ስለ ምን እንደ ሆነ ያለዉ ነዉ በትክክል ኣዉቃለሁ ማለት የሚችለዉ።
እኔ ስለ ምን እንደ ሆነ ገና እንደሰማሁ ገምቻለሁ።
በቅርቡ እኔ ከገመትኩኝ ፍጹም የራቀ ትርጉም በኣንድ ኢትዮጵያዊ አደባባይ ሲነገር ሰምቼ የእኔ ግምት እና የእሱ ትርጉም መራራቅ ደነቀኝ።
ተመሳሳይ አስተያየት በኢትዮጵያዊያን፣ ያዉም አሜሪካ በኖሩ፣ ሲደጋገም ያስደነግጣል።
ምን ማለቱ እንደሆነ በትክክል እስከሚታወቅ ግምቶቻችን እናወራለን።
የእኔን ግምት ለማጋራት ለዘመድኩን በቀለ የኣንድ ቀን የቤት ስራ ልስጥ። አደባባይ ወጥቶ ሲናገር ስለሰማሁት ግምቱን መርምሮ ለማስተካከል ወይም ትክክል ነዉ ብሎ በግምቱ ለመጽናት።
የኣንድ ቀን የቤት ስራዉ ቀላል ነዉ።
ዘመድ በቀለ ብለህ ከማዉራት ኣንድ ቀን ዕረፍት ዉስድ።
ጠዋት ተነስተህ ከኣልጋ ሳትወርድ መብራት ኣብራ። ድሮ ሰዉ ነቅቶ የጸሃይ ወይም የጨረቃ ብርሃን ከማየት ወደ ኤሌክትሪክ ብርሃን ያሻገረዉ ማን ነበር ብለህ ጠይቅ። ኣፍርካ ዉስጥ ወይም በኣፍርካ ሰዉ ነበር?
ፊትህን ለመታጠብ ይሁን ሻወር ለመዉሰድ የምትጠቀመዉን ዉሃ ወንዝ ሄደህ በእንስራ ከማምጣት ማን ነበር ዉሃን ወደ ላይ ማፍሰስ ችሎ ቤትህ ዉስጥ ያደረሰዉ?
ሻወር ወስደህ መቼም ቡና ማፍላትህ ኣይቀርም፣ ኢትዮጵያዊ ስለሆንክ። እንጨት እያንጣጣህ፣ ቡና ሙቀጫ ዉስጥ ወቅጠህ፣ ጀበና ገነፈለ ወይም ኣልገነፈለም እያልክ ከመጠበቅ፣ ቡና በኣፍታ ፈጭተህ፣ በኣፍታ ቆር ቆር ማድረግ የመጣዉ የት እና መቼ ነበር?
ቁርስ ብለህ ፍሪጅ መክፈትህ ኣይቀርም። ያንን ከሳምንት በፊት የገዛሀዉን ዳቦ እንዳይሻግት ፍሪጅ የፈጠረዉ ማን ነበር?
ቤቱ ቀዘቀዘ ብለህ ጋቢ እንዳትደራርብ የቤትህን ማሞቅያ የሰራዉ ማን ነበር?
ሸንቀጥ ለማለት ወደ ጅምናዝየም ኣቀናህ። ሜዳ ላይ ወጥተህ ከመሮጥ ቤት ዉስጥ ዱብ ዱብ የምትልበትን ማን ነበር የፈጠረዉ? ሌሎቹንም እንደዛዉ። እሺ ፈልገህ ፈልገህ ቦፍሌክስን ኣገኘህ። በኢትዮጵያዊ የተፈጠረ።
ትንሽ ከተረጋጋህ በኋላ አሎ ለማለት ስልክ ኣነሳህ። ማን ነበር ኡኡ ብለህ ከመጣራት ገመድ ዉስጥ እና በሳተላይት ድምጽህን ማስተላለፍ የፈጠረዉ?
ሳተላይት ስትል ከመንኮራኩር በፊት በጣም ቀድሞ የተፈጠረዉ ተሽከርካሪ መኪናን ማን ነበር የፈጠረዉ?
መኪና ብለህ ባቡር ማስታወስህ ኣይቀርም። ባቡር ብለህ ኣይሮፕላን ማስታወስህ ኣይቀርም።
የት እና በእነማን ነበር የተፈጠሩት?
ትንሽ ተረጋግተህ መልሶ ኣገረሸብህ?
እስቲ ልዝናና ብለህ ቲቪ ለመክፈት ሪሞት ኣነሳህ። ሪሞቷ ብልጭ ብላ ቲቪዉን ቦግ ኣደረገችልህ። የማይታየዉን ሴንሰር ወደ ቲቪ ልኮ የሰዉን ምስል እና ድምጽ ቤትህ ዉስጥ ያመጣልህ ማን ነበር?
ቲቪዉም ሰልችቶህ ኮምፒዩተር ወይም ስማርት ፎን ከፈትክ። ዲጅቱን እና ኮምፕዩተሩን ማን ፈጥሮት ነዉ ዩትዩበሮች የሚንጣጡት?
ከስራ ዕረፍት ኣገኘሁ ብለህ ስራ በዛብህ? ፈልጌ ፈልጌ ኣነሰኝ ብለህ ኣለቃቀስክ? ኣይዞህ ማሙሽ። መጽናኛ ኣታጣም።
ከዚህ ሁሉ በፊት የጥንት ፈጠራ ሀ ሁ ነበር። ያየሃቸዉ ሁሉ ስም ኣላቸዉ። ተቀርጸዉ የሚታዩ። ብትፈልግ ሀ ሁን እያንዳንዱ ስም ዉስጥ ታገኛለህ።
ኣሁን ትንሽ ተረጋጋህ? የቴዲ አፍሮን ከፊት የነበርነዉ ወደ ኋላ ቀርተንን እንጉርጉሮ ፈልገህ ኣዳምጥ እና ነገም ቀን ነዉ በል።
ቆጥሮ መሸማቀቅን ኮሌጅ ዉስጥ ኣዉቀዋለሁ። በተለይ የተማርኩኝ የመጨረሻዉ የህሳብ ኮርስ ዉስጥ። አስተማሪዉ ለማስተማር ብሎ ኢዩለር፣ ቴይለር፣ ፉርየ፣ ላ ጵላስ እያለ ስያስተምር እኔ ስም እየቆጠርኩ ተሸማቅቄኣለሁ።
ዶናልድ ትረምፕ ሆል ያለዉ ቀዳዳ ማለት ነዉ።
ምናልባትም ያንን መሸማቀቅ ስለማዉቅ ይሆናል ግምቴ ፍጹም የተለየ የሆነዉ።
በእኔ ግምት ዶናልድ ትረምፕ ስለ ኣፍርካ የተናገረዉ ቶማስ ጀፈርሰን ስለ ኣፍርካዊያን ከተናገረዉ የተለየ ኣይዴለም።
ቶማስ ጀፈርሰን ከሃገራቸዉ ተገደዉ አሜርካ የደረሱትን ኣፍርካዊያንን ቀርቦ ኣነጋግሮ የተናገረዉ ስለ ሰዉነት ገጽታ ሳይሆን ስለ ኣዕምሮ ችሎታ ነዉ። ይህ በማያሻማ ሁኔታ የጻፈዉ ደብዳቤ ዉስጥ ኣለ። ዉበት ያለዉ የምያዩ ዐይኖች ዉስጥ ነዉ ከተባለ ሰንብቷል።
ቶማስ ጀፈርሰን ማለት ስለ ጥንት ታሪክ እስከ ጎደስ አቴና ኣጥንቶ፣ አሜሪካ ዉስጥ እስላም ይሁን ሀይማኖት ዬለሽ ሙሉ የዜግነት መብት ሊኖረዉ ይገባል ብሎ በጽኑ የተከራከረ ነዉ።
በእሱ ግዜ ስልጣኔ የጀመረዉ ከጥንት ግብጥ ሳይሆን ከጥንት ግሪክ፣ ከፈረኦ አክናተን ሳይሆን ከጎደስ አቴና ነዉ ተብሎ ይታሰብ ነበር። አክናተን ከኣቴና አምስት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት የኖረ ቢሆንም።
በእኔ ግምት ቶማስ ጀፈርሰን ስለ ፈረኦ አክናተን በጥልቅ ኣጥንቶ የደረሰበት ቢሆን ኖሮ ጎሰኝነት አሜሪካ ዉስጥ ኣይስፋፋም ነበር።
ለዚህ ነዉ በእኔ ግምት ያኔ የተጀመረዉን የጎሰኝነት መስፋፋት ዶናልድ ትረምፕ ሽት ሆል ብሎ የተቀደደዉ።
ነገ የምንለዉ እነዚህን ቀዳዳዎች ተሯሩጦ ለመዝጋት እንጂ እየተቀደዱ ለመቅደድ ኣይዴለም።
የቤት ስራህን በደንብ ከሰራህ ቀዳዳዉ ግልጥ ብሎ ይታየሃል።
ቀዳዳዉን ለመዝጋት እንደ እነ ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ኒልሰን ማንዴላ የላቀ የኣዕምሮ ችሎታቸዉን ኣሳይተዋል።
በእኔ ግምት ከስሞን ባይልስ በላይ ጂንየስ ማን እንዳለ ኣላዉቅም። ኣዕምሮዋ ስንት ቀመሮችን በቅጽበት እየሰራ እንደምትገለባበጥ መገመት ያቅተኛል። ቶማስ ጀፈርሰን ተነስቶ ብያያት የሚደነቅ ይመስለኛል። ስሉ ሰምታ እንደሚባለዉ የሚቀደደዉ ዶናልድ ትረምፕ እያየ የማይደነቅ ነዉ።
እሱም ቢሆን ለፖለትካ ሽት ሆል ብሎ ተቀደደ እንጂ እንደ ግለሰብ የእሱ ኣዕምሮ የፈጠረን ኣንድ ኣዲስ ነገር መኖሩን ኣላዉቅም። እሱ ይቅር እና እንግልዝ ስግብግብ ሆና ሰብስባ ነዉ እንጂ እነዚህ ሁሉ ፈጠራዎች በእንግሊዛዊያን ብቻ ኣይዴሉም።
የኛዎቹ ደግሞ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወድያ እንደሚባለዉ የሆኑ ይመስላል።