Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Bashuu
Member
Posts: 15
Joined: 15 Jul 2023, 21:32

Abiy Ahmed's Condemning Addis Residents Into Homelessness Continued Anabated!

Post by Bashuu » 03 Jul 2024, 18:42

The Ethiopian Reporter July 3


በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየካ ክፍለ ከተማ ከመለስ ፋውንዴሽን ወደ አዋሬ (አቧሬ) የሚወስድ መንገድ ለመገንባት በቀድሞዎቹ ቀበሌ 23፣ 18 እና ቀበሌ 19 (በአሁኑ ወረዳ 6) በግንፍሌ ወንዝ ግራና ቀኝ የሚገኙ ባለይዞታዎች (ነዋሪዎች)፣ ገሚሶቹ ያለ ማስጠንቀቂያ፣ የካሳ ግምትና ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጣቸው መኖሪያ ቤታቸው መፍረሱን፣ የተወሰኑት ደግሞ ባልታሰበ ጊዜ እንደሚፈርስ ተነግሯቸው፣ ከፍተኛ ሐሳብና ችግር ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ የፈረሰባቸው በዘመድ ቤት፣ በቀበሌ አዳራሽና ወጣቶች ማዕከል ውስጥ አንድ ላይ ታጉረው እንደሚገኙም አክለዋል፡፡

በተለምዶ አዋሬ የሚባለውን አካባቢ ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የልማት ተነሺ የሆኑ ባለይዞታዎች፣ ምትክ ቦታ ባለማግኘታቸው በዘመድ ቤት ተጠግተው እየኖሩ እንደሆነ በምሬት ተናገሩ፡፡

በአዋሬ ጤፍ ሠፈር አካባቢ ሕጋዊነት ያለው የግል ይዞታ ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መንግሥት በልማት ምክንያት እንዲነሱ ካደረጋቸው በኋላ ምንም ዓይነት ካሳ ወይም ተለዋጭ የምትክ ቦታ እስካሁን ስላልተሰጣቸው፣ ዘመድ ቤት ተጠግተው ለመኖር መገደዳቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ለረዥም ዓመታት በአካባቢው መኖራቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ መንግሥት ‹‹ቦታው ለልማት ይፈልጋል›› በማለት የአንድ ሳምንት የዝግጅት ጊዜ ሳይሰጣቸው ቤታቸውን በላያቸው ላይ ማፍረሱን ገልጸዋል፡፡

በአዋሬ ለረዥም ጊዜ በመኖር አካባቢውን ያቀኑ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሚመለከተው አካልም ሆነ መንግሥት፣ የደረሰባቸውን ችግር በማየት አፋጣኝ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

‹‹ጤፍ ሠፈር›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ50 ዓመታት በላይ የኖሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እናት፣ ከበፊት ጀምሮ ግዴታቸውን በመወጣት ግብር ይከፍሉበት የነበረውንና ሕጋዊነት ያለው 475 ካሬ ሜትር ይዞታ መንግሥት ነጥቆኛል ይላሉ፡፡

መንግሥት ከሚኖሩበት ቤት እንዲወጡ ካደረጋቸው አንድ ወር መቆጠሩን፣ እስካሁን ‹‹ተለዋጭ ቦታ ይሰጣችኋል ቆዩ›› መባላቸውን እንጂ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ያስረዳሉ፡፡

ችግራቸው እንዲታይላቸው የአካባቢውን ወረዳም ሆነ ክፍለ ከተማውን መጠየቃቸውንና እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ እንኳን እንዳላገኙ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት በጣም ችግር ውስጥ ሆነው ዘመድ ዘንድ ተጠግተው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን አነስተኛ ቤቶች ያከራዩ እንደነበር፣ አሁን ግን ሁሉ ነገር ተገላቢጦሽ እንደሆነባቸውና የዕለት ጉርሳቸውን ካስጠጓቸው ሰዎች እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ በአካባቢው ለ30 ዓመታት በመኖር ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ደጉንና ክፉውን አሳልፈናል የሚለው ወጣት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ መንግሥት የኮሪደር ልማት ብሎ ሲነሳ ታሳቢ ማድረግ የነበረበት ጉዳዮች ሊኖሩ ይገባ ነበር ይላል፡፡ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሆነው ሕጋዊ የቦታ ይዞታ ያላቸውን ሰዎች እንዴትና የት ማድረግ አለብኝ የሚለውን ማሰብ ነበረበት ሲልም ያስረዳል፡፡

በአዋሬ አካባቢ በርካታ አቅመ ደካማ አረጋውያን እንዳሉና ለአብነትም የእሱ እናት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጾ፣ በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ልዩነት ውስጥ ዕቃችሁን አውጡ ቤታችሁ ሊፈርስ ነው መባላቸውን ገልጿል፡፡

የመኖሪያ ቤታቸው የአየር ካርታ እንዳለውና በወረዳው የሚታወቅ መሆኑን የሚገልጸው ወጣቱ፣ በአሁኑ ወቅት አቅመ ደካማ እናቱን ይዞ አካባቢው በሚገኝ የወጣት ማዕከል ተጠለሉ መባሉን ያስረዳል፡፡

‹‹የአየር ካርታ ያላቸው ነዋሪዎች ተተኪ ቦታም ሆነ የካሳ ክፍያ አያገኙም፤›› የሚል ጭምጭምታ መስማቱን፣ በአካባቢው በእንዲህ ዓይነት መሰል ጉዳይ ቤታቸው የፈረሱ ሰዎች ቅሬታቸውን ለወረዳውም ሆነ ለክፍለ ከተማው ማስገባታቸውን ይናገራል፡፡

በተለይ መጪው ወቅት ክረምት መሆኑ በርካታ ሰዎችን እንዳሳሰበ የሚናገረው ወጣቱ፣ መንግሥት ይህንን ታሳቢ አድርጎ በልማት ለተነሱ የአካባቢው ነዋሪዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል ብሏል፡፡

ከ50 ዓመታት በላይ ወልደው፣ ከብደውና ልጆቻቸውን አሳድገው ብዙ ማዕረግ ያዩበትን ሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ቤታቸውንና ድርጅታቸውን በሦስት ቀናት ውስጥ አፍርሱ መባላቸውን የገለጹት፣ የቀድሞ ቀበሌ 23 (ወረዳ 6) ነዋሪ እናት ሲሆኑ፣ ልማቱን እንደማይቃወሙ፣ ነገር ግን ሕጉን የጠበቀ ግምትና ምትክ ቦታ፣ እንዲሁም ጊዜያዊ ቢሆንም መቆያ ቦታ ከእነክራዩ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ መንገዱ የሚወስደውን ቦታ ከግምት በማስገባትም ቀሪው ቦታ ላይ ፕላኑን የጠበቀ ግንባታ እንዲያካሂዱ እንዲፈቀድላቸውም ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ከመገናኛ ወደ ሰሚት አካባቢዎች በሚወስደው መንገድ በርካታ የግል ይዞታ ያላቸው ነዋሪዎች መነሳታቸውን ባለይዞታዎች ተናግረዋል፡፡