የሰሜን ሀይሎች የሞት የሽረት ትግል ስለሚያደርጉ ፣ መልከአምድሩ ስለሚያግዛቸው ፣ ጦርነቱም ስለሚራዘም ፣ የሎጀስቲክ ችግር ስለሚኖርና ደጀን ህዝብ ስለማይኖር ብልፅግና ድል አያገኝም።
Posted: 16 Feb 2026, 21:29
ከራሱ ስህተትና ከታሪክ ያልተማረው ብልፅግና! History repeats itself , first as tragedy , second as farce.
By Haileyesus Adamu
አውሮፓን አንድ የማድረግ ራዕይ የነበረው ናፖሊዮን ውድቀት መነሻ በ1812 ( እ.ኤ.አ) ወደ ሩሲያ ያደረገው ዘመቻ እንደነበር ይታወቃል። ከ 600,000 በላይ ጦር ይዞ ዘምቶ 100,000 ሺህ ወታደር ብቻ ይዞ ተመልሷል። ከ 130 አመት በሁዋላ አዶልፍ ሂትለር ዘመቻ ባርባሮሳ ( Operation Barbarossa) በሚል ለጀርመን አርአያን ዘር የመኖሪያ ስፍራ lebensraum ወይም (living space) ለማረጋገጥ ወደ ሩሲያ ፌዴሬሽን ዘመቻ አደረገ። የሂትለር የውድቀት ጅማሮ ይህ ከ western front በተጨማሪ ወደ ሩሲያ ያደረገው ኦፕሬሽን ባርባሮሳ መሆኑ እሙን ነው። ወደ ስታሊን ግራንድ ከዘመተው ከ 300,000 የጀርመን ጦር በህይወት ተርፎ የተመለሰው 6000 ወታደር ብቻ ነው።
ናፖሊዮም ሆነ ሂትለር ወደ ሩሲያ ያደረጉት ዘመቻ የውድቀታቸው ምክንያት የሆነው
1. ከፍተኛ የሎጀስቲክ ችግር ስላጋጠማቸው ፦ ጦራቸው ከመሃል አውሮፓ ወደ ምስራቅ ራሺያ በከፍተኛ ሁኔታ በመለጠጡ የለረዥም ግዜ የተሰላሰለ የሎጀስቲክ አቅርቦት ስርዓት ለመዘርጋት ተቸግረዋል።
2. ለሩሲያ ጦር የነበራቸው ዝቅተኛ ግምት (underestimation) ፦ ናፖሊዮም ሆነ ሂትለር ከሩሲያ በኩል ጠንካራ መከላከል ያጋጥመናል ብለው አልጠበቁም።
3. የራሺያ ከባድ ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ ( winter) ፦ ሁለቱም የራሺያ አስቸጋሪ የበረዶ ወራት ከመጀመሩ በፊት ጦርነቱን በአጭሩ መቋጨት እንችላለን ብለው ጠብቀው ነበር። ጦርነቱ ተራዝሞ የበረዶው ወራት ሲመጣ ግን ለራሺያ ሀይሎች የተሻለ ብልጫ ወስደው አሸናፊ መሆን ችለዋል።
ናፖሊዮን ሞስኮ ገብቶ ቢወጣም የሂትለር ጦር በቅርብ ርቀት ተሳልሟት ቢመለስም ይህ የምስራቅ ዘመቻ ለሁለቱም ውድቀት ሁነኛ ምክንያት ሁኗል።
ወደ ሀገራችን ስንመጣ በደርግ ግዜ በነ ጀኔራል አማን አምዶም የተጀመረውን የኤርትራን ጉዳይ በሰላም የመፍታት አማራጭ ወደ ጎን በመተው መንግስቱ ሀይለማርያም የቀይ ኮከብ ዘመቻ በሚል ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ዘመቻ አድርጎ ነበር። ይህ ዘመቻ ውጤታማ ባለመሆኑ በሂደት ደርግ ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ተሸንፎ ሀገሪቱን ለኢህአዴግ አስረክቧል። የቀይ ኮከብ ዘመቻ የከሸፈው ለምንድን ነው በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ምክንያቶች ቢቀርቡም በዋናነት ግን እነ ናፖሊዮን እና ሂትለር ሩሲያ ካጋጠማቸው ጋር ተመሳሳይነት አለው።
1. የሎጀስቲክ ችግር ፦ ከመሃል ሸዋ እስከ ሰሜን ምፅዋ የተለጠጠው የጦር ሀይል ለረዥም ግዜ የሚቆይ የሎጀስቲክ አቅርቦት ስርዓት አልነበረውም።
2. ለኤርትራ እና ለትግራይ አማፅያን የነበረው ዝቅተኛ አመለካከት ፦ በጦርና በመሳሪያ ብዛት በቀላሉ አማፅያኑን መደምሰስ ይቻላል ብሎ ማመን። በዛኛው ወገን ያሉት ጠንካራ ተጋድሎ እንደሚያደርጉ አለመጠበቅ።
3. መልከአምድሩ ፦ እነ ናፖሊዮን እና ሂትለር የራሺያ የበረዶ ወራት ወታደራቸውን እንዳሰመጠው የሰሜን ኢትዮጵያ ተራራማ እና በረሃማ ቦታዎች ከመደበኛ ወታደር ይልቅ ለጉሪላ ተዋጊው የተሻለ ብልጫ ስለሰጡ አብዛኛው የደርግ ወታደር በሰሜን ኢትዮጵያ ተራራዎች ተውጦ ቀርቷል።
ለውጡን ተከትሎ ራሱን ከኢህአዴግ ወደ ብልፅግና የቀየረው መንግስት ፈልጎትም ይሁን ተገዶ ራሱን የሰሜን ጦርነት ውስጥ አግኝቶታል። የጦርነቱ መነሻ የሰሜን እዝ መጠቃት ሆነም አልሆነም በመጀመሪያው ዙር ጦርነት መቀሌ በሁለት ሳምንት የገባው የብልጽግና ጦር ከወራቶች በሁዋላ በአሉላ ዘመቻ በተምቤን ተራራዎች ላይ ተመትቶ ከትግራይ ክልል አፈግፍጎ ለመውጣት ተገዷል።
ብልፅግና በመጀመሪያ ዙር ጦርነት በፍጥነት ያገኘውን ድል በዘላቂነት መቀየር ያልቻለው እነ ናፖሊዮን ሂትለር እንዲሁም ደርግ ያጋጠማቸው አይነት ምክንያቶች ስላጋጠሙት ነው።
1. የሎጀስቲክ ችግር ፦ ከአዲስ አበባ እስከ መቀሌና ሽሬ ጦርህ ከተለጠጠ ይህንን በዘላቂነት የሚያቆይ የተሰናሰለ የሎጀስቲክ ስርዓት ያስፈልጋል። ብልፅግና ጦሩን ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ለረዥም ግዜ የሚያቆይ ከፍተኛ የሎጀስቲክ ችግር አጋጥሞት ነው።
2. ለትግራይ ሀይሎች የነበረው ዝቅተኛ ግምት ፦ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒሰትር በፖርላማ " ተበትኗል ዱቄት ሁኗል ወዘተረፈ" እያለ የናገረው ንግግር ነው። የትግራይ ሀይሎች ጦርነቱን የህልውና ጉዳይ አድርገው ስለወሰዱት የሞት የሽረት ትግል አድርገዋል።
3. የትግራይ መልክዓምድር ፦ ተራራማው የትግራይ መልከአምድር ለአካባቢው ሀይሎች የተመቸ ሲሆን ለብልፅግና ጦር ግን ፈተና ሁኖበት ነበር።
አሁን ላይ ብልፅግና በድጋሚ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሀይሉን እያስጠጋ ነው። ይህ ጦርነት ከመጀመሪያው በምን ይለያል?
1. የሰሜን ሀይሎች በአንድ ጓራ የተሰለፉበት መሆኑ ፦ በመጀመሪያው ዙር ከብልፅግና ጎን ተሰልፈው የነበሩት የኤርትራ እና የአማራ ፋኖ ሀይሎች አሁን ላይ ከትግራይ ቲዲፍ ጋር በአንድ አይነት አሰላለፍ ውስጥ መሆናቸው።
2. የሱዳን ጦርነት ፦ በመጀመሪያው ዙር ጦርነት አንፃራዊ መረጋጋት ላይ የነበረችው ሱዳን አሁን የእርስበርስ ጦርነት ላይ መሆኑዋ እንዲሁም በሱዳን ያሉት ሀይሎች ከሁለት ጎራ ተሰልፈው በዚህኛው የሰሜን ጦርነት የሚሳተፉ መሆኑ
3. የግብፅ ሳውዲ አረቢያ እና UAE በየመንና በሱዳን እንደሚያደርጉት በዚህኛው ጦርነት በተለያዩ ጎራ ሁነው ሊሰለፍ የሚችሉበት እድል መኖሩ።
4. የጦርነት ሜዳው ከትግራይ ክልል በተጨማሪ አማራ ክልል እና ኤርትራን ሊያካትት የሚችል መሆኑ።
5. ብልፅግና ከትግራይ በተጨማሪ ከአማራ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ስለተጣለ ደጀን የሚለው ህዝብ ከጦርነት ሜዳው በጣም የራቀ መሆኑ ።
እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ አስገብተን ልንደርስበት የምንችለው ድምዳሜ ብልፅግና ከራሱ የቀደመ ስህተት ፤ እንዲሁም ከታሪክ መማር አለመቻሉን ነው። ብልፅግና የፈለገ ድሮን ፣ ተዋጊ ጀት፣ ከባድ መሳሪያ እንዲሁም የወታደር ብዛት ቢኖረው የሰሜን ሀይሎች የሞት የሽረት ትግል ስለሚያደርጉ ፣ መልከአምድሩ ስለሚያግዛቸው ፣ ጦርነቱም ስለሚራዘም ፣ የሎጀስቲክ ችግር ስለሚኖርና ደጀን ህዝብ ስለማይኖር ብልፅግና እንደሚያስበው በቀላሉ ድል አያገኝም። በተቀራኒው የውድቀቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ።
ለሀገራችን መልካም ሀሳብ ፣ ለህዝባችን በጎ መሻት ያለን ሁሉ ብልፅግና በሀገር ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈልግ ጫና ልናደርግ ይገባል። ከአማራም ሆነ ከትግራይ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ሀቀኛ ድርድር ያስፈልጋል ። ብልፅግና የሀገሪቱን ችግር ብቻውን እንደማይፈታው ተረድቶ ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ፊቱን ማዞር ይኖርበታል።
በመጨረሻም የዛሬ ፅሁፌ መቋጫ በመግቢያዬ ላይ ያሰፈርኩት የካርል ማርክስ ንግግር ይሆናል። History repeats itself, first as tragedy , second as farce.
Please wait, video is loading...