ጃዋር ሞሃመድ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ጠርዝ የያዙ አጀንዳዎች መነጋገሪያ ሆኖ የቀጠለ ሰው ነው! ከሜንጫ እስከ ውጡልን፣ ሌላ ጊዜ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያስጨንቀው፣ ሌላ ጊዜ የለውጥ ሞተር፣ በሌላ ወቅት ሁለተኛ መንግስት፣ ....እያለ ቀጥሏል። ጃዋር ከተለያዩ ኃይሎች ጋር ሆኖ የተለያዩ አጀንዳዎች አራማጅ ሆኗል። ባህርዳርና ኬሚሴ ላይ የሚናገረው የተለያየ ነው። አዲስ አበባና አምቦ ሆኖ የሚሰጠው መግለጫ ለየቅል ነው። በእነዚህ የተለያዩ መልኮቹ ተፅዕኖ ከመፍጠር ባለፈ ስልጣንን እንደጉድ ጅራቷን ያዝኩ፣ ደረስኩባት እያለ ተመልሷል። አሁንም እየሞከረ ነው!
ለውጥ መጣ እንደተባለ የለውጡ ካልኩሌተር፣ ምተር ወዘተ የሚሉ ማድመቂያዎቹን ተቀባብቶ በሰማኒያ ሚሊዮን ብር ግቢ ውስጥ ሁለተኛው መንግስት ነኝ ብሎ፣ አገዛዙም አንድ ጊዜ የኦሮሚያን ፕሬዝደንትነት፣ ሌላ ጊዜ የካቢኔ ስልጣን ይሰጠዋል እየተባለ በብልፅግና የፖለቲካ ተቋራጭነት ቆይቷል። የጃዋር ቤት አራተኛው ቤተ መንግስት ተደርጎ (ከአራት ኪሎ፣ የፕሬዝደንት ፣ ከእነ ከሽመልስ ቢሮ ቀጥሎ) የተለያዩ ክልሎች አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን እያገኘ የራሱንም የአገዛዙንም ፍላጎት ሲያስፈፅም ቆይቷል። ጃዋር ከደብረብርሃንና ደጀን ወደ አዲስ አበባ የሚወስዱትን ጨምሮ በአገዛዙ ፍላጎት መንገድ ከማዘጋት ጀምሮ በሌሎች ክልሎች (በተለይ አማራ) በርካታ በርካታ የአገዛዙ ፕሮጀክት ተቋራጭ ነበር። በዚህ ወቅት ከአገዛዙ ሳይርቅ ቀጣይ ቃል የተገባለት ስልጣን ነበር። ሁሉም በሚፈልጉት መንገድ አልሄደም።
በግሉ ሁለተኛ መንግስትነት ሲያዳግተው በኦፌኮ በኩል ሞክሯል። የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አስተባብራለሁ ብሎ ጥረት አድርጓል።
ከታሰረ በኋላ ትህነግ ወደ አራት ኪሎ ሲመለስም ጃዋር ሌላ ህልም ነበረው። የተወሰኑ የኦሮሞ ልሂቃን ከትህነግ ጋር ሆነው ከፊት እናመጣዋለን ብለው እንደነበር የተደበቀ ጉዳይ አይደለም። በእስር ወቅትም ሆነ እንደተፈታ ጃዋር "ጦርነትን እቃወማለሁ። ትብብርን እደግፋለሁ" የሚል ለስለስ ያለች አቋም ይዞ ነበር። ያ ወቅትም አለፈ።
ከእስር ከወጣ በኋላ በተለያዩ አገራት ዞሮ ከአገዛዙ ጎን ቁሙ ብሏል በይፋ ሰብኳል። አብይ ምን ያድርግ ብሎ ተከራክሯል። መሳሪያ ያነሳህ ሁሉ መሳሪያህን አውርድ ብሎ መክሯል። "ከእስር በኋላ ተምሬያለሁ"ወዘተ ብሎ ተማፅኗል። ግን ከአብይ ጋር ይተዋወቃሉ። "እባብ ለእባብ" እንደሚባለው ነው። አብይ አላመነውም። ጃዋር በእነዚህ ስልቶች የሚከተለው አብይ የሚወደውን ስልጣን ነው። የሚሮጡት ለተመሳሳይ ዋንጫ ነው!
ከእስር በኋላ እንደ ድሮው አዲስ አበባ ሆኖ የአብይን ኮቴ እየተከተለ ስልጣንን መጠበቅ አልቻለም። ቄሮ የሚለውን ኃይል በመፈክር ብቻ ማቆየት አይችልም። ሚዲያውን አዳክመው ቢሮ ዘግተዋል። እነአብይ መሬትና ቤትን ከባለቤቱ እየቀሙ ሰጥተውታል። ጃዋር ዱላ ይዞ ኮዬ ፈጨና መሰል አካባቢዎች ወጣቱ ኮኖዶሚኒዬም እየሰበረ እንዲገባ ራሱ ተገኝቶ መርቷል። እነ አብይ መስጠት የሚችሉትን ያህል ግን አይችልም። በኢኮኖሚ ጥቅም አራቁበት። ቀሪው ጫካ ገባ። ቀሪው ከአገዛዝ ጋር ጠረጠረው። ከዚህ ባሻገር በተለያየ መንገድ ያገኘው ሀብት ተያዘ። የአገዛዙ መዋቅርም ሆነ ሌላው ከጃዋር ጋር መገናኘት ወንጀል ተደረገበት። አጃቢም ሌላውንም እንደ ድሮው አያገኝም። ስለሆነም ሌላ መንገድ መሞከር ነበረበት። ከአራት ኪሎ በቅርብ ርቀት መሆን ባይችልም ኬንያ ለመቀመጥ አመቻቸ። እንደ ተሰዳጅ "ልዑልም" እንደ ተፅዕኖ ፈጣሪም ብዙም ሳልርቅ ከአፍንጫቸው ስሬ ነኝ አለ። ቤተ መንግስት የመሰለ ቤት ውስጥ ተቀመጠ። የዲፕሎማሲ ማዕከሏ ኬንያ፣ የተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ኃይሎችን የሚያገኝባት ኬንያ፣ አውሮፓ ህብረት ወዘተን የሚይዝበት ኬንያ ሌላ ለስልጣን መስፈንጠሪያ ሆነች። አንድ ቀን ድንገት አገዛዙ ቢወድቅ በአቋም ሳይርቅ፣ በቦታም ሳይርቅ፣ እርቅ ሰላም ወዘተ የሚል፣ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ልተነጠለ፣ የጎረቤት አገሪት ድጋፍ ያለው አልጋወራሽ ለመሆን ነበር። ግን እባብ ለእባብ ነው። የስልጣን ጨዋታው አብይ ጋር ነው። ኬንያም ተከትሎ አሳደደው።
አሁን ያለበት የድሮዎቹ የተለየ ይመስላል። ታጣቂ፣ ጦርነት አልደግፍም ከሚለው አቋም ተለይቷል። ከታጣቂውም፣ ጦርነት ከሚፈልገውም ጋር አለ። ስለ ሰላምም ያወራል። አሁን እንደ ሁለተኛ መንግስት አይደለም። አሁን እስረኛ ሆኖ እንደተደራደሩት አይደለም። አሁን እሱም በሂደቱ ንቁ ተሳታፊ ነው። ለውጥ ያመጣሉ የሚባሉት ጋር ሁሉ አለ። ጃዋር አገዛዙን አውቀዋለሁ የሚለው ብቻ ለቀጣይ ተመራጭ አያደርገውም። በርካታ የእስካሁኑን ካርዶች ይጠቀማል። አብይ እንደመጣበት አይነት "የሰፊ ህዝብ ወኪል" ጉዳይ ይጎትታል። የአገዛዙን ካድሬና ልሂቅ አሰባስባለሁ ይላል። ስልጣን ላይ የነበረ ኃይል በአገር ላይ ችግር እንዳይፈጥር "የእናንተው ልጅ" ነው የሚል መታወቂያን ያወጣል። በእምነቱም፣ በብሔሩም አለኝ በሚለው ልምድም ከጀርባዬ አሉ በሚላቸው ያኮረፉ ሰዎችም (እነ ለማን ጨምሮ) ሌላ እድል ሙከራ ላይ ነው።
ጃዋር ባለ ብዙ መልክ ነው። የፖለቲካ ሳይንሱን ያውቀዋል። የእነ ማኪያቬሌይ "እድልን ስትመጣ ተጠቀምባት" መርህን ከኦነግም ከሌላው ከጎለመሰበት ፖለቲካ ጋር አዳቅሎ ሳይፈራ ሳያፍር፣ የፈፀመው እየታወቀ "አልፀፀትም" እያለ ይሞክራል። የፖለቲካ መልኩ ብዙ ነው። አላማው ግን ስልጣን ነች። ከአብይ አህመድ ጋር የሚለያዩት በጥቂት ጉዳይ ነው። ጃዋር ጊዜ እየቀያየረ ያሰበውን አስረግጦ ይናገራል። አብይ ያሰበው ያመልጠዋል እንጅ እንደ ጃዋር በነፃነት አይናገራትም። አካሄዳቸውን ግን የትም ፍጭው ነው። ስልጣንን ይከተሏታል። ለስልጣናቸው ማንም ጋር ቢሆን ያብራሉ። ለስልጣናቸው ዛሬ ያወረዱትን ነገ ከፍ፣ ዛሬ የገጠሙትን ቀጣይ ሲጨብጡት ፊታቸው ላይ አያስነቁም። ባለ ብዙ የፖለቲካ መልክ፣ ግን አንድ አላማ። ስልጣን። ሌላው የስልጣን መናጇቸው ነው። አሯሯጭ ነው። ሄደው ሄደው የሚመዟትን ይመዛሉ። ካርዳቸው ብዙ ነው። ግባቸው ግን አንድ ናት። የመጨረሻው ደቂቃ ላይ እናልፋለን ብለው ያስባሉ። በለውጡ ወቅት አብይ እንዳደረገው፣ በተለያዩ ጊዜያት ጃዋር እንዳደረገው አሁንም እንደሚሞክረው!
ጃዋር እንደ ቴፕ ካሴት ነው። ተገልብጦ ይጫወታል። ያለማቋረጥ ፖለቲካውን በተለያየ "ቢት" ይዘፍነዋል። በተለያየ ዜማ ይጫወተዋል። አላማው ግን ተመሳሳይ ነው። አብይ በአንድ ወቅት የኦነግ አባል ነበርኩ እንዳለው ጃዋርም የማንኛውም ቡድን አባል ነበርኩ ብሎ ሊመጣ ይችላል። ከጠቀመው የአልሻባብም ቢሆን!ሁለቱም የፖለቲካ ወንድማማቾች፣ አምሳዮች ናቸው። ይጣሉ እንጅ የፖለቲካ መልካቸው የመንትዮች ያህል ተመሳሳይ ነው! GETACHEW SHIFERAW
-
MINILIK SALSAWI
- Senior Member
- Posts: 12640
- Joined: 24 Aug 2012, 12:02
- Contact: