Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
MINILIK SALSAWI
Member+
Posts: 9546
Joined: 24 Aug 2012, 12:02
Contact:

በኦሮሚያ ክልል አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ተገደሉ

Post by MINILIK SALSAWI » Today, 12:35

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሱሉልታ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ የሆኑት አበበ ወርቁ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው አማጺ ቡድን በደረሰባቸው ድንገተኛ ጥቃት መገደላቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።

ታጣቂ ቡድኑ ጥቃቱን የፈጸመው ዛሬ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ መሆኑን የገለጹት የዋዜማ ምንጮች፣ ከወረዳ አሥተዳዳሪው ጋር የነበረ የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ በቡድኑ ታፍኖ መወሰዱን አስረድተዋል።



ዋና አሥተዳዳሪው፣ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊው እና በርካታ የጸጥታ ኃይሎች ታጣቂ ቡድኑ በስፋት ይንቀሳቀስበታል ወደተባለው "ሞዬ ጋጆ" በተባለው ስፍራ ሲደርሱ አማጺ ቡድኑ ድንገተኛ የእሩምታ ተኩስ እንደከፈተባቸው ተጠቁሟል።
በዚህም ዋዜማ ለጊዜው ቁጥራቸውን ማጣራት ያልቻለችው የጸጥታ ኃይሎች ሲገደሉ፣ በርካቶች ደግሞ ቆስለው ጫንጮ ሆስፒታል መግባታቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

ከጸጥታ ዘርፍ ኃላፊው በተጨማሪ በርካታ የጸጥታ ኃይሎች በቡድኑ ታፍነው መወሰዳቸውንም ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት መረዳት ችላለች።

ከወራት በፊትም በተመሳሳይ በዚሁ ታጣቂ ቡድን ጥቃት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኮማንደር ለገሰ ሥዩም መገደላቸውን ዋዜማ መዘገቧ ይታወሳል።

ሟቹ አበበ ከሁለት ዓመት በፊት የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ ሆነው ከመሾማቸው በፊት፣ የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ እንደነበሩ ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል።