ ህፃን እያባበሉ መኖር እንዴት እንደሚሰለች ብታውቁ ኖሮ ቆም ብላችሁ ማሰብ ትጀምሩ ነበር።