ከሚሴ የገባው የህወሀት ሃይል በተባበረው የኢትዮጵያውያን ክንድ ተደቁሶ በየጥሻው ወድቆ ቀርቷል። ፈጣሪውን ህወሀትን ተማምኖ፣ በስሙ እየማለ ለህወሀት መስዋዕትነት ሲያስጨፈጭፍ የከረመው ሸኔ ያለአቅሙ ከኢትዮጵያ ኮማንዶ ጋር ገጥሞ ለወሬ ነጋሪ እንዳይቀር ሆኖ መወገዱን ዘግይቶ ከመከላከያ አከባቢ ያገኘሁት መረጃ አረጋግጦልኛል። የኮምቦልቻ መስመር ሲዘጋበትና እንደረመጥ ሲያቃጥለው መሽሎኪያ ፍለጋ ሰሜን ሸዋ ምንጃርና መንዝ የገባው ጥቂት የህወሀት ጀሌ አንድ ነፍስ ሳይተርፍበት በገባበት ቀርቷል። አሁንም እንደአይጥ ጉድጓድ ለጉድጓድ እየተሽሎኮሎከ ሞቱን በገዛ እጁ እየተጋታት ይገኛል።
በሰሜን ወሎ ያለው ሁኔታም ፍጹም እየተቀየረ ነው። በርካታ አከባቢዎች በኢትዮጵያ ሀይሎች እጅ መግባታቸው ታውቋል። ደሴና ኮምቦልቻ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት የሚሰማ መልካም ነገር እንደሚኖር እጠብቃለሁ። አሁን ባለው ሁኔታ የህወሀት ጀሌ ደሴና ኮምቦልቻ መቆየት የሚፈልግ አይደለም። እየመጣበት ካለው ህዝባዊ ሱናሚ የሚተርፍ እንዳልሆነ ተረድቶታል። ከሸኔ ጋር ከሚሴ ላይ ለመፍጠር ያቀደው ጥምረት ከተበላሸበት ወዲህ ወደፊት መራመድ እሳት፣ ወደኋላም መመለስ እሾህ ሆኖበታል። ነፍሱ ከወሎ ምድር ላይ እየቃተተችበት ወደ አሜሪካና አውሮፓ አንጋጦ የድረሱልኝ ልመና ላይ ይገኛል።
በአፋር ጀግኖች ብድራቸውን በልኩ እየመለሱ እንዳለም መረጃዎች ያመለክታሉ። ጭፍራን ነጻ ያወጡት የአፋር ልዩ ሃይል፣ ሚሊሺያና የምስራቅ ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በድል ጎዳና ታሪክ እየሰሩ ቀጥለዋል። አሁን የህወሀት ትርፍራፊ ሃይል ባቲ ላይ እየተሰባሰበ እንደሆነ ይነገራል። ምሱን ቀምሶ፣ አከርካሪው ተመቶ እዚያው በገባበት እንደሚቀር አልጠራጠርም። በአጠቃላይ የግንባሮች ውሎ ለኢትዮጵያውያን ተስፋ፣ ለህወሀትና ደጋፊዎቹ ጽልመት ሆኖ በአንጸባራቂ ድል ታጅቦ እንደቀጠለ ነው።
በደጀንና በማሰልጠኛ ካምፖች የሚታየው መንፈስ ደግሞ ኢትዮጵያ ተአምረኛ፣ ሲነኳት ቀፎው እንደተነካ ንብ የሚተም፣ ስለ ሀገር የትኛውንም ዋጋ የሚከፍል፣ እንደትላንቱ እንደጥንቱ ኢትዮጵያን ለመድፈር የመጣን ጠላት በህብረትና አንድነት አሳፍሮና ትምህርት ሰጥቶ የሚመልስ ህዝብ እንዳላት ለጠላትም ለወዳጅም ያረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል። በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተደረጉት ህዝባዊ ትዕይንቶች ለውስጥ ጎጠኞችና ሶላቶ ባንዳዎች ብቻ ሳይሆን ለነጮች የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ምኞት ግልጽ መልዕክቶች የተላለፉባቸው ናቸው። በአዲስ አበባው ትዕይንተ ህዝብ የወ/ሮ አዳነች አቤቤ ንግግር ወኔ ቀስቃሽ፣ ልብ የሚያሞቅ፣ የሀገር ፍቅር አጉልቶ የሚሳይ ነበር። ወ/ር አዳነች በተደጋጋሚ በየመድረኩ እያደረጉ ያለውና ብርታት፣ ጉልበትና ተስፋ የሚሰጡ ንግግሮች በጣም ወሳኝ ናቸው። የእሳቸው ከውስጥ የሚፍለቀለቅ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ስሜት በአርአያነት ተወስዶ ሌሎችባለስልጣናትም በየዕለቱ በአገኙት አጋጣሚ ሊያደርጉት ይገባል።
እዚህም እዚያም የደጀኑ ሃይል ተነቃንቋል። በውጭም በውስጥም ያለው ኢትዮጵያዊ በአንድ ድምጽ፣ በአንድ መንፈስ ተነስቷል። በየከተሞቹ በግንባር ለሚዋደቀው ወገን የሚደረገው ድጋፍ ለጠላት ሃይል ወሽመጥ የሚቆርጥ፣ ለምዕራባውያን ሀገራት እጃቸውን እንዲሰበስቡ የሚያደር መሆኑን እየታዘብን ነው። ድምጻውያን በየማሰልጠኛ ካምፑ ተገኝተው የሚያቀርቧቸው ወኔ ቀስቃሽ የሙዚቃ ዝግጅቶች ለግንባሩ ድል ሚናቸው ከፍተኛ ነው። በውጭ ሀገራት ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች የሚኖሩባችውን ሀገራት መንግስታት በማስጨነቅ የህወሀትን የጥፋት አጀንዳ ከመደገፍና ከማራገብ እንዲቆጠቡ እያሰሙ ካሉት ያልተቋረጠ ተቃውሞ ባሻገር ለተፈናቃይ ወገናቸውና ለመከላከያ ሰራዊት እያደረጉ ያሉት የገንዘብ ድጋፍ የደጀኑ ወገን ቁርጠኝነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነው። በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንም በሽብር ወሬ ኢትዮጵያን ሊያተራምሱ የተነሱ ሚዲያዎችን እግር በእግር እየተከታተሉ በማጋለጣቸው CNN እና BBC መሰል የምዕራባውያን ልሳኖች ጭንቅ ውስጥ መግባታቸው በራሱ ትልቅ ድል ተደርጎ መመዝገብ ይኖርበታል።
የግንባሩና የደጀኑ ቅንጅት በሀገራዊ ፍቅርና ወኔ ተቃኝቶ ኢትዮጵያን ለማዳን በመረባረብ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ሃያላኑን፣ ጉልበተኞቹን ሀገራት ለመቋቋም የሚያስችላት የዜጎቿ አንድነት ከምግዜውም በላይ ተጠናክሮ መጥቷል። ትላንትም አልተንበረከክንም። ያን ጊዜም ለሃያላኑ እጅ አልሰጠንም። በደም በአጥንታችን እንደትላንት ጥንቱ በዚህ ዘመንም ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዢዎች አንገቷን የማትሰብር፣ ለጉልበተኞች የማትንበረከክ መሆኗን ይህ ትውልድ በነቂስ ሆ ብሎ ተነስቷል። እንበርታ!