Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
MINILIK SALSAWI
Senior Member
Posts: 11601
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

በአርሲ የ21 ኦርቶዶክሳውያን ተገደሉ፣ ቤተ ክህነቱ የኃዘን መግለጫ አወጣ; ተጨማሪ ሰባት ኦርቶዶክሳውያን ተገደሉ

Post by MINILIK SALSAWI » 01 Mar 2026, 00:56

በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሽርካ ወረዳ በጃዊ ቀበሌ 21 ኦርቶዶክሳውያን በታጣቂዎች ጥቃት ሕይወታቸው መገደላቸው ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።

VIDEO https://t.me/merejainformation/16415

በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሽርካ ወረዳ በጃዊ ቀበሌ 21 ኦርቶዶክሳውያን በታጣቂዎች ጥቃት መገደላቸውን በመግለፅ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ከሚመለከተው የፌደራል የመንግሥት አካላት ጋር ተወያይቶ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሶማሌ እና የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አሳሰበዋል።

ሊቀ ጳጳሱ እያሰለሰ በቀጠለው የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ችግር የካቲት 19 ለ20 አጥቢያ 21 ኦርቶዶክሳውያን የተገደሉ ሲሆን እነዚህም አንድ ካህን፣ ሁለት ሴቶች እና 18 ወንድ ኦርቶዶክሳውያን መሆናቸው ታውቋል።

ከተገደሉት በተጨማሪ ሁለት ክርስቲያኖች ታግተው ሲወሰዱ፣ ሌሎች ስምንት ወገኖቻችን በጎቤላ ሆስፒታል በሕክምና ላይ እንደሚገኙ በደብዳቤው ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በክርስቲያኖች ላይ በደረሰው ግድያ ጥልቅ ኀዘን እንደተሰማቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል። የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ሠፍሯል።
====

የኀዘን መግለጫ

በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሽርካ ወረዳ በጃዊ ቀበሌ 21 ኦርቶዶክሳውያን በታጣቂዎች ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን እንገልጻለን።

በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሽርካ ወረዳ በጃዊ ቀበሌ በታጣቂዎች ጥቃት የካቲት 19 ለ20 አጥቢያ አንድ ካህን፣ ሁለት ሴቶች እና 18 ወንድ ኦርቶዶክሳውያን በግፍ መገደላቸውን የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ለጽሕፈት ቤታችን ከጻፉት ደብዳቤ ስንመለከት እጅግ በከፍተኛ ኀዘን ተሰምቶናል።

በመሆኑም በሀገረ ስብከቱ በተለያዩ ጊዜያት በኦርቶዶክሳዊያን ልጆቻችን ላይ የሚፈጸመውና የተፈጸመው ዘግናኝና እጅግ አሳዛኝ ግድያዎች የኦርቶዶክሳዊያን ልጆቻችንን በየትኛውም የአገራችን ክፍል በነጻነት የመኖርና ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የመፈጸም መብትን የሚጋፋ በመሆኑ የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ጉዳዮን በልዩ ሁኔታ መከታተልና የማያዳግም መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ መፈለግ እንዳለባቸው እያሳሰብን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትም የአካባቢው ችግር በመሠረቱ እስከሚፈታ ድረስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።

በመጨረሻም በዚህ ዘግናኝና አሳዛኝ ግድያ ሕይወታቸውን ላጡ ልጆቻችን እግዚአብሔር አምላክ መንግሥተ ሰማያትን እንዲያወርስልን እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥልን የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የዘወትር ጸሎቷ መሆኑን እንገልጻለን።

አባ ሳዊሮስ
የአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

በምሥ/አርሲ ተጨማሪ ሰባት ኦርቶዶክሳውያን ተገደሉ፤ ቀብራቸው ዛሬ ተፈጽሟል
========
⚫️ " ትክክል ነው። የተገደሉት ሰባት ሰዎች ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ አስከሬናቸው ተገኝቷል። እነዚህ ትናንት ወዲያ ከተገደሉት 21 ምዕመናን ውጭ የተገደሉ ናቸው " (የአርሲ ዞን ሀገረስብከት)
+++++
ከትናንትና ወዲያ "21 ምዕመናን ሲገደሉ፣ ስምንት የደረሱበት አልታወቀም፣ ስምንት ሆስፒታል ገብተዋል፣ ሁለት ታግተዋል" በተባለበት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ትናንት ምሽት ተጨማሪ ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን መገደላቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአርሲ ዞን ሀገረ ስብከት፣ እንዲሁም በዞኑ የሽርካ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ ከትናንት ወዲያ ግድያ በተፈጸመበት በሽርካ ወረዳ ጃዌ ዋጩ ቀበሌ፣ ትናንት ምሽትም ሌላ ጥቃት ተፈጽሞ ሰባት ምዕመናን በታጣቁት አካላት ተገድለዋል ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አንድ የሽርካ ወረዳ ቤተክህነት አካል ዛሬ ከሰዓት በሰጡን ቃል፣ " ትናንት ምሽትም ሰባት ሰዎች ተገድለዋል። ቀብራቸው ዛሬ ተፈጽሟል " ብለዋል። በዚህም እስካሁን ተረጋገጠው መረጃ ብቻ በሁለት ቀናት በቀበሌው የተገደሉት ምዕመናን ብዛት 28 ደርሷል።

" ትናንት ማታም በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል። ሲቃጠሉም ነው ያደረሩት። አንድ ቤተክርስቲያን ተዘርፏል" ያሉን የቤተክህነቱ አካል፣ "ቤተክርስቲያን ዙሪያ ያለ ደጀሰላም እና አዳራሽ ተቃጥለዋል " ብለዋል።

"ሥጋቱ አሁንም እንዳለ ነው" ያሉም ሲሆን "ይህ ጥቃት የተሰነዘረበት ቤተ ክርስቲያን ጃዊ አቦ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እንደሚባል ገልጸው "የተወሰነ ኃይል ብቻ ከዞን መጥቷል። ሟቾቹ እንዲቀበሩ ያደረጉት እነርሱ ናቸው። ግን ይቆዩ፣ ይሄዱ ይሆን አይታወቅም " ነው ያሉት።

የአርሲ ዞን ሀገረ ስብከት በበኩሉ "የሚያገኟትን ነገር እየተጠቀሙ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠግተው ሲኖሩ የነበሩ አቃቢት እና ነዳያን በተጠቀሰው ቦታ ትናንት ምሽት በተሰነዘረ ጥቃት ተገድለዋል" ሲል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

ይህን ያሉት አንድ የሀገረ ስብከቱ አመራር በሰጡን ቃል፣ "ትክክል ነው። የተገደሉት ሰባት ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ አስከሬናቸው ተገኝቷል። እነዚህ ትናንት ወዲያ ከተገደሉት 21 ምዕመናን ውጭ የተገደሉ ናቸው" ብለዋል።

ከሟቾቹ ባሻገር "ደጀ ሰላሙ ሙሉ ለሙሉ ተቃጥሏል። የሰበካ ጉባዔው ጽሕፈት ቤት የስንዴ እህል ነበረው እሱም ወድሟል። ብዙ ቤቶችም ተቃጥለዋል" ሲሉ አክለዋል።