በዚህም ሶስት ዓመት ሙሉ የረባ ነገር መስራት ያቃታቸው ሽማግሌዎች በተጨመረላቸው የአንድ ዓመት ጊዜ ታዐምር እንደሚሰሩ ይደሰኩራሉ። እስከአሁን የታየው የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ውጤት እና አፈፃፀም ግን በስልጠና እና ስብሰባ ጨረር እየለቀቁ የፈረንጅ ፈንድ ማሳደድ...
ምንም ሳይሰሩ በሚዲያ ጋጋታ አጃክሞ መብላትና አየር መያዝ እንዲሁም ገዥውን ፓርቲ ማድመቅ ነው። እናም ትልምና ሕልም የሌለው በሕዝቡ ያልታመነ እርባናየለሽ ግሩፕ መሆኑ በስራው ተረጋግጧል። በዚህ ላይ የሀገር ሕመም፤ የወገን ስቃይ የማይገዳቸው የመንግስት አጀንዳ አስፈፃሚዎች መሆናቸው ታይተዋል።
ማንም እንደሚረዳው ምክክር የሚያስፈልገው ልዩነትን ለማጥበብ እና ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር ነው። በመሆኑም ዋንኛ የምክክሩ አካላት በተቃራኒ የፖለቲካ መስመር የተሰለፉ ሃይላት መሆን አለባቸው።
በተለይ ተቃራኒ የታሪክ አረዳድ ያላቸው፣ በሀገረ መንግስት ብያኔ የተለያየ እይታ ያላቸው፣ የሚጋጩ እና የተቃረኑ ትርክት ያነገቡ የፖለቲካ ሃይሎችን ማሳተፍ የውዴታ ግዴታ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በመንግሥት እንደተመሠረተው አይነት የብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን ከሆነ ከእከክልኝ ልከክልህ ያለፈ ሀገራዊ ፋይዳ አይኖረውም። ለዚህ ነው የጋሽ መስፍን አርአያ የምክክር ኮሚሽን አርአያ ላይሆን ከጅምሩ የወደቀው።
ምክክር ማለት ዛሬ እንደተካሄደው አይነት ነው። ለሀገራችንም የሚያስፈልጋት እንዲህ አይነቱ ነው። በተቃርኖ የፖለቲካ ጎራ የተሰለፉ...የሚጋጩ ሕልሞችን ያነገቡ...በታሪክ እና ትርክት የማይስማሙ ሃይላትን በአንድነት አሰባስቦ ስለ ሀገራቸው መፃኢ ዕድል እንዲነጋገሩ ማስቻል ትልቅ እርምጃ ነው።
ለሀገሪቱ የሚበጃት፣ ከጦርነት አዙሪት የሚያላቅቃት፣ የስቃይ ዘመኗን የሚያሳጥርላት...ከእሳት አበላ የሚያወጣት...ወደ ጋራ ሕልም የሚያሻግራት ይህ ነው። በመሆኑም እንዲህ አይነቱን [ምክክር] አጠናክሮ ሰፊው ሕዝብ ዘንድ ማስረፅ ያስፈልጋል። ከድፕሎማቲክ ማሕበረሰቡም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኝ መስራት ይገባል።
ጥላዬ ያሚ
.
.