(በአፋን ኦሮሞ ጽፌው ሌሎች ወደ አማርኛ የተረጎሙት )
አብይ አህመድ እና የብልጽግና ደሴት ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እየደረሰ ካለው የኢኮኖሚ እና የጸጥታ ቀውስ የሕዝቡን ትኩረት ለማስቀየስ እየተጠቀሙባቸው ካሉት ዜዴዎች አንዱ የባህር በር ፕሮፓጋንዳ ነው።
በርግጥ የባህር በር መኖር ለየትኛውም ሀገር ኢኮኖሚ እና ደህንነት ፋይዳ አለው። ነገር ግን ሁሉም ሀገራት ባህር ስለማያዋስናቸው (landlocked ስለሆኑ) ወደብ የማግኘት እድል የላቸውም። ይህንን እድል ካጡ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች። ሀገራችን የባህር በር ያጣችበት ምክንያት ውስብስብ ከሆነው የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት አፈጣጠር ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው።
ኢትዮጵያ በባህር የተከበበች ባትሆንም የባህር አገልግሎት እንዳይኖራት የሚከለክላት ነገር ግን የለም። ይህንንም በሕግ እና በኢኮኖሚ ማረጋገጥ ትችላለች። በሕጋዊ መልኩ የተባበሩት መንግስታት የባህር ሕግ ኮንቬንሽን (UNCLOS) ከባህር የማይዋሰኑ የጎረቤት ሀገራት ወደቦችን የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ይህ ማለት የባህር ድንበር ያላቸው ሁሉም ጎረቤት ሀገራት ድንበር ላልሆኑ ሀገራት የወደብ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል። አፈፃፀሙ በድርድር እና በስምምነት ላይ የሚመሰረት ይሆናል።
ይህ ማለት ከሕግ አንጻር ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ምንም አይነት አተካሮ ውስጥ መግባት አያስፈልጋትም። የባህር በር ለመጠቀም ከጎረቤት ሀገራት ጋር መዋጋት ይቅርና መለመን እንኳን የለባትም። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች አሉ፦
1. የባህር ዳር-ድንበር ባላቸው አምስት ጎረቤት ሀገራት ተከበናል። ከእነዚህ አምስት ሀገራት ውስጥ የሦስቱን (ጂቡቲ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ) ወደቦች መጠቀም የምትችል ብቸኛዋ ጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያ ነች። የእነርሱ ብቸኛ ደንበኛ መሆን እንችላለን ማለት ነው። የተቀሩት ሁለቱ ሀገራት (ኬንያ እና ሱዳን) እንኳን ቢሆኑ ወደቦቻቸው ብዙ ተጠቃሚ ደንበኛ የላቸውም። ይህ ስለሆነ እነዚህን ጎረቤት ሀገራት አወዳድረን መምረጥ እንችላለን። ስለዚህ እነዚህ ሀገራት እኛን “ወደቦቻችንን ተጠቀሙ” እያሉ የተሻለ ዋጋና አገልግሎት በማቅረብ ሊወዳደሩ ይገባል እንጂ እኛ እነሱን የምለምንበትም ሆነ የምንዋጋበት ምክንያት የለም። ለምሳሌ ኡጋንዳ እንደ ኢትዮጵያ የባህር ድንበር የላትም። ከኬንያ እና ከታንዛኒያ የተሻለ ዋጋ እና አገልግሎት ያለውን አወዳድረው ይጠቀማሉ። እኛ በአምስት አገሮች የተከበብነው ደግሞ የተሻሉ ብዙ ምርጫዎች አሉን ማለት ነው።
2. ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት እና የቆዳ ስፋቷም ግዙፍ በመሆኑ፤ ሰፊ የገበያ፣ ማለትም አምራችና ሸማች አላት። ወደ ውጭ የሚላኩ እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ እየሄዱ ነው። ይህ ማለት ባለ ወደብ የሆኑት ጎረቤቶቻችን ይህን የእኛን ሰፊ ገበያ ለመቀራመት እንዲወዳደሩ ትልቅ ኃይል ይሰጠናል።
ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ለምን አወዛጋቢ አጀንዳ ይሆናል? ሁለት ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው ከታሪክ የወረስነው ቁርሾ የሚፈጥረው ጥርጣሬ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ የአብይ አህመድ የጦረኝነት ፖለቲካ አካሄድ ነው።
ታሪክ፦ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና በተወሰነ ደረጃ ከሱዳን ጋር የግጭት እና ውዝግብ ታሪክ አላት። እነዚህ ታሪካዊ ቁስሎች በአግባቡ ስላልዳኑ ኢትዮጵያ የእነዚህን ሀገራት ወደቦች፣ በተለይም ለወታደራዊ አገልግሎት የምትጠቀም ከሆነ በእኛ ላይ የበላይነት በማግኘት ትደፈጥጠናለች ብለው ይሰጋሉ።
የአብይ የጦረኝነት ፖለቲካ፦ አብይ የባህር በር ጉዳይን ያነሳበት ሁኔታ እና ጊዜ ከላይ የተጠቀሰውን ታሪካዊ ቁርሾ በመቀስቀስ ለጎረቤት ሀገራት ተቃውሞ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። የሶማሌላንድን የባህር በር ለማግኘት የተደረገውን የከሸፈ ሙከራ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሶማሌላንድ ከሶማሊያ የተገነጠልች ቢሆንም እንደ ነፃ ሀገር እውቅና ስላላገኘች የባህር በር ጉዳይ ላይ ስምምነት መፈፀሟ (በተለይም የጦር ወደብ) ቀድሞውንም ከኢትዮጵያ ጋር ታሪካዊ ቅራኔ ያላትን ሶማሊያን ክፉኛ አስቆጣ። ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና ለመስጠት የገባችው ቃል ደግሞ ሶማሊያን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም መሰል ጉዳዩች የሚያሳስባቸው ሀገራትንም አስደነገጠ። ስለዚህም እንደ ቻይና እና አሜሪካ ያሉ በሌሎች ጉዳዮች ባላንጣ የሆኑ ሀገራት በአንድ ድምፅ ኢትዮጵያን አወገዙ። በተጨማሪም በሶማሊያ ውስጥ የጎሳ ጉዳይ ጠንካራ መሆኑ እየታወቀ የገዳቡርሲ ጎሳ የሆነውን የባህር ዳርቻ መሬት ለመውሰድ ከይስሐቅ ጎሳ ከሆነ ፕሬዝዳንት ጋር ነው ስምምነት የተፈፀመው። ይህ ማለት ሌሎች እክሎች ባይኖሩ እንኳን የገዳቡርሲ ጎሳ አባላት የወደቡን ግንባታ እና ሥራ አይፈቅዱም፤ ለማትጓጎልም ይሰሩ ነበር።
ታዲያ ወደብ ለማግኘት አብይ ቀላሉን መንገድ ትቶ ውስብስቡን ለምን መረጠ? የእውነት አቅዶበት እና ተዘጋጅቶ የገባበት ነገር አይደለም። የሶማሌላንዱን ስምምነት ሲያደርግ ‘የባህር በር አስገኘሁኝ’ በሚል ፕሮፓጋንዳ የሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎችን ለመመከት ይጠቅመኛል ብሎ አስቦ ነበር። በሶማሊያን ድንበር የባህር በር የማግኘት እውነተኛ እቅድ ቢኖረው ኖሮ የእርሱ ሸሪክ የነበረው ፈርማጅሆ ፕሬዝዳንት እያለ ስምምነት ማስፈረም ነበረበት። በተመሳሳይ መልኩ በአሰብ ወደብ ጉዳይ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ቢፈልግ ኖሮ ከኢሳያስ ጋር በአንድ ሳንባ ካልተነፈስን በሚሉበት ጊዜ መፈጸም ነበርበት። ሆኖም የባህር በርን ጉዳይ ከኤርትራዊያን ጋር አንድም ቀን በቅጡ ተነጋግሮ እንደማያውቅ በጫጉላ ሽርሽሩ ጊዜ በቅርብ ከነበሩ ሰዎች ማረጋገጥ ይቻላል። የአሰብን ጉዳይ እንደ አጀንዳ ያነሳው ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ከኢሳያስ ጋር ፀብ ውስጥ ስለገባ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጎኑ በማሰለፍ ሊመጣ በሚችል ግጭት ውስጥ ራሱን ለማዳን ነው።
ለመሆኑ ብልጽግናዎች እንደሚሉት እነሱ የአሰብን ወደብ በወታደራዊ መንገድ ማግኘት ያዋጣል ወይ የሚለውን እንይ። አሰብን ለመያዝ የሚደረገው ወታደራዊ አካሄድ በሦስት ደረጃዎች ሊከናወን ይችላል፦
1. የመጀመርያው አሁን ያለውን የኤርትራ መንግስት ገልብጦ የአሰብ ወደብን ለኢትዮጵያ አሳልፎ የሚሰጥ መንግስት ማቋቋም ነው (Regime Change)፦ ውስብስብ የሆነው የኤርትራ ውስጣዊ ፖለቲካ እና የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ ይህን ማድረግ ያስችላል ወይ የሚለውን ለጊዜው እንተወው። ቢቻል እንኳን የኤርትራ ብሔርተኝነት ከ70 ዓመታት በላይ በጦርነት ወላፈን ሲግል የነበረ በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ የምታስቀምጠው ቡድን ከጅምሩ ከፍተኛ የቅቡልነት ችግር ስለሚገጥመው አንድ ስንዝር መሬትን የመስጠት አቅም አይኖረውም። ከሰጠ ደግሞ ውሎ ሳይደር በውስጣዊ አመጽ ይናጣል። ለዚህ ማሳያው አብይ የወደቡን ጉዳይ እንዳነሳ የኢሳያስን መንግስት ክፉኛ በመኮነን የሚታወቁ የኤርትራ ተቃዋሚዎች እንኳን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መቃወማቸው ነው። የብሔርተኝነትን ኃይል መረዳት የፈለገ ትግራይን ለመደፍጠጥ የተደርገውን ሙከራና የገጠመውን ፈተና ማስተወስ ይኖርበታል።
2. ኤርትራን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ስር መመለስ (Reincorporation)፦ ይህ የዓለም አቀፍ ሕግን መጣስ ብቻ ሳይሆን የኤርትራ ብሔርተኝነት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ማለቂያ ወደሌለው ጦርነት መግባት ነው።
3. በአሰብ ዙሪያ ያለውን መሬት ቆርጦ ወሰድ (Annexation) ፡- ይህ ለጊዜያዊ ፕሮፓጋንዳና ሕዝቡን እልል ለማስባል ይጠቅም ይሆናል። የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰትን ወደ ጎን እንተውና ፤ አሰብን በጉልበት ቆርጦ ለመጠቀም የማያቋርጥ ወታደራዊ ጥበቃ ያስፈልጋል። በዚህ ዓይነቱ ጦርነት ምክንያት በሰው እና በገንዘብ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ከወደቡ ከሚገኘው ትርፍ አንፃር አዋጭ ይሆናልን?
በአጠቃላይ በጦርነት የባህር በር ተጠቃሚ ለመሆን መሞከረ ከሚያስገኘው የትኛውም ጥቅም ይዞ የሚመጣው መዘዝ ይበልጣል። የሚያስከትለው ቀጣይነት ያለው ጦርነት እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ወደቡን ማግኘት ከሚያስገኘው ጥቅም በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በደርግ ዘመን የአሰብ እና የምፅዋ ወደቦች ቢኖሯትም እነዚያ 17 ዓመታት የኢኮኖሚ ውድቀት የታየባቸው ጊዜያት ነበሩ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከ1998 በኋላ እነዚህን ሁለት ወደቦች እንዳትጠቀም ብትከለከልም ኢኮኖሚዋ በፍጥነት ያደገበት ዘመን ነበር። ልዩነቱ ምንድን ነው? በደርግ ዘመን ኢትዮጵያ ወደብ ቢኖራትም ከፍተኛ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ነበረች። በኢሕአዴግ ዘመን ግን ወደብ ብታጣም አንፃራዊ ሰላም ነበራት።
ሰላም ካለ ውሎ ቢያድርም የባህር በር ለማግኘት የሚስችል ሁኔታን መፍጠር ይቻላል። የወደብ መኖር ግን የሰላም ዋስትና ሊሆን አይችልም። ሰላም ያላት ሀገር ኢኮኖሚዋን በመሳደግ በተለያየ ስልት የባህር በር ባለቤት ለመሆን የሚያስችላትን ሁለገብ ጉልበት መገንባት ትችላለች። ውስጣዊ ሰላም የሌላት ሀገር ግን ስፍር ቁጥር የሌለው የባህር በር ባለቤት ብትሆን እንኳ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ልትጠቀምበት አትችልም። ረዣዥም የባህር ዳርቻ ያላቸውን የመን እና ሶማሊያን እንደምሳሌ እንውሰድ። የመን ከቀይ ባህር እስከ አረቢያን ባህር የሚዘልቅና 2,252 ኪ.ሜ የሚረዝም የባህር ድንበር አላት። ሶማሊያ ደግሞ በአፍሪካ ረዥሙ የሆነውን 3,330 ኪ.ሜ የሚዘቅ የባህር ዳርቻ ተፈጥሮ አድሏታል። ነገር ግን እነዚህ ሁለት ሀገራት ነፃነታቸውን ከተጎናጸፉ ወዲህ ሰላም ኖሯቸው ስለማያውቁ፣ ብዙ ወደቦች ቢኖሯቸውም ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ አልረዳቸውም። ዛሬም ከዓለም ፍጹም ደሃ ከሆኑ ሀገራት ተርታ ተሰልፈው ቀጥለዋል።
የወደብ ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ መቀረቡ ብቻውን ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያለትን ጥቅምና መብት ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል ይላሉ የብልጽግና ሰዎች። እውነት ነው። ነገር ግን ይህን አጀንዳ አጋንኖ ማቅረብ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳትም አስከትሏል። ከሶማሊያ ጋር የነበረው እሰጣ ገባ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሎ ያለፈ ክስተት ነበር። የሀገራትን ሉዓላዊነት የማናከበር፣ በጉልበተኛነት (aggressor) እንዲንፈረጅ አድርጓል። ሶማሊያንም፣ ሶማሌላንድንም አስከፍተን ከሁለት ያጣ ሆነናልም። ከአሰብ ጉዳይ ጋር ተያያዞ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ሽኩቻ ደግሞ ወደ አውዳሚ ጦርነት ሊወስደን ይችላል።
በአጭሩ በባህር በርም ሆነ በሌላ ጉዳይ አብይ እየተከተል ያለው የጦረኝነት ፖሊቲካ ድሮ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ምሰሶ (anchor state) እየተባለች ስትወደስ የነበርችዋን ኢትዮጵያ፣ የአካባቢው ዋና የግጭት አምራች (net insecurity exporter) ሆና እንድትታይ አድርጓል። በተጨማሪም ይህ የባህር በርን በጉልበት የመጎናጸፍ አጀንዳ የአፍሪካ ቀንድን ተፈጥሯዊ ሀብት መቀራመት የሚፈጉ ኃይሎች ተንጋግተው እንዲመጡ በመጋበዝ፣ የአከባቢውን ሀገራት የውስጥ ፖሊቲካና ጉርብትና ለጣልቃ ገብነት ተጋላጭ አድርጓል።
በአጠቃላይ የባህር በርን በተመለከተ አብይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከተለው መንገድ፣ አስቀድሞ የታሰበበት በተጠና እቅድ የተመራ ሳይሆን፣ ለጊዜያዊ ሞቅታ ሲካሄድ የነበረ በመሆኑ፣ የታሰበውን የባህር በር ማስገኘቱ ይቅርና፣ ወደፊት ለማግኘት ያለን እድልም ያጠበበ ሆኗል። የጎረቤት ሀገራትን ወደብ በጉልበት ለመውሰድ መዛቱና መሞከሩ፣ እነዚያን ሀገራት ስጋት ውስጥ በመክተት የኢትዮጵያ ጠላት ከሆኑ ሀገራት ጋር እንዲወዳጁ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የውስጥ ግጭት አሉታዊ ሚና እንዲጫወቱ በመገፋፋት የጸጥታና ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራን አከናንቦናል።
አሁን ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ጦርነት እየተናወጠች ባለችበት ወቅት ‘በባህር በር’ ስም ሌላ ጦርነት መጨመር የአገሪቱን ህልውና ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የሚከት ነው። በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ወደብ የሌላት ሀገር እንደመሆኗ በዓለም አቀፍ ሕግ የተደነገገ ወደቦችን የመጠቀም መብት አላት። ከዚህም በላይ ሰፊ ገበያ ያላት ሀገር እና በአምስት የባህር በር ባላቸው ሀገራት የተከበበች በመሆኗ አወዳድራ በርካሽ ዋጋ መጠቀም ትችላለች። ስለሆነም በዚህ በአሁኑ ወቅት በወታደራዊ ኃይል የትኛውንም ጎረቤት ሀገር ለማስፈራራት ከመሞከር ይልቅ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ትስስርን በማጠናከር ጥርጣሬን እና ፍርሃትን በመቀነስ የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ወደቦችን ማልማት የተሻለ ነው።ውስጣዊ ሰላማችንን አረጋግጠን ኢኮኖሚያችን መልሰን በመገንባት የማምረትና የመሸመት አቅማችንን የበለጠ ስናሰፋ፤ ዛሬ ወደብ ላለመስጠት የሚያንገራግሩ ሀገራት "ኑ ውሰዱ" ብለው ደጃችን ይጠናሉ።
ይህም ስለሆነ ህዝባችን የባህር በርን አስመልክቶ በአሁኑ ወቅት የሚደርግን ጠብ ዓጫሪ ፕሮፓጋንዳም ሆነ ጦርነት ከሚኖረው ፋይዳ ይልቅ የሚያስከትለው አደጋ እጅጉን ስልሚያይል ሊቃወመው ይገባል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባው ጉዳይ የእርስ በእርስ ጦርነቶችን አስቁመን ሰላምን በማስፈን በጦርነት የወደሙ ማህበራዊና እሴቶች እና ኢኮኖሚያዊ መሰረተልማቶችን ጠገነን ሁለንተናዊ አቅመችንን ማጠናከር ነው። ሰላምና ልማታችንን በአስተማማኝ መሰረት ላይ ካቆምን በኃላ ለባህር በር ጉዳይ በሙሉ ቀልብእና አቅም መፍትሄ እናፈላልጋለን።