በስተመጨረሻም ይዟቸው መጥቷል!
ኦህዴድ በአዲስ ጉዳይ ተቃውሞ ሲገጥመው "ጉዳዩ በሽምግልና ተይዟል" አለ እንደ ጎረቤት ጠብ። በዚህም ሳያበቃ በስብሰባው ተቃውሞ ያነሱበት ተሳታፊዎች ዘንድ ሽማግሌ እልካለሁ አለ። "ሽማግሌ የሚባል እንዳይመጣብን" አሉ በኦህዴድ ላይ ተቃውሞ ያስነሱት ተሳታፊዎች።
በመጨረሻም እነዛን "ሽማግሌ" የተባሉ በሚዲያ እያመጣ "ሰላም ወዘተ" እያስባለ ነው። አዲስ አበባ የሁሉ ኢትዮጵያዊ ስትሆን ሰላም የሚጠፋ፣ የኦሮሞ ስትሆን ሰላም የሚሰፍንባት አድርጎ ኢትዮጵያውያንን መርገምን ስራቸው አድርገውታል። ኦህዴድ በመከባበር የምትታወቀውን ሀረርን ሀውልቶቿ አፍርሶ በህይወት ያሉትንም እየገደለ ስሟን እንዳበላሸው፣ አይደለም ኢትዮጵያዊያንን ጃማይካዎችን ጨምሮ የሌሎች አገር ዜጎች በሰላም ይኖሩባት የነበረችውን ሻሸመኔን የደም ምድር እንዳደረገው አዲስ አበባንም የዘር ፍጅት ማዕከል ማድረግ ነው የፈለገው።
በሴራ፣ በገንዘብ፣ በማታለል፣ በማስፈራራት ሳይችል ሲቀር በሽማግሌ ስም መጥቷል። ተወያዮቹን በሽማግሌ ማታልል አልቻለው ሲል ወደ ህዝብ አምጥቶ ሊያወናብድ ነው።
አብዛኛዎቹ ደግሞ ኦህዴድን ደግፈው የቆሙ ናቸው። ሽማግሌ ሳይሆኑ በእምነትና ሽምግልና ስም ለኦህዴድ የሚያግዙ ናቸው!
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ
*****
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤
የተከበርከው የአማራ ሕዝብ፤
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ዙሪያ የተሄደባቸውን መንገዶች፣ የታዩ መዋቅራዊ ግድፈቶችን፣ የመርህ ጥሰቶችን፣ እንዲሁም ሀገራችን ያለችበትን አጠቃላይ የፖለቲካና የደህንነት ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
የሕዝብ ጥሪ እና የአቋም መግለጫ ነጥቦች፤
አብን ወደ ሀገራዊ ምክክሩ የገባው የኢትዮጵያን ጥልቅ የፖለቲካ ችግሮች በኃይል ሳይሆን በውይይት፣ በጫና ሳይሆን በመደማመጥ፣ በአንድ ወገን የበላይነት ሳይሆን በድርድርና በጋራ መግባባት፣ እንዲሁም አንዱ አሽናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት ሳይሆን ሁሉንም ወገን አሽናፊ በሚያደርግና ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ባደረገ የሰጥቶ መቀበል መርህ ለመፍታት የሚያስችል እውነተኛ ሀገራዊ መድረክ ይፈጠራል በሚል እምነት ነበር።
ሆኖም በሂደቱ ውስጥ የታየው ሁኔታ ከተራ የአሠራር ግድፈት ወይም ከመደበኛ የፓለቲካ ልዩነት የዘለለ ሆኖ አግኝተነዋል። የምክክር ሂደቱን ተዓማኒነት፣ አካታችነት፣ ገለልተኝነት እና ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ተደጋጋሚና የተደራጁ ጥፋቶች ተፈጽመዋል። በገዢው አካል የተፈጸሙ መዋቅራዊ ጥሰቶች፣ ጫናዎች እና ወገንተኛ አካሄዶች ምክንያት ሂደቱ የሚጠበቅበትን ያህል ውጤታማ እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋት ደቅነዋል።
በዚህ ረገድ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ካጋጠሟት ውስብስብ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፈተናዎች መካከል አሁን ያለንበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄና አስተዋይነትን የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አኳያ የሚከተሉት መሠረታዊ ጉዳዮች በጥንቃቄ እንዲታዩ እናሳስባለን።
1. የአዲስ አበባ ህዝብ ውክልና እና የራስ-አስተዳደር መብት፣
በምክክሩ ሂደት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ህልውና፣ ባለቤትነት እና የራስ-አስተዳደር መብት ዙሪያ የታየውን የክህደት ተግባር በትኩረት መከታተል ያስፈልጋል። በከተማዋ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ባለቤትነትና ተጓዳኝ የፖለቲካ እና የህግ ማዕቀፎችን በሚመለከቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚመከርበት መድረክ ላይ በበርካታ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ድምፅና ፍላጎት ባግባቡ ሳይወከልና የከተማዋ ሕዝብ እንደ ዋና ባለቤት (Body Politic) ሳይቆጠር መታለፉ እጅግ አሳሳቢ ገመና ሆኖ ተመዝግቧል።
የከተማዋን ነዋሪዎች መብትና ዘላቂ ጥቅም ያስከብራሉ ተብለው የተወከሉ አካላትም የተጣለባቸውን አደራ በመዝንጋት የአንድን ወገን አካል ያልተገራና ድንበር የለሽ ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሉ የከተማውን ህዝብ መብትና ጥቅም አሳልፈው ሲስጡ ተመልክተናል።
ይህ ተግባር በኢትዮጵያ አግላይ የብሔር ፌደራሊዝም ከተዘረጋበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም የቆየው ተከታታይ የመብት ገፈፋ እና የማግለል ሂደት የመጨረሻው ምዕራፍ ማሳያ ነው። በመሠረቱ ህብረ-ብሔራዊና ኮስሞፖሊታን ውቅርና ገጽታ ያለው የአዲስ አበባ ሕዝብ ለአግላይና ዘውጌያዊ የፖለቲካ ሥርዓት የማይመጥን (misfit) ተደርጎ ተስሏል። እጅጉን ያሳዘነን አሁን ያለው መንግሥትም ስለ መደመር፣ ስለ ለውጥ፣ ስለ ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እና ስለ ኢትዮጵያዊነት ውህደት (synergy) ደጋግሞ እየሰበክ፤ በተግባር ግን ለአዲስ አበባ ሕዝብ ምንም ዓይነት ቦታና ዕውቅና የማይሰጠውን አግላይ ዘውጌያዊ ፖለቲካ ሙጥኝ ብሎ ለማስቀጠል መሞከሩ ነው።
ሆኖም ድርጅታችን አብን በጽኑ የሚያምነው የተዛባው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊከተለው የሚገባው ትክክለኛና ምክንያታዊ አቅጣጫ የአዲስ አበባን ገጽታ ወደ አግላይ ዘውጌያዊነት መለወጥ ሳይሆን፤ ይልቁንም የአዲስ አበባን ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ሞዴል በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች ላይ ማስፋፋትና ማፅናት እንደሆነ ነው። በእርግጥም "አንድነት በልዩነት" (Diversity in Unity) የሚባለው ታላቅ መርኅ በመሬት ላይ እውነተኛ ትርጉምና ሕይወት የሚያገኘው እነዚህ ሁለት መሠረታዊ ዕሴቶች በተግባር ተጣጥመውና ተዋህደው ሲተገበሩ ብቻ ይሆናል ነው።
ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ የከተማችሁን ህልውና እና መብት የሚመለከቱ ጉዳዮችንና በዚህ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶችን በከፍተኛ ንቃት እንድትከታተሉ፤ የራስ-አስተዳደርና የፖለቲካ መብታችሁን እና መጻኢ እድላችሁን በህጋዊ መንገድ ለማስከበር በአንድነት እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
2. ድብቅና መንታ የፖለቲካ ስልቶች፣ መዋቅራዊ ስጋቶች፤
ስርዓቱ በአደባባይ የሚይያስተጋባቸው የሀገራዊ አንድነት፣ የጋራ ብልፅግና፣ የዜጎች እኩልነት፣ የህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትና የመሻገር ዲስኩሮች በተግባር መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚጻረሩና ሰፊ ክፍተት ያለባቸው እንደሆኑ የምክክር ሂደቱ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል። አጠቃላይ የፖለቲካ ሂደቶቹን በጥንቃቄና በሚዛናዊነት ስንመረምር (Hermeneutics of Suspicion) በአንድ በኩል ስለ ሀገራዊ አንድነትና ወንድማማችነት እየተሰበከ፣ በሌላ በኩል መንግሥታዊ መዋቅሮችን ይየአንድን ቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያነት የማዋል ጥረት እንደሚደረግ በስፋት አስተውለናል።
ከአዲስ አበባ በመቀጠል ጎልቶ የወጣው የመንግስት አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች በምክክሩ መካከል ድንገት "በፓርላማ የሚመረጥ ፕሬዚደንት" ይሁን በሚል ያቀረቡት አማራጭ ነው። ለዚህም የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ በማጣቀስ ለማቅረብ ሞክረዋል። ነገር ግን ከንጽጽር ጥናት መርኅ አኳያ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከደቡብ አፍሪካ ሁኔታ ጋር ፍጹም እንደማይመሳሰል እየታወቀ የቀረበው ሃሳብ የምድብ ስህተት (category error) እንዳለበት በሂደቱ አስገንዝበናል።
እንደሚታወቀው ደቡብ አፍሪካ አካታችና ስኬታማ የፖለቲካ ሽግግር ያደረገች፣ ጠንካራ እና ነፃ የሲቪክ ማህበራት ያሏት፣ የዳበረ የዲሞክራሲ ባህልና ህገ-መንግስታዊ ስርአት የገነባች ሀገር ነች። ስለሆነም እነዚህ መሠረታዊ ተቋማዊና ፖለቲካዊ ባህሎች በበቂ ባልተገነቡባት ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ በይስሙላ እያጣቀሱ ለማቅረብ መሞከር የህዝብን ትኩረት ለማሳትና አምባገነንነትን በህግ ለማስፈን የሚደረግ ጥረት ነው።
በሌላ በኩል ድርጅታችን አብን ለሀገራችን የፕሬዚዳንታዊ ወይም ከፊል-ፕሬዚዳንታዊ ስርዓት አማራጭን ያቀረበ ሲሆን ዓላማውም ተወዳዳሪ ዕጩዎች የመላው ሀገሪቱን ዜጎች ድምፅ ለማግኘት ሲሉ ድንበር ተሻጋሪና አስተሳሳሪ የሆኑ ሀገራዊ የፖለቲካ (Cross-cutting & Unifying Politics) አጀንዳዎችን እንዲያራምዱ ያስገድዳል በሚል እምነት ነው። በገዢው አካል በኩል የቀረበው ግን በሂደት ስልጣንን በአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን እጅ ለማከማቸት እንዲያስችል ህጋዊ ሽፋን ከመስጠት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል።
በተጨማሪም ወደ አዲስ አበባ ጉዳይ ስንመለስ በአንድ በኩል ትልልቅ ሀገራዊና ቀጠናዊ አጀንዳዎችን ደጋግሞ በማስተጋባት፣ ሆኖም በተግባር የአዲስ አበባ ከተማን መሬትና አስተዳደር በተናጠል የመቆጣጠር ፍላጎት ታይቷል። ይህ አካሄድ ሀገራችንን ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ከማሸጋጋር ይልቅ የፖለቲካ ችግሮቻችንን ይበልጥ የሚያወሳስብ በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ሂደቱን በጥንቃቄ ሊከታተለውና ሰላማዊ ትግል ሊያደርግበት ይገባል።
3. የአብን አቤቱታዎች፣ የቀጠሉ ጥሰቶች እና ቀሪው የምክክር ሂደት፤
ድርጅታችን በምክክር ሂደቱ ውስጥ የታዩትን አግላይና አፋኝ አካሄዶች በዝምታ አላለፋቸውም። ይልቁንም በሂደቱ የታዩትን ያልተገቡ ጣልቃገብነቶችና ሕገ-ወጥ ድርጊቶች በጽናት በመቃወም የሚከተሉትን እርምጃዎች ወስዷል፦
ሀ/ ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሁለት ጊዜ መዋቅራዊ ግድፈቶች እንዲታረሙ የሚያስገነዝቡ ይፋዊ የአቤቱታ ደብዳቤዎችን አስገብተናል፤ ሁለት ጊዜ በጊዜያዊ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ተገኝተን በሂደቱ ላይ ያየናቸውን ስጋቶች በፊት ለፊት ውይይት አስረድተናል።
ለ/ ለገዢው የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የሚፈጸሙ ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የሚያሳስብ ደብዳቤ የጻፍን ሲሆን፣ ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአካል ተገናኝተን የተፈጸሙትን ጥሰቶችና አላስፈላጊ ጣልቃገብነቶች በመጥቀስ ባስቸኳይ እንዲታረሙና ሂደቱ እውነተኛ የምክክር ሂደት እንዲሆን ፓርቲው ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት በአጽንኦት አሳስበናል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ እነዚህን መሠረታዊ ግድፈቶች ለማረም የተወሰደ አዎንታዊ እርምጃ አለመኖሩ እጅግ አሳዛኝ ነው።
እስካሁን ከታዩት አጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በመነሳት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊገነዘቡት የሚገባው ዋና ነጥብ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ አንድ እርምጃ ወደፊት በሄደ ቁጥር፣ ገዢው አካል የራሱን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያደርገው ስልታዊ ተፅዕኖ እና ጣልቃገብነት እየጨመረ እንደሚሄድ አሁናዊ ሁኔታዎች ያመላክታሉ። በተለይም ገዢው አካል በቁጥጥሩ ስር ያሉትን የፓርላማ፣ የህግ አስፈጻሚና የጸጥታ መዋቅሮች በመጠቀም ከምክክር መድረኩ የሚመጡ ምክረ-ሀሳቦችን በተዛባ መልኩ ወደ ራሱ የፖለቲካ መስመር ለማስገባት ሊሞክር ይችላል።
ሆኖም በዚህ ዙሪያ ያለንን ጽኑ አቋም ዳግም በመግለጽ እነዚህ መዋቅራዊ ጥሰቶች የሚቀጥሉ ከሆነ፣ እንዲሁም አንድ ወገን ብቻውን የሚወስንበት፣ አግላይና አምባገነናዊ ስርዓትን የመጫን እንቅስቃሴ የማይቆም ከሆነ ድርጅታችን አብን በከፍተኛ ንቃትና ብስለት ሂደቱን ከመከታተል ባለፈ፤ አሁንም ይሁን ወደፊት ለእንደዚህ ዓይነቱ የይስሙላ የፖለቲካ ድራማ (Facade) ፈጽሞ እውቅና የማይሰጥና የማይተባበር መሆኑን በአጽንኦት እንገልፃለን።
ከፊታችን ያለው መንገድ ፈታኝ ቢሆንም፤ ያሉትን ክፍተቶች ለማስተካከልና አገራዊ መግባባቱን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ለማስኬድ የተሻለ የፖለቲካ ንቃት፣ ጥንቃቄና ብርቱ ሰላማዊ ትግል ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን። በመሆኑም ህዝባችን በቀሪዎቹ የምክክር ምዕራፎችና በቀጣይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃትና በተደራጀ መንገድ እንዲሳተፍ ጥሪ እናደርጋለን።
4. ለሚዲያዎች የቀረበ ማሳሰቢያ፤
ሀገራዊ ምክክሩ አሁንም እየተካሄደ ባለበትና ድርጅታችን አብን የተፈጸሙትን ጥሰቶችና መዋቅራዊ ግድፈቶች ለኮሚሽኑ፣ ለገዢው ፓርቲና ለመላው ህዝባችን ይፋ ባደረገበት በዚህ ወቅት፤ አንዳንድ የግል ሚዲያዎችና የመንግስት ብዙኃን መገናኛዎች የተሳሳቱ ዘገባዎችን (Wrong Framing)፣ የተቀናጁ ሀሰተኛና አሳሳች መረጃ የማሰራጨት ዘመቻዎችን (Disinformation & Misinformation Campaigns) በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ሚዲያዎች ያቀረብናቸውን መሠረታዊ አቤቱታዎች አፋልሰው በማቅረብ፣ የገዢውን አካል አጀንዳዎች ብቻ በማቀንቀን፣ እስካሁን የነበረውን ሂደትና ውጤት ሆነ ብለው በተዛባ መልኩ በመዘገብ የቀረቡ ቅሬታዎችን ዋጋ ለማሳጣትና የገዢውን አካል የወደፊት የፖለቲካ ፍላጎት ህጋዊ ለማስመሰል የሚያደርጉት ጥረት መሆኑን ታዝበናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሚዲያወችን በተመለከተ በዚሁ የምክክር መድረክ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ሚዲያወች ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ እንዲሁም ገለልተኝነታቸውን የጠበቁ ሀገራዊ ተቋማት እንዲሆኑ ምክክር እየተደረገበት ባለበት ሰዓት፤ ይልቁንም ከዚህ በተቃራኒ ሚዲያወችን ለ misinformation እና disinformation ማሰማራት ድርብ ስህተት መሆኑን ታዝበናል።
በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእነዚህን ሚዲያዎች ወገንተኛና አድሏዊ አካሄድ በደንብ እንደሚያውቅና በንቃት እንዲከታተለው ለማስታወስ እንወዳለን። ሚዲያዎቹ ሚዛናዊና ነፃ የመረጃ ሽፋን የመስጠት ሙያዊና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን የዘነጉ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ከእንደዚህ ዓይነቱ አሳሳችና የአንድ ወገን አጀንዳን ለማስፈጸም ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ በጥብቅ እናሳስባለን።
5. ለገዢው አካል የቀረበ ማስታወሻ፤
ከስምንት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ፤ አምባገነኑን፣ አድሏዊውንና ዘውጌያዊውን የኢሕአዴግ ሥርዓት በመጣል አሁን ያለው መንግሥት ወደ ሥልጣን እንዲመጣ በተደረገው መራራ ትግል ውስጥ የአማራ ወጣቶችና መላው ሕዝባችን ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ታሪካዊ ተጋድሎ እና የከፈሉት መስዋዕትነት በግልጽ ሊታወቅና ሊታወስ ይገባል።
ነገር ግን ገዢው አካል ወደ ሥልጣን የመጣውም ሆነ ሥልጣኑን አስጠብቆ የቆየው በራሱ ጥረትና በአንድ ወገን ትግል ብቻ እንደሆነ አድርጎ የመተረክ ዝንባሌ ከወዲሁ መታረም ይገባዋል። የሕዝብን መራራ መስዋዕትነትና ታሪካዊ አደራ የመካድ እአካሄድ ከባድ የፖለቲካና የታሪክ ዋጋ እንደሚያስከፍል ገዢው አካል በጥብቅ ሊገነዘበውና ከእንደዚህ ዓይነት አሳሳች ስሜቶች ሊቆጠብ እንደሚገባ እንመክራለን።
6. ለተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ የቀረበ ጥሪ፤
የተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ፤ ድርጅታችን አብን በዛሬው ዕለት በከፍተኛ አክብሮትና በኃላፊነት ስሜት ጥሪ ያቀርብልሀል፤ በኦሮሞ ህዝብ ስም ጽንፈኛ ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ኃይሎች የሚያራምዱት የአካባቢያዊነትና የመገለል ፖለቲካ የሰፊውን ኦሮሞ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚያስከብር አይደለም።
በተለይ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ አንጡራ፣ የአንድነት ጌጥ እና የሉአላዊነታችን መገለጫ መዲና፣ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ እና የነዋሪዎቿ የራስ-አስተዳደር ማዕከል ሆና እንድትቀጥል አብን ያቀረበው ምክንያታዊ እና ሚዛናዊ የመፍትሔ ሀሳብ ለአማራ ህዝብና ለሌሎች ህዝቦች ብቻ ሳይሆን፣ የወንድም ኦሮሞ ህዝብን ዘላቂ ሰላምና ጥቅም ጭምር የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው።
ስለሆነም በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚደረግ ማናቸውም የብቸኛ ባለቤትነት ወይም የሌሎችን መብት የመጋፋት ፍላጎት፤ በህዝቦች መካከል የቆየውን ታሪካዊ ወንድማማችነት እና አንድነት የሚያበላሽ፤ በሂደትም የኦሮሞን ህዝብ የሚነጥልና የሚጎዳ የታሪክ ስህተት እንዳይሆን ለማሳሰብ እንወዳለን።
ድርጅታችን አብን፤ በአማራ ህዝብ ስም በአንዳንድ አካላት የሚሰነዘሩ ተመሳሳይ አክራሪ ፍላጎቶችን (Maximalist Claims) ውድቅ በማድረግ አሳታፊና ሀገራዊ መፍትሔዎችን ሲያራምድ እንደቆየው ሁሉ፤ የኦሮሞ ህዝብም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና በኦሮሞ ህዝብ ስም ፍላጎታቸውን በኃይል ለመጫን የሚሞክሩ አካላትን አቋም ውድቅ በማድረግ ለእውነተኛ የጋራ እድገትና ሰላም አብሮን እንዲቆም ታሪካዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
7. ለተከበርከው የአማራ ሕዝብ፤
በዚህ የምክክር ሂደት እንደታየው፤ በሀገራችን ውስጥ የሰፈነውና የተደራጀው ፀረ-አማራ (Anti-Amhara) ትርክትና መዋቅራዊ ጫና አሁንም አልተቀረፈም፤ ይልቁንም ተባብሷል። ይህንን ፈተና ለመሻገር ሰፊና የተደራጀ የቤት ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል። ስለሆነም በዚህ አሳሳቢ ወቅት መከፋፈል ለውድቀት የሚዳርግ መሆኑን ተረድታችሁ በአንድነት እንድትቆሙ እና በሕዝባችን መካከል ልዩነትንና ክፍፍልን የሚዘሩ አካላት ከዚህ ጎጂ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርጉ እያሳሰብን፤ አሁን ያለንበት ወቅት የውስጥ ልዩነቶችን የምናሰፋበት ሳይሆን፤ ለህልውናችንና ለእኩልነታችን በጋራ የምንቆምበት መሆኑን እንገልጻለን።
8. ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለኢፌድሪ መንግሥት የቀረበ ጥሪ፤
የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን የነበረውን የመጠራጠርና የመነቃቀፍ ፖለቲካ በማስወገድ፤ ለሀገርና ለህዝብ ዘላቂ ጥቅም ሲባል በጋራና በስፋት እንድንሰራ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ገዢው አካል ይህንን ሀገራዊ የምክክር እድል ለቡድን ስልጣን ማጠናከሪያ ከመጠቀም ይልቅ ሀገርን ወደ ዘላቂ ሰላምና ወንድማማችነት ለመምራት እንዲጠቀምበት፤ በሀገርራችን ውስጥ ያለው የፖለቲካና የማህበራዊ ክፍፍል ጥልቅ መሆኑን ተረድቶ እውነተኛ የፖለቲካ መታረቂያ መንገድ እንዲከተል በጋራ እንድንታገል ጥሪ እናስተላልፋለን።
9. የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤
አብን የሕዝባችንን ታሪካዊ አደራ በመሸከም፤ መዋቅራዊ መሰናክሎችን በጽናትና በበሰለ መንገድ በመታገል እውነተኛ ፍላጎቱን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል። የጀመርነው የፍትህ፣ የእኩልነት እና የነፃነት ትግልም የሕግ የበላይነትና እውነተኛ ዴሞክራሲ እስከሚረጋገጥ ድረስ በጽኑ ሰላማዊ መንገድ ትግሉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እናረጋግጣለን።
ለሀገራችን የፖለቲካ ቀውስ ዘላቂ መፍትሔው እውነተኛ ምክክር፣ ድርድርና ወንድማማችነት ብቻ ነው!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)**
ነሐሴ 09/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ