የኤርትራ ወጣቶች የጨለመ ተስፋ!
Posted: 13 Apr 2025, 12:15
ነጻነትን ፍለጋ...: የኤርትራዊው ስደተኛ ማስታወሻ

የኤርትራ ወጣቶች የራሳቸው ዘላቂ ተስፋ፣ ራዕይና የሕይወት ግብ የላቸውም፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በግዴታ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ነው የሚያጠናቅቁት። ሳዋ በተባለው የወታደር ማሰልጠኛ ማእከል ሁለንተናዊ ሰብኣዊ መብታቸው ይጣሳል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በወቅቱ የ 17 ዓመት ታዳጊ የነበረው ዘካርያስ ክብረኣብ ከዚህ የግዴታ ውትድርና ለማምለጥና ነጻነቱን ለመቀዳጀት የነበረው ብቸኛ አማራጭ ወደ አውሮፓ አህጉር መሰደድ ነበር። ቢሆንም በአፍላ አእምሮው አስቀድሞ በኤርትራ ርእሰ መዲና አስመራ ሳለ እንዳሰበው የስደት ጉዞው አልጋ ባልጋ አልነበረም። ወደ አውሮፓ አህጉር ለመድረስ ለወራት ያህል በቃላት ለመግለፅ የሚከብዱ ስቃዮችን፣መከራዎችንና ሰቆቃዎችን ተቋቁሞ ማለፍ ነበረበት። ታዳጊው ዘካሪያስ በዚህ መከረኛ ጉዞው በሰሀራ በረሃ በብርቱ ውኃ ጥም የተነሳ ከሞት አፋፍ ደርሶ ለጥቂት በተዓምር ተርፏል፡፡በሜዲቴራንያን ባሕር ጉዞውም በረሃብ፣በብርቱ ንፋስና ዝናብ እንዲሁም በኃይለኛ የማዕበል ወጀብ ከሞት ጋ ግብግብ ገጥሞ ሕይወቱ ለጥቂት ተርፋለች። አውሮፓ ከገባም በኋላ ካሰበውና ካለመው በተቃራኒ በጣልያን አገር ሚላን ከተማ ውስጥ አሰቃቂ የጎዳና ሕይወትን ለመምራት ተገደደ። በጀርመን አገር በስደት የተነሳ እስራትንና የወኅኒ ሕይወትን ተጋፍጧል፡፡ ከእስራቱ በኋላም ወደ ትውልድ ሃገሩ እንዲመለስ ተወሰነበት፡፡ ይህንን ሁሉ ፈተና አሸንፎ ያለመውን ነጻነት ለመቀዳጀትና የጥገኝነት ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ የተሻለ ሕይወትን ለመምራት ለበርካታ ዓመታት በስዊዘርላንድና በጀርመን በሚገኙ በርካታ የስደተኛ መጠለያ ማዕከላትና ጣቢያዎች ብዙ መታገልና ሕይወትን የሚያስከፍሉ ፈታኝ መሰናክሎችን ማለፍ ነበረበት።
ይህ የዓመታት የጉዞ ማስታወሻው ከትውልድ ከተማው አስመራ አንስቶ ያለመውን ተፈጥሯዊ ነጻነቱን እስኪቀዳጅ ድረስ ያደረገውን መልከ ብዙ የሕይወት ፍልሚያና የስደት ጉዞ ያሳያል፡፡