https://ethiopianreporter.com/142009/
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈረንሣይ አገር ያስመጡት የመነጋገሪያ ስልክና የጦር ሜዳ መነጽራቸው እንዲሁም አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ተራራ ላይ ራሳቸውን ያጠፉበት ተመሳሳይ ናስማርስ ሸጉጥ የሰሜኑ ጦርነት ከመከሰቱ በፊትና በጦርነቱ ወቅት ከተዘረፉ ከ1,000 በላይ ውድና በዘመናችን ሊተኩ የማይችሉ ቅርሶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚህ ውድ የአገር ቅርሶች የተዘረፉት ደግሞ ከብሔራዊ ሙዚየም ቀጥሎ በርካታ ዕድሜ ጠገብ ቅርሶችን በውስጡ አካቶ እንደያዘ ከሚነገርለት በደሴ ሙዚየም፣ በንጉሥ ሚካኤል አይጠየፍ ቤተ መንግሥትና በመርሆ ቤተ መንግሥት ነው።
በሙዚየሙ ከነበሩት ከአምስት መቶ በላይ ቅርሶች መካከል በአሁኑ ወቅት የሚገኙት ከሁለት መቶ ያልበለጡ ቅርሶች ናቸው፡፡ ዘረፋውም በሕወሓት ታጣቂዎችና ጦርነቱን ተገን በማድረግ ለዘረፋ በተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተካሄደ ይታመናል።
የንጉሥ ሚካኤል ሰዓትና ማበጠሪያ፣ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ የዝሆን ጥርስ፣ ከ450 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ የሸክላ ዕቃዎችና ሌሎች በሙዚየሙ የሚገኙ በርካታ ቅርሶች ተዘርፈዋል፡፡ ቀሪዎቹም ተሰባብረዋል፡፡ ዛሬ ላይ ሙዚየሙ እዚህ ግባ የሚባል ቅርስ የለውም፡፡
የደሴ መዚየም በ1909 ዓ.ም. ደጅ አዝማች ዮሴፍ ብሩ በህንዳውያን ጠበብቶች ያሠሩት ቤተ መንግሥት ሲሆን፣ በ12,565 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈና 22 ክፍሎችን የያዘ ጥንታዊ ቤተ መንግሥት ነው። በቀድሞ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ትዕዛዝ በ1973 ዓ.ም. ወደ ሙዚየምነት የተቀየረው ቤተ መንግሥት፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሙዚየምነት ሲያገለግል ቆይቶ በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከመዘረፍ አልፎ በርና መስኮቶቹ በጥይት ተበሳስተው ታሪካዊ ውድመት ደርሶበት ነበር።
የተዘረፉ ቅርሶችን ከማስመለስ አኳያ አመርቂ ውጤት ባይገኝም ከተዘረፉት 550 ቅርሶች መካከል 15 የሚሆኑት ብቻ መመለሳቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መቆያ ማሞ ለሪፖርተር ተናግረዋል። ሙዚየሙ በጦርነት ወቅት ከደረሰበት ጉዳትና ዘረፋ በተጨማሪ በዕድሜ ብዛትና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር አቶ መቆያ ተናግረዋል፡፡
-
- Member
- Posts: 4380
- Joined: 15 Jun 2018, 17:40