Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
MINILIK SALSAWI
Senior Member
Posts: 12348
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

የምክክር ተብዬው ጉድ! ..... የቡድን አላማቸውን ለማስፈፀም ጥድፊያ ላይ ናቸው!

Post by MINILIK SALSAWI » 19 Jul 2026, 01:23

የምክክር ተብዬው ጉድ!
ብልፅግና የሚያወራለት ምክክር ከምርጫ የበሳ የጨረባ ሆኗል። ተሳታፊ ተብለው የሄዱት ራሳቸው ምክክር ተደረገበት የሚባለውን ምን እንደሆነ አያውቁትም!
1) ተሳታፊዎችን በቡድን ከፍለዋቸዋል። በቡድን የተመደቡት ተሳታፊዎች አንድ አጀንዳ ይሰጣቸዋል። የሚሰጣቸው አጀንዳ ደግሞ ቢከራከሩ ለውጥ የማያመጡበት፣ አገዛዙ ላይ ምንም አይነት ጫና የማይፈጥር ከሆነ ብቻ ነው። ከተመደቡበት ውጭ ባለው አጀንዳ አያገባቸውም ተብለዋል። ለአብነት ያህል ከአማራ ተወካይ የተባሉት ብዙዎቹ ከጉልህ የአማራ ጥያቄዎች ይልቅ አጨቃጫቂ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንዲመደቡ ተደርገዋል። ለምሳሌ ያህል የኃይማኖት አባቶች ሊመክሩበት የሚገባው ኃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ የእምነቱ እውቀት የሌላቸውን አካላት መድቦ ሌሎች አጀንዳዎች ላይ እንዳይደርሱ አድርጓል። የአዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች ዋና ጉዳዮች ላይ ኦህዴድ ብልፅግና ጥቅምና አካሄድ ይደግፋሉ ያላቸውን ነው የመደበበት።
2) በየቡድኑ የተመደቡትም መካከል ኦህዴድ ብልፅግና እያገኘ "አቅጣጫ" የሚሰጣቸው እያንዳንዱ ተሳታፊ የሚያነሳውን በማጥናት የሚያስተካክሉ ሰዎች የተመደቡበት ነው።
3) በርካታ ጉዳዮች ምክክር የተባለው ከመጀመሩ በፊት ብልፅግና አቋም የያዘባቸው ናቸው። በዚህ "አቅጣጫ" መሰረት ነው ያስቀመጣቸው ሰዎች ምክክር ተብየውን የሚመሩት።
እንደ አጠቃላይ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው ወዘተ ብለው የሚያደርቁት መድረክ ተሳታፊ የተባሉት እንኳን አጀንዳ ተከልላ ተሰጥታቸው ነው ጉንጭ አልፋ ክርክር የሚያደርጉት። ዋና ዋና የተባሉ ጥያቄዎች ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ ሌሎች እንዳይሳተፉ ተደርገዋል።
ለይስሙላህ አዳራሽ ውስጥ አስገብተው መሰረታዊ ያልሆኑ፣ ሌሎች ባለድርሻዎች በደንብ ሊወያዩበት የሚችሉት አጀንዳ ላይ ጠምዶ የራሱ ብሎ የሚያስባቸው አጀንዳ ላይ ደጋፊዎቹን አሰልፏል። ይህ ምርጫ ላይ ከሚያደርጉት በከፋ የጨረባ አካሄድ ነው። ቢያንስ በምርጫ ወቅት እንኳን አጀንዳዎቹ ላይ በሚዲያ ክርክር ይደረጋል። ምክክር በተባለው መርጠው አጀንዳ ይሰጣሉ። መርጠው ተወያይ ይመድባሉ። እየሆነ ያለው ይህ ነው! የጨረባ ነው!
በአጭር ምሳሌ!
ለ50 ተማሪዎች መቶ ጥያቄ ያለው ፈተና ታወጣለህ!
እያንዳንዱ ተማሪ ሁለት ሁለት ጥያቄ ብቻ ይመልሳል።
በተናጠል ያረምክላቸውን 50 ተማሪ የመለሰው እያንዳንዱን ጥያቄ መቶ ታደርገዋለህ። እያንዳንዱ 98 ጥያቄ ሳይሰራ ተፈቶኖ አለፈ ትለዋለህ። ይህ ፖለቲካ ሲሆን ደግሞ ምክክር የተባለው መድረክ ማለት ነው!

የቡድን አላማቸውን ለማስፈፀም ጥድፊያ ላይ ናቸው!
1) የኦህዴድ ብልፅግና ምክክር ኮምሽኑን የሚያይበት የሚጠቀምበትም ሌሎች ምክክሩ ይጠቅማል ከሚሉት፣ ምክክሩን ከሚያዩበት በተቃራኒ ነው። የፈለጉት እስካሁን ጀምረዋቸው ላልጨረሷቸው ፕሮጀክቶች ህጋዊ ሽፋንነት መስጠት ነው። የአገሬው አርሶ አደር "አንድ ሰኔ የነቀለውን ሰባት ሰኔ አይተክለውም" እንደሚለው ኦህዴድ ብልፅግናም በዚህ ወቅት በተቀናቃኞቹ ላይ በምክክር ስም የሚያደርገው ብልጫ ለአመታት የማይካካስ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ጥድፊያው። በአንድ ወሳኝ የፖለቲካ ሰኔ ተቀናቃኞችን ከፖለቲካ ትርክት፣ ስልጣንና መሰረታዊ ጥያቄዎች አርቆ የክፍለ ዘመን የፖለቲካ ሰኔ እንዳይክሳቸው ማድረግ ነው። እስካሁን ያሰባቸውን ሁሉ በኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ስም ዶሴ የሚዘጋበት ነው።
2) ይቀናቀኑናል የሚሏቸውን የፖለቲካ ሃይሎችና ማህበረሰቦች በጦርነት ጠምደዋል። በርካቶችን አስረው፣ ቀሪውን በተለያየ መንገድ ከጨዋታ ውጭ አድርገዋል። ዳያስፖራው ኩርፊያ ላይ ነው። በዚህ ወቅት ተረጋግቶ ምክክር ወዘተ ሊያደርግ የሚችለው የተደራጀው፣ ስልጣን አስጠባቂው ኃይል ነው። ሌላው ትኩረቱ ጦርነት ላይ ነው፣ በአጀንዳ አለመግባባት ይተራመሳል። ሌላው ኩርፊያ ላይ ነው። ይህን የሌሎችን ትርምስና ተረጋግቶ አጀንዳ አለማስያዝ፣ ከመድረክ ማራቅ ኦህዴድ ይፈልገዋል። አሸንፋለሁ የሚለው በዚህ መንገድ ነው። ኦህዴድ በክፈለ ዘመን የማይገኝ እድልን በጥቂቶች ታጅቦ የሚሮጥበት መድረክ ለማሳካት ሌላው በትርምስ ውስጥ መሆኑን ይፈልገዋል። ኦህዴድ ብልፅግና "በጊዜ የለም" መርህ እየሰራ ያለው ይህን ሌሎች በትርምስ ውስጥ፣ እሱ በአንፃራዊነት አጀንዳ ለመምራት ያለውን እድል አሟጦ ለመጠቀም ነው።
3) ሌሎች በትርምስ ውስጥ ባሉበት በዚህ ወቅት ኦህዴድ ብልፅግና ሌሎቹን ከአጀንዳ አርቆ ለዘመናት ስልጣንና ትርክት የሚቆጣጠርበትን አጀንዳ "አርቀን እንስቀለው" ብሎ እየሰራ ነው።
መርሁ “ተቀናቃኞቻችንን በጦርነት ጠምደንና እረፍት አልባ አድርገን አጀንዳቸውን አርቀን እንቅበረው፣ የእኛን አጀንዳ አርቀን እንስቀለው” በሚል መርህ እየተመሩ የገቡበት እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ “አሁን በደንብ ከነቀልናቸው መልሰው ለማንሰራራት ብዙ ጊዜ ይጠይቃቸዋል፤ ላያንሰራሩም ይችላሉ፤ እስከዚያ እኛ ተጨማሪ ስራዎችን እንሠራለን” ብለው በሚያምኑት መሰረት ነው እየሰሩ ያሉት። "አርቀን የቀበርነው የሌሎች አጀንዳ እስኪወጣ፣ እኛ አርቀን የሰቀልነውን እስኪያወርዱ ዘመናት አይበቃቸውም" ብለው ነው እየሰሩ ያሉት።
4) ይህ የምክክር ጉዳይ ለብልፅግና የአገር ችግር መፍቻ አይደለም። የአገር ጉዳይ በዚህ ወቅት ጉዳያቸው አይደለም። ቅድሚያ መቀመጫዬን እንዳለችው እንስሳት ቅድሚያና ቅድሚያ ስልጣንና የቡድን ጥቅም ከዛ እነሱ የሚበይኑት፣ እንደፈለጉ የሚያደርጉት፣ በእነሱ የጥቅምና ትርክት ማዕቀፍ የሚሽከረከር የኢትዮጵያ ጉዳይ ሊሰሩ ይችላሉ። ይህ አጣዳፊ ጉዳያቸው አይደለም።
5) ይህ ምክክር የሚሉት እስካሁን ያላሳካቸውን አላማዎቹን ማሳኪያ የትግል ግንባር ነው። “የትኛውንም መንገድ ተጠቅመን የምንፈልገውን ካሳካን፣ የተከልነውን ስርዓት፣ ያቆምነው መዋቅርና ያወጣነውን ህግ ለመሻር ጊዜ ይወስዳል፤ የሆነ ጊዜ ቢሻር እንኳን ሙሉ በሙሉ አይሆንም” የሚል አቋም ይዘው እንደሚሰሩ ይታወቃል፡፡ አገዛዙ ይህን አላማውን ለማስፈፀም ለአባላቱ በተደጋጋሚ የሚነግራቸው “መፍጠርና መፍጠን” የሚል መፈክር ነው።
በኮሚሽኑ ውስጥ ለሀገራቸው በጎ አስተዋፅኦ ለማድረግ ዓላማ የነበራቸው አካላት የሉም ማለት አይደለም፡፡ አሉ፡፡ ሆኖም ከኦህዴድ ብልፅግና ሸፍጥና አካሄድ አንፃር ተቋሙ እንደ ተቋም እና ብዙሃኑ የኮሚሽኑ አባላት የኦህዴድ ብልፅግና ጉዳይ አስፈፃሚዎች መሆናቸው የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡
የምክክር ኮሚሽን የሚቋቋመው ያለፉ የታሪክ ጠባሳዎች እንዲሽሩ መንገድ ለመፈለግ ነው፡፡ ያደረጉ አከራካሪ የታሪክና የትርክት ጉዳዮች በነጻነት እየተነሱና ውይይት እየተደረገባቸው የጋራ መፍትሄ እንዲበጅላቸው ለማድረግ ነው፡፡ በአጠቃላይ የጋራ አማካይ (mean) የሚባለውን በመፈለግ ሁሉም የእኔ የሚላቸውን ህጎችና መዋቅሮች ለማደራጀት ነው፡፡ የኦህዴድ ብልፅግና ድራማ ግን በጥያቄ ላይ ጥያቄ የሚጨምር፣ በችግር ላይ ችግርን የሚደራርብ፣ ተጨማሪ የጦርነትና ትርምስ ምክንያቶችን የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ኦህዴድ ብልፅግና እየሰራ የሚገኘው እስካሁን የጀመራቸውን የስልጣን፣ የሀብትና ትርክት ቅርምት፣ ተቃውሞ ያስነሱበትን አካሄዶች፣ ተቃውሞ ያስነሱብኛል ያላቸውን ጉዳዮች ብዙሃንን አሳትፈናል በሚል ማህተም ማስመታትና ህጋዊ ሂደት አስመስሎ ለማቅረብ ነው። ይህ ሁሉ ጥድፊያ ይህን የቡድን አላማ ለማስፈፀም ነው።

TO READ MORE ARTICLS ON TIS ISSUE : https://www.facebook.com/Getachew.Shiferaw.Offical



MINILIK SALSAWI
Senior Member
Posts: 12348
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

የምክክር ኮምሽኑ ጉዳይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስም የተጭበረበረ ምደባ

Post by MINILIK SALSAWI » 19 Jul 2026, 02:02

ከአርትፊሻል ኢንተለጀንስ እስከ አርቲፊሻል ተሳታፊዎች!
የምክክር ኮምሽኑ ጉዳይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስም የተጭበረበረ ምደባ እያነጋገረ ነበር። አሁን ደግሞ አርቲፊሻል ተሳታፊ ተጨምሮበታል።
የምክክሩ ጉድ መቼም ብዙ ነው! ከተለያዩ ክልሎች የመጡት ተሳታፊዎች በመጀመሪያ የምትወያዩት በምትፈልጉት አጀንዳ ላይ ሳይሆን እኛ በመደብናችሁ ነው ተባሉ። በሁሉም አጀንዳዎች ላይ መወያየትና ጉዳያችን ማስረዳት እንፈልጋለን እሱም ቢቀር ቅድሚያ በምንሰጠው አጀንዳ ላይ መድቡን በሚል ቅሬታ ቢያቀርቡም ያገኙት መልስ የተመደባችሁት በአርትፊሻል ኢንተለጀምስ ነው የሚል ሆነ።
ይችን አርትፊሻል ኢንተሌጀንስ በተለያዩ መድረኮች ላይ በማደናገሪያነት ስትነሳ ሰምተናል። ለመሆኑ አርትፊሻል ኢንተሌጀንስ ቢሆንስ የምንፈልገውን/እንድንሠራለት ያዘዝነውን ይሠራል እንጂ ከልብ አውቃ ነው ያለው ማነው? እንድትታመን ሳይንስና ቴክኖሎጂን መጥቀስ የተለመደ ድራማ ነው!
ለምሳሌ
ከዚህ አካባቢ የመጡትን ተሳታፊዎች በየክልላቸው ካነሱት አጀንዳ ጋር እንዳይገናኙ አድርገህ መድብ ሲባል ይህንኑ ያደርጋል እንጂ በፍትሃዊነት እመድባለሁ ብሎ የሚሟገት ሰው እኮ አይደለም። እሱም መድቦ ከሆነ እንዴት መመደብ እንዳለበት መሥፈርቱ ምንድን ነው ተብሎ ይጠየቃል እንጂ አርትፊሻል ኢንተለጀንስ ስለመደበው ትክክል አስመስሎ ማቅረብ ማጭበርበሪያ ነው!
ይህን ብለን ሳናበቃ ከራሳቸው ከኮሚሽነሮቹ የሰማነው ምክክሩ አርትፊሻል ብቻ ሳይሆን ተሳታፊዎችን አርቲፊሻል ለማድረግ እየጣረ እንደሆነ ነው።
በዛሬው ውሎ 500 ተሳታፊዎች ይይዛሉ ተብለው የተነገሩት አዳራሾች ከተጠበቀው ተሰብሳቢ በላይ የተገኘባቸው መሆኑ ሲታይ ማን ተጨምሮ ነው የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ለዚህ ጥያቄ የምክክር ኮሚሽነሮች የሰጡት ምላሽ ታዳሚውን በእጅጉ አስደምሟል። በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የተጋበዘው ተሳታፊ ብዛት 4,000 ቢሆንም ከኦሮሚያ ክልል ተጨማሪ 3,000 ሰዎች ሳንጋብዛቸው ተገኝተው ልንመልሳቸው ባለመቻላችን ተሳታፊው ወደ 7,000 አድጓል መልስ ተሰጥቷል ነው።
ሆኖም ሁሉም ተሳታፊ ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚገባው የተሳታፊ መታወቂያውን እያሳዬ በመሆኑ ተጨመሩ የተባሉ ሰዎች ይህ ችግር ሲገጥማቸው አልተስተዋለምና መታወቂያቸው ቀድሞ የተዘጋጀ መሆኑን አረጋግጧል።
በዚህም ምክንያት በተነሳ ተቃውሞ ምክክሩ እስካሁን እንዳልጀመረ ታውቋል። ስለምክክሩ እየተሰማ ያለው ችግር በርካታ ከመሆኑ የተነሳ የቱን አንስቶ የቱን መተው እንደሚቻል ግራ እያጋባ ነው! ተሳታፊ ዙሪያ ከተቋማት ውክልና፣ ከክልሎች ውክልና እንዲሁም በአጀንዳ ምደባ ላይ እየተደረገ ያለው ዓይን ያወጣ ሸፍጥ ግን ይህ አርቲፊሻል ምክክር የአገርን ችግር ከመጨመርና ይበልጥ ከማወሳሰብ ውጪ ችግር ሊፈታ እንደማይችል የሚያረጋግጥ ነው።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለስንቱ ቅጥፈትና ማታለያ ቅመም እየሆነች ትቀጥላለች? ዝናብ ከማዝነብ እስከ ምክክር ተሳታፊ ምደባ፣ ስንቱን ጉድ አየነው!
ድራማ ብለን እንደቀልድ ብናልፈው መልካም ነበር። ነገር ግን ውሎ አድሮ አገርን ውድ ዋጋ የሚያስከፍል አደገኛ ድራማ በመሆኑ በቀላሉ ሊታለፍ አይገባም። ቅጥፈቱ በሚገባ ተሰንዶ መቀመጥ ይገባዋል!


በጓዳ ሌላ በይፋ ሌላ
ኦህዴድ ብልፅግና በምክክር ኮምሽኑ ጉዳይ በርካታ አቋሞችን ይዟል። ብዙዎቹ ደግሞ በጓዳ የተያዘባቸው አቋምና በይፋ ለህዝብ የሚነገረው እጅግ የተለያየ ነው። ለአብነት ያህል በክልሎችና በህገ መንግስቱ ጉዳይ ለህዝብ የሚነግሩትና በውስጥ አቋም የያዘበት የተለያየ ነው።
"የሚጠናከር እንጂ የሚፈርስ ክልል የለም፤ የሚጨመር እንጂ የሚቀነስ አንቀፅም የለም!" ብለው አቋም ይዘዋል።
ይህ ከላይ የቀረበው ሀሳብ በጊዜ የለንም መንፈስ እየሮጡ ያሉት የኦህዴድ ብልፅግና ሰዎች አቋም ነው፡፡ ይህንን አቋማቸውን ለሌሎች የብልፅግና ቅርንጫፍ ፅ/ቤት አባላት ጭምር ግልፅ አድርገውላቸዋል፡፡ እንደተለመደው ለሚዲያ ፍጆታ የቆጥ-የባጡን ሲናገሩ ቢደመጡም፣ ምክክር የሚባለው የኦህዴድ ብልፅግናን ዓላማ ለማሳካት የተዘጋጀ እንጅ አጋንነው የሚናገሩትን ሁሉ የሚያካትት አይደለም። አንዳንዱን ህዝብ መክሮበት ነገር ግን ያልወሰነበት አስመስለውም አዳፍነውት ሊያልፉ ይችላሉ።
አንዳንድ ቅን ወገኖች የክልል አደረጃጀት የሚሻሻል ይመስላቸዋል፡፡ አንዳንዶችማ እርግጠኛ ሆነው ሲናገሩና ሲጽፉም ይስተዋላል፡፡ ይህ የማይሆን ከንቱ ምኞት መሆኑን የኦህዴድ ብልፅግና ሰዎች ግልጽ አድርገዋል፡፡ “የሚጠናከር እንጂ የሚፈርስ ክልል የለንም” ብለው እቅጩን ተናግረዋል፡፡ እርማችሁን አውጡ ማለታቸው ነው፡፡ አሊያም ልዩ ኃይሉ ላይ እንዳደረጉት አማራ ክልል እንደ ቤተ ሙከራ አድርገው ሊሞክሩት ይችላሉ። ኦሮሚያ ላይ እንደማያደርጉት ከተናገሩ ቆይተዋል። ትናንትም ሽመልስ አብዲሳ ደግሞ ተናግሮታል።
አንዳንዶች እንደ አንቀጽ 39 ያሉ የህገ መንግስቱ አንቀጾች የሚቀየሩ የሚመስላቸውም አሉ፡፡ ኦህዴድ ብልጽግናዎች ግን የሚጨመር እንጂ የሚቀነስ አንቀጽ የለም ብለው እቅጩን ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ነው ምክክር የሚባለው ሂደት የሀገርን ተንከባላይ ችግሮች ቀርፎ ወደፊት የሚያሻግር ሳይሆን፣ በፈተና ላይ ፈተናን የሚደራርብ፤ በችግር ላይ ሌሎች ችግሮችን የሚያከማች ከመሆን አያልፍም የምንለው። ኦህዴድ ብልፅግና የምክክርና ውይይትን መልካም ስም ተጠቅሞ ይህን ሂደት የስልጣን ማጠናከሪያ ከማድረግ ያለፈ አላማ እንዲኖረው አይፈልግም።የተሳታፊዎችን ካርድ ሕገወጦች ወስደውታል ተብሏል! መቸም ህገወጥ የተባሉት አካላት ካርዱን ገንዘብ ሊያወጡበት አይወስዱትም። የተደራጀ ኃይል ነው ሌባው። አገዛዙ።
ዋዜማ ሬዲዮ እንደዘገበው ከተለያየ አካባቢዎች ለምክክር ኮምሽኑ ተሳትፎ የመጡ ተሰብሳቢዎች "መግቢያ ካርድ አልቋል" ተብለዋል። ለተሳታፊዎች በሚበቃ መልኩ ካርድ ተዘጋጅቶ እንደነበር የተዘገበ ሲሆን ካርድ የለም የተባሉ ለተሳትፎ የመጡት አካላት ለኮምሽኑ ባቀረቡት ጥያቄ የሚደንቅ መልስ ተሰጥቷቸዋል። ኮምሽኑ የካርዱ እጥረት ሊከሰት የቻለው ካርዱን ህገወጦች ወስደውት ሊሆን እንደሚችል ገልፆ ማጣራት እንደሚያደርግም አሳውቋል።
ከዚህ ባሻገር በማይፈልጉት አጀንዳ ላይ ብቻ እንዲወያዩ በመገደዳቸው ራሳቸውን ከምክክሩ ያገለሉ እንዳሉም ያነጋገራቸውን እማኞች ጠቅሶ ዋዜማ ዘግቧል።
ከአሁኑ አጀንዳም ካርድም እየተሰረቀ ነው ለማለት ነው!Getachew Shiferaw

MINILIK SALSAWI
Senior Member
Posts: 12348
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

የምክክር ኮምሽን ብለው ብዙ የሚያወሩለት በየቀኑ ቀልዱ ጨምሯል።

Post by MINILIK SALSAWI » 19 Jul 2026, 02:05

ምኑን ምክክር ሆነና?
የምክክር ኮምሽን ብለው ብዙ የሚያወሩለት በየቀኑ ቀልዱ ጨምሯል። ተሳታፊ ትሆናላችሁ ተብለው ከየክልሉ የመጡት "መግቢያ አልቋል" ተብለው ሲመለሱ ከኦሮሚያ ደግሞ ከመጀመሪያው ለተሳትፎ ያልታጩ 3000 ሰዎች ሰተት ብለው ወደ አዳራሽ ገብተው ውለዋል። በዚህ ምክንያት አዳራሹ ሁሉ አልበቃ ብሏል።
ዋናው አላማ ምክክር ተደረገ ከተባለ በኋላ ጉዳዩ በድምፅ ብልጫ እንዲያልፍ ሊያደርጉ ነው። መጀመሪያ ነገር ሰው በማይፈልገው አጀንዳ እንዳይወያይ አደረጉ። ትኩረት በማይሰጠው ጉዳይ ላይ ስለሆነ እነሱ አደራጅተው ባስገቡት ሰዎች ምክንያት ሀሳብ ተሰጥቶበት ያልፋል። ያም አልበቃቸው ሲል ተሳታፊ ተብለው የመጡትን አትገቡም አሏቸው። ሌሎች አቋርጠው እየወጡ ነው። ይባስ ብለው ያለ ከልካይ ወደ አዳራሽ የሚገቡ 3000 ተጨማሪ ሰዎች አምጥተዋል። በተነገራቸው መሰረት እጃቸውን አውጥተው የሚፈልጉትን አጀንዳ በብልጫ ያሳልፋሉ።
አስባችሁታል? እግርኳስ ቢሆን ተጨማሪ አንድ በረኛ፣ ተጨማሪ ሁለት አጥቂዎች፣ ተጨማሪ ሶስት ተከላካይ ወዘተ ሊያስገቡ ማለት ነውኮ። ከዛ ደግሞ የተቃራኒን ሁለት ሶስት ተጫዋች የሆነ መስፈርት ጠቅሰው አትገቡም ብሎ እንደመከልከል ማለት ነው።
እና ይህ ምኑን ምክክር ሆነው?
....................................................
በአዲስ አበባ ላይ የወሰኑት
ኦህዴድ ብልፅግና በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ በምክክር ኮምሽኑ ሊያፀድቅ የፈለገው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ካስተላለፈ ቆይቷል። ኦህዴድ ብልፅግና በአዲስ አበባ ጉዳይ "ቢያንስ ቢያንስ" ብሎ የመጨረሻ የያዘው አማራጭ "የጋራ ጥቅም" የሚል ነው። የጋራ ጥቅም ሲባል በቃሉ ማማር መልካም ነገር እንዳትጠብቁ።
እስካሁን ኦህዴድ ብልፅግና በአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ "ቢያንስ ቢያንስ" ብሎ በመጨረሻ አማራጭነት ሲከተለው የቆየው "ለኦሮሚያ ልዩ ጥቅም" የሚል ነው። በምክክር ኮምሽኑ እንዲወሰን "ቢያንስ ቢያንስ" ተብሎ የመጨረሻ አማራጭ ተብሎ የተወሰነው "የጋራ ጥቅም" ነው! ይህ የጋራ ጥቅም ማለት ኦሮሚያና አዲስ አበባ በጋራ ይወስናሉ ማለት ነው። ከአዳነች አቤቤ በተጨማሪ ሽመልስ አብዲሳ በአዲስ አበባ ላይ የመወሰን ስልጣን ይሰጠዋል እንደማለት ነው። ለሌሎች ኢትዮጵያውያን "ከልዩ ጥቅም ወደ ጋራ ጥቅም አቋም ቀይረናል" ብለው አቆንጅተው፣ ቀባብተው የሚያቀርቡት ይህን አቋም ነው።
ኦህዴድ ብልፅግና በምክክር ኮምሽኑ በዋነኛነት ጥርሱን ነክሶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች የአዲስ አበባ የባለቤነት ጉዳይ አንዱ ነው። ለዛም ነው 4 ሺህ ተሳታፊ ይኖረዋል ለሚባለው ምክክር ተጨማሪ ህገወጥ 3 ሺህ ከኦሮሚያ አምጥተው ያጥለቀለቁት። 4 ሺህ ተሳታፊን "ጠጋ በል" ብለው ከተቀመጡት 3 ሺህ ህገወጥ ተሳታፊዎች ባሻገር ከ4 ሺህ መካከል ከ40 በመቶ በላይ የብልፅግና መዋቆርና አባል ነው። ቀሪው "መግቢያ ካርድ የለም ተብሎ፣ ሌላው በአንድ አጀንዳ ብቻ አልወያይም ብሎ ቀርቷል። በዚህ ሁሉ መሃል ከእነ አካቴው አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነች ብሎ በእጅ ብልጫም ሊያስወስን ይችላል። በዚህ ማጭበርበር ውስጥ አይደለም ዋና ከተማዋን የሌሎች ክልል ከተሞችንም "የኦሮሚያ ናቸው" ብለው እጅ ማስወጣት ይችላሉ። Getachew Shiferaw

MINILIK SALSAWI
Senior Member
Posts: 12348
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

የምክክር ተብዬው ጉድ! ገዥዎቹ አማራ እንዲጠመድባቸው የሚፈልጓቸው አጀንዳዎች እና የአማራ ቀዳሚ አጀንዳዎች!

Post by MINILIK SALSAWI » 19 Jul 2026, 02:10

ገዥዎቹ አማራ እንዲጠመድባቸው የሚፈልጓቸው አጀንዳዎች እና የአማራ ቀዳሚ አጀንዳዎች!
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በሚገባ የሚታወቁ ናቸው፡፡ የሕዝብን ፍላጎት ከልብ የሚያደምጡ እና ለእውነተኛ እኩልነትና ፍትሕ የተዘጋጁ ሃይሎች ቢኖሩ፣ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ተቀባይነት በማግኘታቸው የሚጠቀሙ እንጂ የሚጎዱ ወገኖች የሉም፡፡ ይሁን እንጂ ትናንትም ሆነ ዛሬ የአማራ ሕዝብ በጥላቻና በጥርጣሬ የሚያዩ ሃይሎች የሕዝባችንን ጥያቄዎች ለመደፍጠጥ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ተረጋግጧል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ወደ ጎን ገሸሽ እንዲሉ በመደረጋቸውና በመደፍጠጣቸው ምክንያት የምትጎዳ እንጂ የምትጠቀም ኢትዮጵያ አትኖርም፡፡ የአማራ ሕዝብ ጉዳት የሀገራችንም የሌሎች እህትና ወንድም ብሔሮችም ነውና፡፡ ኢትዮጵያ አንደኛው አካሏ እየደማ ልትለመልም አትችልምና!
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ፣ ግልጽ የሆኑት የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ወደ ጎን እየተገፉ፣ ሌሎች ጉዳዮች “የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው” ተብለው እንዲቀርቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህ በትህነግና ኦነግ ፊታውራሪነት በተመራው የሽግግር ጉባኤ ተብዬም በግልጽ የታየ ነበር፡፡ ዛሬም ያው ነው፡፡
ለምሳሌ ገዥዎቹ አማራ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ጊዜውን እንዲያጠፋ ይፈልጋሉ!
1) ገዥዎቹ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሰንደቅ ዓላማ ይቀየርልኝ ጥያቄ ላይ ጊዜውን እንዲያጠፋ ይፈልጋሉ። ይህ ግን የእነሱ አማራን ከሌላው ጋር ማነታረኪያ እንጂ የአማራ ሕዝብ አፋጣኝ ጥያቄ አይደለም፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ጥያቄ የአማራ ሕዝብ ብቻ ሊሆን የሚችልበት ምንም ዓይነት አመክንዮም የለም፡፡ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ማዳፈን የሚፈልጉ ሃይሎች ሰንደቅ ዓላማን የአማራ ሕዝብ ጥያቄ አድርገው የሚያቀርቡት አማራውን ከዋና ጥያቄዎቹ ለማራቅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
2) እነዚህ አካላት የአማራ ሕዝብ ጥያቄ “አንቀጽ 39 ከሕገ መንግሥቱ ይፋቅልኝ” የሚል ጥያቄ ላይ ተቸክሎ ሌሎች ጋር እንዲነታረክ ይፈልጋሉ። የአማራ ህዝብ መሰረታዊ የህገ መንግስት ጥያቄ ያለው ቢሆንም ውጤት በሚያመጡለት፣ ከሌሎች ጋርም ተግባብቶ የሚሄድበት እንጅ እነሱ ለሚያስቡት ወጥመድ ለመግባት ብቻውን የሚያነሳው ጉዳይ አይደለም።
አንቀጽ 39 ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚመለከት እንጂ አማራውን ብቻውን የሚያሳስበው ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለሆነም የአማራ ሕዝብ “ከዋነኛ ጥያቄዎቼ መካከል አንዱ አንቀጽ 39 ይፋቅ/ይሰረዝ የሚል ነው” ብሎ አያውቅም፡፡ ይህን የሚሉ ሃይሎች አማራን ከመሠረታዊ ጥያቄዎቹ ለማራቅ የሚሠሩ ሃይሎች ናቸው፡፡
3) እነዚህ ፀረ አማራ ሃይሎች “ከአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች መካከል ፌደራሊዝም ቀርቶ አሐዳዊ ሥርዓት እውን ይሁን” የሚል ነው ሲሉም ይደመጣል፡፡ ይህን የሚጠቀሙት በአንድ በኩል አማራን በሀሰት የድሮ ስርዓት የሚናፍቅ ጭምር ለማስመሰል ነው። አማራ በሀሰት ጨፍላቂ ተደርጎም በየአካባቢው በሚወጋበት አወቃቀር እንኳን ከሌላው በተሻለ በክልሉ ጥያቄ አለን የሚሉትን ቋንቋቸውን አክብሮ አስተዳደራቸውን አክብሮ የሚኖር ህዝብ ነው። ማንም ክልል የሌለው አማራ ላይ ግን እየተከበረ ይገኛል።
4) አማራን ከዋና ጥያቄዎቹ ለመግፋት የሚሰሩ ኃይሎች አማራ ለአንድ ኃይማኖት የቆመ አስመስለውም በሀሰት ያቀርቡታል።
እነዚህ ፀረ አማራ ሃይሎች አማራነትና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶነትን አንድ አድርገው በማቅረብ የአማራን ሕዝብ በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችና ብሄረሰቦች ዘንድ ለማስጠላት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሃቁ ግን ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ አማራ ባለ ብዙ ሃይማኖት ሕዝብ ነው፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ እስልምና፣ ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ፣ ይሁዳዊነት ወዘተ ሁሉ የአማራነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ የአማራ ልጆች ለብሔሮች እና ሃይማኖቶች እኩልነት ከማንም በላይ ታግለዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔሮችና ሃይማኖቶች ነጻነትና እኩልነት ከማንም በላይ የታገሉት የአማራ ልጆች መሆናቸውን ማንም ህሊና ያለው ሰው ሊመሰክረው የሚችለው ሃቅ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለብሔሮችና ሃይማኖቶች ነጻነትና እኩልነት ይቆማል፡፡ ገዥዎቹ ጥያቄህ ናቸው ብለው ጊዜውን እንዲያጠፋ የሚፈልጉለት እነዚህ ጥያቄዎች ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር ተመካኮሮ፣ ጊዜ ወስዶ የሚያስተካክላቸው ናቸው።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ግልጽ ናቸው፡-
1) ዘመናትን ያስቆጠረው የሕዝብ ቁጥር ቅነሳ ጥያቄ አለበት።
ከአማራ ሕዝብ ቁልፍ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የሕዝብ ቁጥርን የተመለከተው ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ለመጀመሪያው ጊዜ (ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ) በውል አልተቆጠረም፡፡ በአፄ ሃይለሥላሴ ዘመን አማራ ነኝ ማለት ከኢትዮጵያዊነት እንደማነስ የሚቆጠርበት ዘመን ነው፡፡ አማራነት ምንድን ነው? አማራ ማን ነው? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ግልጽነት ያልነበረበት ጊዜም ነበር፡፡ አማራነትን ከኦርቶዶክስ ክርስትና ጋር ብቻ የማያያዝ አዝማሚያም ነበር፡፡ በዚህ ያልተጠራ ሁኔታ ውስጥ የአማራ ሕዝብ በትክክል ሊቆጠር አይችልም፤ አልቻለምም፡፡ በዘመነ ደርግ የነበረው ደግሞ ከዚህም የከፋ ነው፡፡ አማራነት ከመሬት ከበርቴነት፣ ከአድኃሪነት፣ ከፊውዳልነት ጋር ተያይዞ ሲቀርብ የነበረበት፣ በርካቶች ሕይወታቸውና ንብረታቸውን ለማትረፍ አድፍጠው የነበሩበት ዘመን ነበር፡፡ አማራነት በአርሲ፣ በወለጋ እና በሌሎችም አካባቢዎች ከመሬት የሚያፈናቅልና ለመከራ የሚዳርግ ማንነት ሆኖ ነበር፡፡ ይህን ነው በወሮ-በላው የወያኔ ቡድን ዘመነ መንግሥት ተጠናክሮ የቀጠለው፡፡ የዘመነ ወያኔው ቆጠራ እምብዛም ትንታኔ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ከወያኔ ዘመን አንስቶ ያለው ሁኔታ አማራው በሕዝብ ቁጥርም ሆነ በመልክዓምድር (demography and geography) እንዲያንስና እንዲኮሰምን የተደረገበት ዘመን ነው፡፡
ስለሆነም የአማራ ሕዝብ በቁጥር ቀዳሚ እንጂ ሁለተኛ አይደለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የሚካሄድ ቆጠራም የአማራን ሕዝብ ሊወክል አይችልም፡፡ በመሆኑም የውጭ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባሉበት እንደገና የአገሪቱ ሕዝብ መቆጠር ይኖርበታል፡፡ አንዱና ወሳኙ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ይህ ነው፡፡
2) የማንነትና ወሰን ጥያቄ!
ሌላው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ከማንነትና ወሰን ጋር የተያያዘው ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ በሕዝብ ብዛትም በመልክዓምድርም እንዲያንስና እንኮሰምን ተደርጓል፡፡ በርካታ የአማራ አካባቢዎች ያለ ሕዝቡ ፍላጎት ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲካለሉ ተደርጓል፡፡ ይህ ከመሠረቱ መቀየር ይገባዋል፡፡
3) የታሪክ ትርክት ጥያቄ!
ሌላው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ከታሪክና ትርክት ጋር የተያያዘው ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ነጻነት፣ ለሕዝቦቿ እኩልነትና ፍትሕ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ጨቋኝ እንዲታይ ያልተቋረጠ እኩይ ፕሮፓጋንዳ ሲካሄድበት ኖሯል፡፡ ይህም ያለማቋረጥ የሚፈናቀል፣ የሚሳደድ፣ የሚገደል ሕዝብ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም ይህ አደገኛ (ዛሬም ያልተቋረጠ) ትርክት ከመሠረቱ መነቀል ይገባዋል፡፡
4) የአዲስ አበባ ጥያቄ!
ሌላው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የተያያዘው ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ በታሪክ የአዲስ አበባ (በራራ) ባለቤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ አበባ የለማችው በመላው ኢትዮጵያዊያን ላብና ጥረት መሆኑ ደግሞ የሚካድ አይደለም፡፡ ከዚያም አልፎ አዲስ አበባ ለቀዳማዊ ሃይለሥላሴ መንግሥት ምስጋና ይግባውና የአፍሪካ ህብረት (የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) ዋና መቀመጫ ናት፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫም ናት፡፡ ስለሆነም የአፍሪካዊያን የዲፕሎማቲክ ከተማ መሆኗም እሙን ነው፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ ከአንድ ብሔር ጋር መጣበቅ አይገባትም፡፡ አዲስ አበባን ከአንድ ብሔረሰብ ጋር ማያያዝ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ መፍረድ ነው፡፡ ውሎ አድሮ የሚፈነዳና አገርን የሚያደርስ ቦምብ ነው፡፡
5) የቋንቋ ጥያቄ!
ሌላው የአማራ ህዝብ ጥያቄ ቋንቋን የተመለከተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለ ብሔር፣ ባለ ብዙ ሃይማኖት እና ብዙ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሃይሎች ባለቤት መሆኗን እንገነዘባለን፡፡ ስለሆነም ብዝሃነቷን ከግምት ውስጥ ያስገባ ጠንካራ አንድነት ያስፈልጋታል፡፡ ይህን ለማድረግ አንዱ መንገድ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተናጋሪ ያላቸውን ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ ማድረግ ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ 5 ቋንቋዎች የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋዎች መሆን እንዳለባቸው በራሱ ሰነዶች ላይ አስቀምጧል፡፡ ለምን 5 ብቻ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያስፈልገው ነው፡፡ 5ቱ በምን መስፈርት ተመርጠው ነው? ሌሎች ለምን ቀሩ? ይህ በቂ ውይይት፣ ክርክርና ምላሽ የሚያስፈልገው ነው፡፡ በእኛ እምነት ከ1 ሚሊዮን በላይ ተናጋሪ ያላቸው ቋንቋዎች የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋዎች መሆን አለባቸው፡፡
በሌላ በኩል፣ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የሚኖረው በክልሎች በመሆኑ እያንዳንዱ ክልልም ብዝሃ ቋንቋ ያለው መሆኑን መቀበልና ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎችን በሕገ መንግሥቱ እንዲያካትት መደረግ ይኖርበታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አማርኛ ቋንቋ የመላው ኢትዮጵያውያን የመግባቢያ ቋንቋ በመሆኑና ለጋራ አንድነታችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላለው የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን ቢደረግ አገራችን ትጠቀማለች፡፡ ይህ አማራ ለራሱ ጥቅም ብቻ የሚያነሳው ሳይሆን ለኢትዮጵያም ሲል የሚጠይቀው ነው።
6) የዲሞክራሲ ጥያቄ!
ሌላው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ዲሞክራሲን የሚመለከት ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያ እንደ አገር ልትቀጥል የምትችለው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ሲሆን ነው ብሎ ያምናል፡፡ ዲሞክራሲ በሌለበት ፌደራላዊ ሥርዓት አይታሰብም፡፡ እኩልነት አይኖርም፡፡ ፍትሕ አይታሰብም፡፡ ስለሆነም ለኢትዮጵያ ህልውናና ሁለንተናዊ ብልጽግና ዲሞክራሲ ቁልፍ እሴት ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ለሃቀኛ የሕዝቦች ነጻነት፣ እኩልነትና ፍትሕ ዋጋ ሲከፍል የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ ወደፊትም ለእነዚህ አገር-አድን እሴቶች ይታገላል!
7) የመወከል፣ የመደራጀት በተለይም በሌሎች ክልሎችና አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች መብቶችና ጥበቃ ከዘር ፍጅት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከዋና ጥያቄዎቹ መካከል ናቸው።
እነዚህ ሁሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ሲታሰቡ ያለ ህገመንግስት ሊታሰቡ አይችሉም። ነገር ግን አማራ በእሱ ላይ ጭምር የሀሰት ትርክት የሚተርከው ህገ መንግስት ላይ ያለው ጥያቄ ገዥዎቹ ከሌሎች ጋር ለማነታረክ የሚያነሱት ቁንፅል አንቀፆች አይደሉም። ሁሉን አቀፍ ትርጉም ያለው ነው። ይህንም የሚያሳካው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ነው።
ገዥዎቹ አማራ በሀሰት የሚፈረጅባቸውን የተወሰኑ ጉዳዮች ይዘው "እነዚህ ናቸው ጥያቄዎችህ" የሚሉት ከዋና ጥያቄዎቹ ከማራቅ ባሻገር ለሌሎች ብሔሮች "መጣባችሁ" ለማለት ጭምር ነው። ነገር ግን አማራው ለሌሎች እህት ወንድሞቹ ጥያቄዎቹን እያስረዳ፣ እየተግባባ ይሄዳል እንጅ አገዛዙ በሚፈልገው ወጥመድ ተይዞ ሌላ የከፋ ዘመን ለማሳለፍ አይፈልግም።
ገዥዎቹ አማራ እንዲጠመድባቸው የሚፈልጋቸውም ላይ አማራ ጥያቄ የለውም ማለት አይደለም። ነገር ግን በራሱ ጊዜ፣ በራሱ አቀራረብ፣ ዋናዎቹን ጥያቄዎች በማይሸፍን፣ ለወጥመድ በማይመች መልኩ የይደርም፣ ሲፈልግ በራሱ ደረጃ የሚያወጣላቸው፣ በራሱ ሲፈልግ የሚያስቀድማቸውም የሚያቆያቸውም ሊሆኑ ይችላሉ። Getachew Shiferaw

MINILIK SALSAWI
Senior Member
Posts: 12348
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

የምክክር ኮምሽኑን ሂደት ለምንድን ነው የምንተቸው?

Post by MINILIK SALSAWI » 19 Jul 2026, 14:45

የምክክር ኮምሽኑን ሂደት ለምንድን ነው የምንተቸው?

ምክክር አንድ ጉዳይ ወይም ጉዳዮች ያገባናል የሚሉ አካላት ተመካክለው መፍትሔ እናመጣበታለን የሚሉበት መድረክ ነው! ይህ የምክክር ፅንሰ ሀሳብ ነው። ይህኛው "ምክክር" ግን መሰረታዊ ሀሳቡን አያሟላም!

1) አጋዛዙ ጭምር በኢትዮጵያውያን መካከል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት ያለመ ምክክር እንደሆነ ይነግረናል። ነገር ግን የምክክር ኮምሽኑ ተሳታፊዎች ወደ አዳራሽ ከመግባታቸው በፊት ኦህዴድ ብልፅግና በጉዳዮቹ ላይ ቀድሞ ወስኗል። ስለሆነም የምክክር ኮምሽኑ ተሳታፊዎች ለይስሙላህ የተመረጡ ያደርጋቸዋል።

2) ምክክር የሆኑ አካላት ያገባናል በሚሉት ጉዳይ ተመካክለው የሚወስኑበት ሆኖ እያለ አሁን እየሆነ ያለው ተሳታፊዎች ጉዳያቸው ባልሆነው ነጥብ እንዲወያዩ የሚያደርግ ነው። ከዩኒቨርሲቲ የመጡ እምነት የለንም የሚሉ ሰዎች የኃይማኖት ጉዳይ ላይ ተመድበዋል። በሌሎች ጉዳይም በተመሳሳይ ተሳታፊዎች አያገባንም በሚሉት ጉዳይ ላይ ተመድበዋል። የማያገባቸው ላይ መክረው ለኢትዮጵያ ምን አይነት መፍትሄ እንደሚያመጣ እግዜር ይወቀው።

3) ተመካካሪ የተባሉት በማያገባቸው ጉዳይ ጉንጭ አልፋ ንግግር አደረጉ ወይም ዝምታ መረጡ ሌሎች የሚፈልጓቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ድምፅ ሳይኖራቸው በሌላ ጉዳይ ላይ ግዴታ ቢወያዩ የምክክርን ፅንሰ ሀሳብ ሊያሟላ አይችልም። የማይፈልጉት አጀንዳ ላይ የተሰለፉ አካላት የሚሰጡት አስተያየት ሚዲያዎች፣ አጥኝዎች፣ የዘመኑ ቲክቶከሮች መንገድ ላይ ያገኙትን ሰው የግምት ጥያቄ ጠይቀውት ከሚመልሰው የግምት መልስና ሙግት የለተየ ነገር ሊያበረክቱ አይችሉም።

4) በርካታ ጥያቄ ያላቸው አካላት በነፃነት ጥልቅ ውይይት አድርገው መወሰን የሚችሉበት ምክክር እና ሰዎች በሚያገባቸውም በማያገባቸውም ጉዳይ ልክ እንደ ሰርቬይ ተጠይቀው የሚያብራሩበት፣ የቡድን ውይይት የማያደርጉበት ፅንሰ ሀሳቡ የተለያየ ነው። ምክክርና የጥናት ግብአት አይነት ሰርቬይ ደግሞ ለእየ ቅል ናቸው!

5) በምክክሩ በፓርቲ ደረጃ ቀድሞ ከመወሰኑ በላይ ከግማሽ ያላነሰው ተሳታፊ የፓርቲ አባልና አመራር ነው። ቀሪው ደግሞ ለገዥዎች ቅርበት ያለው ነው። በዚህ ሁኔታ ህዝብ እየተቃወመው ያለው የኦሮሞ ብልፅግና ሀሳብ እንጅ የህዝብ ጥያቄ ቀድሟል ብሎ ለመገመት አይቻልም።

6) የኢትዮጵያ ችግር ጦር አማዝዟል። በርካታ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነትና ግጭት አለ። ምክክር ሲባል ይህን ይፈታል ተብሎ ነው ሰው የሚገምተው። እውነታው ግን በዥው ፓርቲ ቀጥታ ትዕዛዝ አጀንዳ የሚያስይዙት ሚዲያዎች ስለ ምክክሩ መልካም ነገር አንድ ሀተታ ዘግበው ቀጥለው የጦርነት ቀስቃሽ፣ ጦርነት አወዳሽ ዘገባዎችና ትረካዎችን ነው የሚለቁት። በአንድ በኩል የአዳራሽ ውይይት በሌላ በኩል የጦር ሜዳ ውሎና የቀጣይ ጦርነት አቅጣጫን ነው የሚያመላክቱት። ከዚህ አንፃር ስብሰባ የተጀመረለት ምክክር የትኛውን የኢትዮጵያ ችግር ሊፈታ እንዳሰበ ሁሉ ግራ ያጋባል።

7) የብልፅግና ቅርንጫዎችና አባላት ጭምር ያልተስማሙባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ይነገራል። እነዚህ ጉዳዮች በተወያዮች ብቻ ሳይሆኑ በአገዛዙም ስምንምነት ያልተደረሰባቸው፤ ባልተስማሙ ሰዎች የበላይነት ምክክሩ ጫና እየተደረገበት፣ አቅምና እድል ያገኘ ሁሉ የፖለቲካ ድል ለመጎናፀፍ የሚጥርበት ግንባር እንጅ የሆኑ አካላት በተመጣጣኝ አቅምና ጥቅማቸውን ባገናዘበ መንገድ የሚወያዩበት አልሆነም።

8/ ከተሳታፊዎች ጋር የሚነሳው የምርጫ ቅሸባ አይነት አካሄድ እንዳለ ሆኖ ምክክር ተደረገ ከተባለ በኋላ ይደረስበታል የሚባለው የውሳኔ ጉዳይም አሳሳቢና ከምክክር ፅንሰ ሀሳብ ጋር የሚቃረን ነው።

9/ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ውይይትና ሌሎች መፍትሄዎችን የሚያስናፍቅ ቢሆን አይገርንም። በተቃራኒው ግን ገዥዎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ችግር ሊፈታ ቀርቶ ሌላ የችግር መፈልፈያ አጋጣሚ እንዳይሆ የብዙሃን ስጋት ሆኗል። Getachew Shiferaw





MINILIK SALSAWI
Senior Member
Posts: 12348
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

የምክክር ሂደቱ በመንግሥት ተጠልፏል የሚል ስሜት እየተሰማኝ ነው ( ኮሚሽነሩ )

Post by MINILIK SALSAWI » 21 Jul 2026, 05:13

ምክክሩ ከሀምሌ 8/2018 ጀምሮ ከእኛ እጅ ወጥቷል - ኮሚሽነሩ

(ቦርከና ዜና) — የምክክር ጉባኤው የተመረጡት ስምንት አጀንዳዎች ተገፍተው መንግስት በመረጣቸው አጀንዳዎች ብቻ መደረጉ ተሰማ።

አንድ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራር ከቦርከና ሪፖርተር ጋር በተናጠል በነበራቸው ቆይታ "ከጉባኤው መጀመር በኋላ እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ ደፍረን ውሳኔ የምናስቀይርበት ሁኔታ ላይ አይደለንም ያለነው" ብለዋል።

ከህዝቡ በተሰበሰቡ አጀንዳዎች ሳይሆን መንግስት በመረጣቸው አጀንዳዎች ብቻ እንዲወሰን መደረጉን በማስታወስ "የምክክር ሂደቱ በመንግሥት ተጠልፏል የሚል ስሜት እየተሰማኝ ነው" በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል።

"ምክክሩ ከሀምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ ከኮሚሽኑ እጅ ወጥቷል" ሲሉ የገጠማቸውን ችግር አስረድተዋል።

አክለውም "እኛም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት መድረኩ በይፋ ከተጀመረ በኋላ የቁጥጥር ሂደቶች ይቀንሳሉ ብለን ተስፋ ብናደርግም፣ ጫናው ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል" በማለት ኮሚሽኑ ውስብስብ ችግር ውስጥ መግባቱን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉባዔውን ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን ክፍት ለማድረግ ቢወስንም ከላይ በመጣ ትዕዛዝ የተወሰኑ ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው ሚዲያዎች ብቻ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል።

ህዝቡ ቀድሞም ቢሆን በኮሚሽኑ የስራ ሂደት ጥርጣሬውን ሲገልፅ እንደነበር አስታውሰው የምክክር ሂደቱ አመኔታ ያጣል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ኮሚሽነሮቹ በተቻለ መጠን ግልፅነት ለመፍጠር የቻሉትን ሲሞክሩ እንደቆዩ ገልፀዋል።

MINILIK SALSAWI
Senior Member
Posts: 12348
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

የወቅቱ "ኮንፊውዝ" እና "ኮንቪንስ" .... ከአንድ ታዋቂ የህግ ባለሙያ የተላከ

Post by MINILIK SALSAWI » Yesterday, 00:28

የወቅቱ "ኮንፊውዝ" እና "ኮንቪንስ"
የምክክር ግቡ በሆነ ጉዳይ ወይም ጉዳዮች መግባባት ላይ መድረስ እንጂ በድምጽ ብልጫ ውሳኔ ማሳለፍ አይደለም። ውሳኔ አሸናፊና ተሸናፊ ይፈጥራል። በውሳኔ አሸናፊና ተሸናፊ መፍጠር ደግሞ ከምክክር (ዲያሎግ) መነሻ ተቃራኒ ነው። ምክክር ድርድር (bargaining or negotiations) አይደለም። ምክክር ዲያሎግ ድርድርም ሽምግልናም አይደለም። ምክክር የግልግል ዳኝነት (arbitration) አይደለም። ዝም ብሎ ውይይትም (discussion) አይደለም።
የኢትዮጵያው ግን አስቀድሞ ትኩረት የተረጠው መግባባት ላይ መድረስ ሳይሆን በባሌም በቦሌም ብሎ የያዙትን አቋም ችክ እንዳሉ፣ ጥቅምና እና ፍላጎት ማስጠበቅ ነው። አደረጃጀቱም ይሔንኑ አስረግጦ ለማስጠበቅ በምክክር ስም የመጣ ታክቲክ ነው። አዲሱ confuse and convince ማድረጊያ ነው።
የምክክር ውጤቱ መጨረሻ የሚቀርበው ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እና ለአስፈጻሚው (ለጠቅላይ ሚኒስትሩ) ነው። ማለትም ለብልጽግና ነው። ማለትም በገቢር ለኦሮህዴድ/ለኦሮሞ ብልጽግና ነው።
አራት ሺም በሉት ሰባት ሺ ህ የምክክር ተሳታፊ በብልጽግና ተደርሶና ተቀርጾ፣ በግልፅም በተዘዋዋሪም በብልጽግና እየተመራ ያለው ጉዳይ ነው። ከክልሎችና ከተሞች ተወካዮች (ከእያንዳንዱ 14) እና በፌደራል መንግሥት (በብሎጽግና) ተመርጠው ከሚወከሉ 15 ሰዎች በአብላጫ (በ70%) ውሳኔ እየሰጡበት አጀንዳዎች ላይ በተመካካሪዎች ስምምነት (አራት ሺህ/ሰባት ሺህ) በጭብጨባ አንከብክቦ ማሳለፍ ነው ተግባሩ። በጭብጨባ ያሳልፋል እንጂ በጭብጨባ ይጥላል አይልም። የኮሚሽኑ የውሳኔ አሰጣጥ መመሪያ) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ለብልጽግና) ይልካል። ብልጽግና እራሱ ጠምቆ እራሱ ይጠጣዋል ማለት ነው።
ክልሎችና ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬ ዳዋ) በ14 ውሳኔ ሰጪዎች (እጅ አውጪዎች) በእኩል ይወከላሉ። የፌደራል መንግሥት ደግሞ 15 ሰዎችን ይጨምራል፤እጅ እንዲያወጡ። ኦሮሚያ 14፣ ከአዲስ አበባ፣ ከድሬዳዋ እና ከሐረር ቢያንስ ግማሹ ኦሕዴድ መሆናቸው አይቀሬ ነው። አጠቃላይ 21 ማለት ነው። ከፌደራል 7 አያጣም። ከየክልሉ የሚጠራቀሙ፣ በኦሕዴድ ብልጽግና በእቅድ እጅ እንዲያወጡ የታጩ (የተመረጡ) ቢያንስ 30 የክልል ተወካዮች ማግኘት እጅግ በጣም ቀላሉ ነው። በመሆኑም በዚህም ቢሆን ኦሕዴድ ብልጽግና አስቀድሞ የጨረሰው ጉዳይ ነው። አዳማ ላይ በብልጽግና ደረጃ አቋም የተያዘባቸውን ጉዳዮች እንዳሉ ታውቋል። ቀጥሎ በምክክር ኮሚሽኑ እጅ ይወጣባቸዋል። በመቀጠልም በጭብጨባ ወደ ሕዝብ ተወካዮች (ወደ ብልጽግና) ይላካሉ። ይሁን እንጂ የምክክር ኮሚሽኑ የውሳኔ ሥርዓት/ሒደት የኦሮሞን ጥቅም የሚያሳጣ ነው በሚል በጎን ሆን ብለው ያስጮሃሉ። ምናልባትም አብይ አሕመድ ያስጮኻል። ይህ አዲሱ Confuse and convince ስልት እንጅ ቀድመው የጨረሱት ጉዳይ ነው። የምክክር ኮምሽኑ የተበላ ዕቁብ ነው!
(ይህ ፅሁፍ ከአንድ ታዋቂ የህግ ባለሙያ የተላከልኝ ነው)

MINILIK SALSAWI
Senior Member
Posts: 12348
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

የምክክር ሂደቱ በአገዛዙ መጠለፉንና አጀንዳዎች ተደልዘው ከኮሚሽኑ እጅ መውጣታቸውን አንድ የኮሚሽኑ አመራር ተናገሩ!

Post by MINILIK SALSAWI » Yesterday, 03:06

የምክክር ሂደቱ በአገዛዙ መጠለፉንና አጀንዳዎች ተደልዘው ከኮሚሽኑ እጅ መውጣታቸውን አንድ የኮሚሽኑ አመራር ተናገሩ!

ከሕዝብ ተሰብስበዋል የተባሉ አጀንዳዎች ተገፍተው በአገዛዙ በተመረጡ አጀንዳዎች ብቻ ምክክሩ እንዲመራ መደረጉን የገለፁት የኮሚሽኑ አመራር፡ "ከጉባኤው መጀመር በኋላ እኛ የምናውቀው ነገር የለም፡ ደፍረን ውሳኔ የምናስቀይርበት ሁኔታና አቅም አጥተናል" ብለዋል።

ይህም፡ መድረኩ የአገዛዙን ገጽታ ለመገንባትና ቅቡልነት ለማስገኘት የተደገሰ ሴራ እንጂ ለሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውጥረት ፋይዳ እንደሌለው ማረጋገጫ ሆኗል።

ይሄንን ተከትሎ፡ የፖለቲካ እስረኞች ሳይፈቱ፣ ጦርነቱ ሳይቆምና የሐሳብ ነፃነት ሳይከበር የሚደረግ የምክክር ሂደት ሀገሪቱን ከቀውስ እንደማያወጣ እና የአገዛዙን ገፅታ ከመገንባት የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው የፖለቲካ ምሁራኖች እየገለፁ ይገኛሉ።

ሙሉ መረጃውን በዚህ ተመልከቱ




Post Reply