Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Assegid S.
Member
Posts: 950
Joined: 11 Aug 2013, 07:11
Contact:

የ-አሻጋሪው ፀሎት

Post by Assegid S. » 05 Aug 2024, 12:31

https://www.eaglewingss.com/



ሰሞኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ “ቢጠባ ቢጠባ እንደማይነጥፍ የእናት ጡት ነው” ብለው ካሞካሹዋቸው ዓለም አቀፍ አራጣ ሰብሳቢ ድርጅቶች ለሚቀበሉት ብድር “አደረኩ” ያሉትን “የገንዘብ ምንዛሪ ማሻሻያ” አስመልክቶ የሰጡት ገለፃ ... ሃሰት፣ ከኢኮኖሚያዊ መርሕ እና ሥርዓት ውጪ ማስተባበያ የተሞላ ብቻም ሳይሆን፣ “ቢያልቅም ደሃው ነው የሚያልቀው” የሚል የግዴለሽነት ስሜት ያዘለ ነበር። ቢሮክራቱና ባለሥልጣናቱ ከደሞዛቸው አልፎ የሚዘርፉት ካዝና እንዲሞላ “ደሃው በኣናቱ ይተከል” አይነት እሳቤ እጅግ ያሸማቅቃል።

ምስኪኑ ህዝብ የእራሱንና የልጆቹን ጉሮሮ አርጥቦ ኣንዲት ዕለት ማደር እንደ ኣንድ ሺህ ቀናት ረዝሞ ጣር እንደሆነበት በመርሳት …  “ብትራቡም ለኣንድ ዓመት ነው” ብሎ መዘበት አስተዛዛቢ ነው። ለመሆኑ የምን ዋጋ (product / service price) ነው በየትኛው የገበያ Ceteris paribus እሳቤ ከኣንድ ዓመት ቦሓላ ወደ ኋላ ተመልሶ ከነበረበት ቦታ ሲገባ ያየነው? ነው ወይንስ ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ትላንትን አያስተውልም “short memory” ነው ያለው ብለው እንዳሰቡ ነው? ለማንኛውም ግን፦ ግዴለሽነታቸው፣ ህዝብን ረስተው ሥልጣናቸውን ብቻ ማሰባቸው ይህቺን ግጥም እንድፅፍ አድርጎኛል።

የ-አሻጋሪው ፀሎት

ሰሜን በጥይት ዶፍ
ደቡብ በጭቃ ጎርፍ
ምስራቅ በረሃብ ጅራፍ
ምዕራብ በስለት ኣፍ
ላይበቅል እንደ ዘር
ረግፎ ቢሆን ኣፈር …

ደጃፉ ተዘግቶ 
ቅዬው ኦና ቀርቶ
አልቆ ሰው እንስሳው
ጭር ቢል ከተማው …
አሜን! ተመስገን! ነው
ለመብራት - ዘንባባው

ኑሮ ሽቅብ ጋሽቦ
ህይወት ቁልቁል ጋልቦ
ሰውም እንደ ቅጠል  
ቀሎ ቢንጠለጠል …

ከሚራመድ አጥንት
ፈጥኖ  የቆመ እንጨት
ቢሸለምም ዋጋ
ግንድ ቀድሞ ከስጋ …

“ልጅህን” ብቻ አደራ
“ከአህዛብ” መከራ!
ብቻውንም ቢሆን
አሻግረው ባህሩን!

ዳር-ዳሩም ቢናጋ
መሓሉ እንደ ረጋ
ወንበሬ አደባባይ … ሆኖ ሰፊ ሜዳ   
ምድሩን አድርገኸው … “ከጉንዳን” የፀዳ
እንዲህ እንደ አሁኑ … እግሬ እንደተዘርጋ
እልፍ ማለዳ መሽቶ … እልፍ ለሊት ይንጋ!


N.B. የዚህን አጭር ግጥም ቃላቶች በተቻለ መጠን ለማንኛውም አንባቢ ግልፅ ትርጉም እንዲኖራቸው ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ያም ሆኖ ግን የተወሰኑ ቃላቶችና ስንኞች  ድርብ ብቻ ሳይሆን ድርብርብ ትርጉም አላቸው።  ለእነርሱም መግለጫ (ፍቺ) ከመስጠት ይልቅ literally 'catch me if you can’ ብዬ ማለፉን መርጫለሁ።