


ትንቢተ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 38
፩ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
፪ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በጎግ ላይና በማጎግ ምድር ላይ፥ በሞሳሕና በቶቤል ዋነኛ አለቃ ላይ አቅናበት፥ ትንቢትም ተናገርበት፥
፫ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሞሳሕና የቶቢል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ።
፬ እመልስህማለሁ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ፥ አንተንና ሠራዊትህንም ሁሉ፥ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ጋሻና ራስ ቍርን ሰይፍንም ያያዙትን ሁሉ፥ ታላቁን ወገን አወጣለሁ፥
፭ ፋርስንና ኢትዮጵያን ፉጥንም ከእነርሱ ጋር ጋሻና የራስ ቍርን የለበሱትን ሁሉ፥
፮ ጋሜርንና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻም ያለውን የቴርጋማን ቤትና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ ብዙዎችንም ሕዝቦች ከአንተ ጋር አወጣለሁ።
፯ አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ወገኖችህ ሁሉ ተዘጋጁ፥ አንተም ራስህን አዘጋጅተህ አለቃ ሁናቸው።
፰ ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፤ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘላለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፤ እርስዋም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች ሁሉም ሳይፈሩ ይቀመጡባታል።
፱ አንተም ትወጣለህ፥ እንደ ዐወሎ ነፋስም ትመጣለህ፤ አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ምድርን እንደ ደመና ትሸፍናላችሁ።
፲ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይገባል፥
፲፩ ክፉ አሳብንም ታስባለህ፥ እንዲህም ትላለህ። ቅጥርን ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፤ ተዘልለው ወደሚኖሩ፥ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡ እገባለሁ፤
፲፪ ምርኮን ትማርክ ዘንድ ብዝበዛንም ትበዘብዝ ዘንድ፥ ባድማም በነበሩ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ።
፲፫ ሳባና ድዳን የተርሴስም ነጋዴዎች መንደሮችዋም ሁሉ። ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን? ይሉሃል።
፲፬ አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለዚህ ትንቢት ተናገር ጎግንም እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል ሳይፈራ በተቀመጠ ጊዜ አንተ አታውቀውምን?
፲፭ አንተም፥ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ሁላቸው በፈረሶች ላይ የተቀመጡ፥ ታላቅ ወገንና ብርቱ ሠራዊት፥ ከሰሜን ዳርቻ ከስፍራችሁ ትመጣላችሁ።
፲፮ ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፥ ጎግ ሆይ፥ በዓይናቸው ፊት በተቀደስሁብህ ጊዜ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።
፲፯ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ በዚያች ዘመን ብዙ ዓመት ትንቢት በተናገሩ በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያቶች በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን?
፲፰ በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
፲፱ በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ። በእርግጥ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤
፳ ከፊቴም የተነሣ የባሕር ዓሣዎችና የሰማይ ወፎች የምድረ በዳም አራዊት በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ በምድርም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮችም ይገለባበጣሉ ገደላገደሎችም ይወድቃሉ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል።
፳፩ በተራሮቼም ሁሉ በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
፳፪ በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ።
፳፫ ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።